የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • wp17 ቁጥር 2 ገጽ 8-9
  • ሳያገቡ መኖር ከክርስቲያን አገልጋዮች የሚጠበቅ ብቃት ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሳያገቡ መኖር ከክርስቲያን አገልጋዮች የሚጠበቅ ብቃት ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2017
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሳያገቡ መኖር እና የሃይማኖት ታሪክ
  • አምላክ ያለው አመለካከት
  • ለምሥራቹ ሲሉ
  • ብሕትውና ከክርስቲያን አገልጋዮች የሚፈለግ ብቃት ነውን?
    ንቁ!—1998
  • ነጠላነት አሳብ ሳይከፋፈል ለማገልገል የሚያስችል አጋጣሚ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ነጠላነታችሁን በጥበብ ተጠቀሙበት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2017
wp17 ቁጥር 2 ገጽ 8-9
ኢየሱስ የጴጥሮስን አማት ሲፈውሳት

ኢየሱስ የጴጥሮስን አማት ሄዶ የጠየቃት ሲሆን ከሕመሟም ፈውሷታል።—ማቴዎስ 8:14, 15፤ ማርቆስ 1:29-31

ሳያገቡ መኖር ከክርስቲያን አገልጋዮች የሚጠበቅ ብቃት ነው?

የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፣ የተለያዩ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናት፣ ቡዲሂዝም እንዲሁም በዓለም ዙሪያ ያሉ ሌሎች ሃይማኖቶች መሪዎቻቸውና ቀሳውስቶቻቸው ሳያገቡ መኖር እንዳለባቸው ያስተምራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ይህ አቋም የተለያዩ ሃይማኖቶች ቀሳውስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየፈጸሙ ላሉት የፆታ ቅሌት ዋነኛ መንስኤ እንደሆነ የሚሰማቸው ብዙ ሰዎች አሉ።

በመሆኑም ‘ሳያገቡ መኖር ከክርስቲያን አገልጋዮች የሚጠበቅ ብቃት ነው?’ ብሎ መጠየቁ ምክንያታዊ ነው። ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት የዚህን ልማድ አመጣጥና ተቀባይነት ያገኘበትን መንገድ እንዲሁም አምላክ ይህን ልማድ አስመልክቶ ያለውን አመለካከት መመርመር ይኖርብናል።

ሳያገቡ መኖር እና የሃይማኖት ታሪክ

አብዛኛውን ጊዜ አንድ ክርስቲያን ‘ሳያገባ የሚኖረው እንዲሁም ከፆታ ግንኙነት የሚታቀበው የሃይማኖት መሪ አሊያም ለሃይማኖቱ ያደረ በመሆኑ ምክንያት’ እንደሆነ ኢንሳይክሎፒድያ ብሪታኒካ ገልጿል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክት 16ኛ፣ ከፍተኛ ቦታ ላላቸው የካቶሊክ መሪዎች (ለሮማ ኩሪያ) በ2006 ባቀረቡት ንግግር ላይ ሳያገቡ መኖር የክርስቲያን አገልጋዮች ብቃት የሆነው ‘ሐዋርያት ከነበሩበት ዘመን ብዙም ሳይርቅ’ እንደሆነ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች አንድ ሰው ክርስቲያን አገልጋይ መሆን ከፈለገ ሳያገባ መኖር አለበት የሚል አቋም አልነበራቸውም። እንዲያውም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረው ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ከመናፍስት የሚመነጩ አሳሳች ቃሎችን ከሚናገሩና ጋብቻን ከሚከለክሉ ሰዎች’ ራሳቸውን እንዲጠብቁ ክርስቲያኖችን አስጠንቅቆ ነበር።—1 ጢሞቴዎስ 4:1-3

ከጊዜ በኋላ የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን የመሠረቱት አብያተ ክርስቲያናት ሳይገቡ መኖርን እንደ ብቃት መመልከት የጀመሩት በሁለተኛው መቶ ዘመን ነው። ሴሊቤሲ ኤንድ ሪሊጂየስ ትራዲሽንስ የተባለው መጽሐፍ ይህ ልማድ “በሮም ግዛት ውስጥ በወቅቱ እየተስፋፋ ከነበረው ከፆታ ግንኙነት የመታቀብ አቋም ጋር የሚስማማ እንደነበር” ገልጿል።

በቀጣዮቹ መቶ ዘመናት የቤተ ክርስቲያን ምክር ቤቶች እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን አባቶች ተብለው የሚጠሩ ሰዎች ‘ክርስቲያን አገልጋይ ለመሆን ሳያገቡ መኖር ያስፈልጋል’ የሚለው ትምህርት እንዲስፋፋ አደረጉ። እነዚህ ሰዎች የፆታ ግንኙነት መፈጸም የሚያረክስና ከሃይማኖታዊ ኃላፊነቶች ጋር የሚጋጭ እንደሆነ ያስቡ ነበር። ይሁንና ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንደገለጸው “በ10ኛው መቶ ዘመን እንኳ በርካታ ቀሳውስት አልፎ ተርፎም አንዳንድ ጳጳሳት ሚስት ነበራቸው።”

ቀሳውስት ሳያገቡ መኖር እንደሚጠበቅባቸው የሚያዘው ደንብ ሥራ ላይ የዋለው በ1123 ዓ.ም. እና በ1139 ዓ.ም. በሮም በተደረጉት የላተራን ጉባኤዎች ላይ ሲሆን ከዚያን ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የምትመራበት ደንብ ሆኗል። ይህ ደንብ ቤተ ክርስቲያኗ የነበራትን ሥልጣን ይዛ መቀጠልና ብዙ ሀብት ማዳን እንድትችል ረድቷታል፤ ምክንያቱም ቀሳውስቷ ቢያገቡ ኖሮ የቤተ ክርስቲያኗን ንብረት ለልጆቻቸው መናዘዛቸው አይቀርም ነበር።

አምላክ ያለው አመለካከት

አምላክ ስለዚህ ጉዳይ ያለው አመለካከት በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ሰፍሯል። ኢየሱስ ልክ እንደ እሱ “ለመንግሥተ ሰማያት ሲሉ” ላለማግባት ስለወሰኑ ሰዎች የተናገራቸውን ቃላት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን። (ማቴዎስ 19:12) ሐዋርያው ጳውሎስም ‘ለምሥራቹ ሲሉ’ ሳያገቡ በመኖር ከእሱ ጋር ተመሳሳይ ውሳኔ ስላደረጉ ክርስቲያኖች ተናግሯል።—1 ቆሮንቶስ 7:37, 38፤ 9:23

ይሁንና ኢየሱስም ሆነ ጳውሎስ ክርስቲያን አገልጋዮች ሳያገቡ መኖር አለባቸው የሚል ትእዛዝ አልሰጡም። ኢየሱስ ሳያገቡ መኖር ‘ስጦታ’ እንደሆነና ይህ ስጦታ ያላቸው ሁሉም ተከታዮቹ እንዳልሆኑ ተናግሯል። ጳውሎስ ሳያገቡ መኖርን ደግፎ የተናገረ ቢሆንም “አግብተው የማያውቁትን በተመለከተ ከጌታ የተቀበልኩት ትእዛዝ የለኝም፤ ይሁን እንጂ . . . የራሴን ሐሳብ እሰጣለሁ” በማለት በሐቀኝነት ተናግሯል።—ማቴዎስ 19:11፤ 1 ቆሮንቶስ 7:25 የግርጌ ማስታወሻ

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስን ጨምሮ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ በርካታ ክርስቲያን አገልጋዮች ባለትዳሮች እንደነበሩ ይናገራል። (ማቴዎስ 8:14፤ ማርቆስ 1:29-31፤ 1 ቆሮንቶስ 9:5) እንዲያውም ጳውሎስ በወቅቱ በሮም ግዛት ውስጥ ተስፋፍቶ ከነበረው የሥነ ምግባር ብልግና አንጻር አንድ ክርስቲያን የበላይ ተመልካች ትዳር ያለው ከሆነ “የአንዲት ሚስት ባል” መሆን እንዳለበት፣ ልጆች ካሉት ደግሞ ልጆቹ “ታዛዥና ቁም ነገረኛ” መሆን እንዳለባቸው ጽፏል።—1 ጢሞቴዎስ 3:2, 4

ከላይ የተጠቀሱት ክርስቲያን አገልጋዮች ከትዳር ጓደኛቸው ጋር የፆታ ግንኙነት ይፈጽሙ ነበር። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ “ባል ለሚስቱ የሚገባትን ያድርግላት” ይላል፤ እንዲሁም ባለትዳሮች ከፆታ ግንኙነት ጋር በተያያዘ ‘አንዳቸው ለሌላው የሚገባውን መከልከል’ እንደሌለባቸው ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 7:3-5) ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው አምላክ አገልጋዮቹ እንዳያገቡ አይከለክልም፤ ሳያገቡ መኖር ከክርስቲያን አገልጋዮች የሚጠበቅ ብቃትም አይደለም።

ለምሥራቹ ሲሉ

ሳያገቡ መኖር ከክርስቲያን አገልጋዮች የሚጠበቅ ብቃት ካልሆነ ኢየሱስም ሆነ ጳውሎስ ነጠላነትን ያበረታቱት ለምንድን ነው? ምክንያቱም አንድ ሰው ሳያገባ መኖሩ ምሥራቹን ለሌሎች ለመስበክ የሚያስችል ሰፊ አጋጣሚ ይሰጠዋል። ያላገቡ ክርስቲያኖች፣ ባለትዳሮች ካለባቸው ጭንቀት ነፃ ስለሆኑ ምሥራቹን በማስፋፋት ረገድ የበለጠ አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላሉ።—1 ቆሮንቶስ 7:32-35

እስቲ የዴቪድን ምሳሌ እንመልከት፤ ዴቪድ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስተማር ሲል በሜክሲኮ ሲቲ የነበረውን ጥሩ ደመወዝ የሚያስገኝ ሥራ ለቀቀ፤ ከዚያም በኮስታ ሪካ ወዳለ ገጠራማ ስፍራ ተዛወረ። ዴቪድ አለማግባቱ ይህን ውሳኔ ለማድረግ እንደረዳው ይሰማዋል? እንዲህ ብሏል፦ “አለማግባቴ እንደረዳኝ ጥርጥር የለውም። ከአዲስ ባሕልና የኑሮ ሁኔታ ጋር መላመድ ቀላል አልነበረም። ሆኖም ብቻዬን መሆኔ ቶሎ መላመድ እንድችል ረድቶኛል።”

ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ተዛውራ የምታገለግለውና ያላገባች ክርስቲያን የሆነችው ክላውዲያ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ለአምላክ በማቀርበው አገልግሎት ደስተኛ ነኝ። አምላክ ምን ያህል እንደሚንከባከበኝ ስመለከት በእሱ ላይ ያለኝ እምነትና ከእሱ ጋር የመሠረትኩት ዝምድና ይጠናከራል።”

“ማግባት ወይም አለማግባት ምንም ለውጥ አያመጣም። ለይሖዋ አምላክ ምርጣችሁን እስከሰጣችሁ ድረስ ደስተኛ ትሆናላችሁ።”—ክላውዲያ

አንድ ሰው አለማግባቱ ሸክም ሊሆንበት አይገባም። ክላውዲያ አክላም እንዲህ ብላለች፦ “ማግባት ወይም አለማግባት ምንም ለውጥ አያመጣም። ለይሖዋ አምላክ ምርጣችሁን እስከሰጣችሁ ድረስ ደስተኛ ትሆናላችሁ።”—መዝሙር 119:1, 2

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ