የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • wp18 ቁጥር 2 ገጽ 4-5
  • ኮከብ ቆጠራና ጥንቆላ—የወደፊቱን ጊዜ ለማወቅ ያስችላሉ?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ኮከብ ቆጠራና ጥንቆላ—የወደፊቱን ጊዜ ለማወቅ ያስችላሉ?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2018
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ኮከብ ቆጠራ
  • ጥንቆላ
  • መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
  • ኮከብ ቆጠራ የወደፊት ዕጣህን እንድታውቅ ያስችልሃል?
    ንቁ!—2005
  • ከዋክብት በሕይወትህ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይገባልን?
    ንቁ!—2000
  • ከዋክብት በሕይወትህ ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ አለ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2010
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2018
wp18 ቁጥር 2 ገጽ 4-5
ኮከብ ቆጣሪዎች የሚጠቀሙበት ካርታ

ኮከብ ቆጠራና ጥንቆላ—የወደፊቱን ጊዜ ለማወቅ ያስችላሉ?

ኮከብ ቆጠራ

ኮከብ ቆጠራ የሚባለው ከዋክብት፣ ጨረቃና ፕላኔቶች በምድር ላይ ባሉ ሰዎች ሕይወት ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳድራሉ በሚለው እምነት ላይ የተመሠረተ የጥንቆላ ዓይነት ነው። ኮከብ ቆጣሪዎች፣ እነዚህ የሰማይ አካላት አንድ ሰው በተወለደበት ወቅት ያላቸው አቀማመጥ የግለሰቡን ባሕርይና የወደፊት ዕጣ እንደሚወስን ይናገራሉ።

ኮከብ ቆጠራ የተጀመረው በጥንቷ ባቢሎን ቢሆንም አሁንም በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት አለው። በዩናይትድ ስቴትስ በ2012 የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚጠቁመው በጥናቱ ከተካፈሉት ሰዎች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ኮከብ ቆጠራ “ሳይንሳዊ ሳይሆን እንደማይቀር” ይሰማቸዋል፤ አሥር በመቶ የሚሆኑት ደግሞ “በሳይንስ የተደገፈ” እንደሆነ ተናግረዋል። ግን እውነታው ይህ ነው? በጭራሽ። እስቲ እንዲህ እንድንል የሚያደርጉንን ምክንያቶች እንመልከት።

  • ፕላኔቶችና ከዋክብት ኮከብ ቆጣሪዎች በሚገልጹት መንገድ በሰዎች ሕይወት ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር የሚያስችል ኃይል የላቸውም።

  • ኮከብ ቆጣሪዎች ብዙውን ጊዜ ትንቢት የሚናገሩት እንዲሁ በደፈናው ስለሆነ በማንም ሰው ላይ ሊፈጸሙ ይችላሉ።

  • ኮከብ ቆጣሪዎች በዛሬው ጊዜ የሚጠቀሙበት ስሌት የተመሠረተው ‘ፕላኔቶች የሚዞሩት በምድር ዙሪያ ነው’ በሚለው ጥንታዊ አመለካከት ላይ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ፕላኔቶች የሚዞሩት በፀሐይ ዙሪያ ነው።

  • የተለያዩ ኮከብ ቆጣሪዎች ስለ አንድ ግለሰብ የሚናገሯቸው ትንበያዎች አይመሳሰሉም።

  • ኮከብ ቆጣሪዎች፣ ሰዎችን የተወለዱበትን ቀን መሠረት በማድረግ በ12 የዞዲያክ ምልክቶች ሥር ይመድባሉ። ሆኖም ባለፉት መቶ ዘመናት ምድር በጠፈር ውስጥ የምትገኝበት ቦታ በጊዜ ሂደት ስለተቀየረ በተለያዩ የዞዲያክ ምልክቶች የሚወከሉት ቀናት፣ ቀደም ሲል ስማቸው ከተሰየመበት ኅብረ ከዋክብት ጋር አይጣጣሙም።

የዞዲያክ ምልክቶች ስለ አንድ ሰው ባሕርይ ፍንጭ እንደሚሰጡ ይነገራል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በአንድ ቀን የተወለዱ ሰዎች ተመሳሳይ ባሕርይ የላቸውም፤ አንድ ሰው የተወለደበት ቀን ከባሕርይው ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። ኮከብ ቆጣሪዎች የአንድን ግለሰብ እውነተኛ ማንነት ከመመልከት ይልቅ አስቀድመው ያስቀመጧቸውን መላ ምቶች መሠረት በማድረግ የግለሰቡ ባሕርይ እንዲህ ነው ብለው ይናገራሉ። ታዲያ ይህ ፍርደ ገምድልነት አይደለም?

ጥንቆላ

ሰዎች ከጥንት ጀምሮ ወደ ጠንቋዮች ይሄዱ ነበር። አንዳንድ ጠንቋዮች ስለ አንድ ነገር ለማወቅ የእንስሳትንና የሰዎችን ሆድ ዕቃ እንዲሁም ዶሮ ጥሬ የሚለቅምበትን መንገድ ይመረምሩ ነበር። ሌሎች ደግሞ ሻይ ወይም ቡና ከጠጡ በኋላ ሲኒ ውስጥ የቀረውን ዝቃጭ በመመልከት ትንቢት ይናገራሉ። በዛሬው ጊዜ ደግሞ ጠንቋዮች ስለ አንድ ሰው የወደፊት ሕይወት ለማወቅ የጥንቆላ ካርድ፣ የክሪስታል ኳስ፣ ዳይ እና እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎች ዘዴዎችን ይጠቀማሉ። ታዲያ በጥንቆላ አማካኝነት ስለ ወደፊቱ ጊዜ በትክክል ማወቅ ይቻላል? በፍጹም። እንዲህ የምንለው ለምን እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

መጀመሪያ ትንቢቶቹ እርስ በርስ ይስማማሉ አይስማሙም የሚለውን ጉዳይ እንመርምር። ጠንቋዮች ስለ አንድ ጉዳይ የሚናገሩት ትንቢት በአብዛኛው እርስ በርሱ ይጋጫል። የሚጠቀሙበት ዘዴ ተመሳሳይ ሆኖ እንኳ የሚናገሯቸው ትንበያዎች ይለያያሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው የእጁን መዳፍ “አንብበው” ስለ ወደፊቱ ጊዜ እንዲነግሩት ሁለት ጠንቋዮችን ቢጠይቅ የሚሰጡት መልስ ተመሳሳይ ይሆናል ብለን መጠበቃችን ምክንያታዊ ነው። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ መልሳቸው ተመሳሳይ አይደለም።

ጠንቋዮች የሚጠቀሙበት ዘዴም ሆነ ትንቢት የሚናገሩበት ዓላማ ጥርጣሬ የሚፈጥር ነው። አንዳንድ ሰዎች ካርዶቹ ወይም የክሪስታል ኳሶቹ ምንም ጥቅም እንደሌላቸው ይናገራሉ። ጠንቋዩ የሚተነብየው ቁሳቁሶቹን በመጠቀም ሳይሆን የግለሰቡን ሁኔታ በመመልከት ነው። አንድ ጠንቋይ ግለሰቡን የተለያዩ ጥያቄዎች ይጠይቀዋል፤ ግለሰቡ ለጥያቄዎቹ የሚሰጠውን መልስና አኳኋኑን በሚገባ በማጤን አንድ ዓይነት መደምደሚያ ላይ ይደርሳል። ከዚያም ጠንቋዩ ግለሰቡ ሳይታወቀው የሰጠውን መረጃ በመጠቀም የሚናገራቸውን ነገሮች እሱ ራሱ እንዳወቃቸው ስለሚታሰብ የሌሎችን አድናቆት ያተርፋል። አንዳንድ ጠንቋዮች ወደ እነሱ የሚመጡ ሰዎችን አመኔታ በማትረፋቸው በርካታ ገንዘብ ማጋበስ ችለዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ኮከብ ቆጠራና ጥንቆላ የወደፊት ሕይወታችን አስቀድሞ ተወስኗል የሚለውን ሐሳብ ያስፋፋሉ። ግን እውነታው ይህ ነው? የምናምንበትን ነገርና ማድረግ የምንፈልገውን ነገር የመምረጥ ነፃነት እንዳለን እንዲሁም የወደፊት ሕይወታችን የተመካው በምናደርገው ምርጫ ላይ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ኢያሱ 24:15

እውነተኛውን አምላክ የሚያመልኩ ሰዎች ከኮከብ ቆጠራና ከጥንቆላ ለመራቅ የሚያነሳሳ ሌላም ምክንያት አላቸው፤ አምላክ የትኛውንም የጥንቆላ ድርጊት ይጠላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ሟርተኛ፣ አስማተኛ፣ ሞራ ገላጭ፣ ምትሃተኛ፣ ድግምተኛ፣ መናፍስት ጠሪ፣ ጠንቋይ ወይም ሙታን አነጋጋሪ በመካከልህ አይገኝ። ምክንያቱም እነዚህን ነገሮች የሚያደርግ ሰው ሁሉ በይሖዋ ፊት አስጸያፊ ነው።”a—ዘዳግም 18:10-12

a ይሖዋ የሚለው ስም “በመላው ምድር ላይ ልዑል” የሆነው አምላክ ስም ነው።—መዝሙር 83:18

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ