“የአገልግሎት ስልታችሁን የምትቀያይሩ ሁኑ
1 የተለያዩ ዓይነት ነገሮች መኖራቸው ለሕይወት ቅመም ነው ይባላል። ብዙውን ጊዜ አንድን ጉዳይ ከተለያየ አቅጣጫዎች አንፃር ማየቱ ነገሩን ይበልጥ ማራኪ ያደርገዋል። ይህ ሁኔታ አገልግሎታችንንም በተመለከተ እውነት ነው። ጠንቃቆች ካልሆንን ከቤት ወደ ቤት ይዘነው የምንሄደው መልእክት ሁልጊዜ አንድ ዓይነት ሊሆን ይችላል። አንድ ዓይነት መግቢያዎችን አሁንም አሁንም መደጋገም ለእኛም ሆነ ለቤቱ ባለቤት አሰልቺ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ የአገልግሎት ስልታችሁን የምትቀያይሩ ሁኑ። ግን እንዲህ ልታደርጉ የምትችሉት እንዴት ነው?
2 ‘እንደምን አደሩ። የመንግሥቱን ምሥራች ለማሰማት ጎረቤቶቻችንን እየጠየቅን ነው’ ከማለት ወይም ተመሳሳይ ነገር ከመናገር ይልቅ የመክፈቻ ቃላታችሁን ለመቀያየር ለምን መንገድ አትፈልጉም? ምክንያቱን ማስረዳት የተባለው መጽሐፍ መግቢያዎችን በሚመለከት ብዙ ሐሳቦች አሉት። ከገጽ 9–15 ላይ 18 የተለያዩ ርዕሶችን የሚመለከቱ መግቢያዎች አሉት። ለአብዛኞቹ ርዕሶች ደግሞ ሁለት፣ ሦስት ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑ ተስማሚ መግቢያዎች ይኖራሉ።
3 “አምላክ ስለ እኛ በእርግጥ ያስባልን?” የተባለውን ብሮሹር የምትጠቀሙ ከሆነ በገጽ 13 ላይ “ሕይወት/ደስታ” በሚለው ሥር ያለው መግቢያ ይረዳችሁ ይሆናል፦
◼ በዛሬ ጊዜ ያለው የኑሮ ሁኔታ በጣም ካሳሰባቸው ሰዎች ጋር እየተወያየን ነበር። ብዙዎች እውነተኛ ደስታ ያለበት ሕይወት ማግኘት ይቻል ይሆን? ብለው ያስባሉ። ይህ ብሮሹር የሚያበረታታና አእምሮን የሚቀሰቅስ ሐሳብ አለው።” ብሮሹሩን ገጽ 25 ላይ ግለጥና ከአንቀጽ 15 እና 16 ላይ አንድ ወይም ሁለት ጎላ ያሉ ነጥቦችን አንብብ።
4 አንዳንድ የመንግሥቱ አስፋፊዎች በተለይም ወጣቶችና አዲሶች እንዲሁም ትልልቆች ጭምር በትራክት ተጠቅሞ ሰዎችን በጥሩ ሁኔታ ማነጋገር የሚቻል ሆኖ አግኝተውታል።
አንድ ወጣት አስፋፊ “በቤተሰብ ኑሮ ተደሰት” በተባለው ትራክት ተጠቅሞ እንዲህ ሊል ይችል ይሆናል፦
◼ “አምላክ ቤተሰቦችን እንዴት በደስታ ሊያስተባብራቸው እንደሚችል የምትገልጽ አጠር ያለች መልእክት አለችኝ። በቤተሰብ ኑሮ ተደሰት የተባለችውን ይህችን ትራክት ብሰጥዎት ደስ ይለኛል።” ከዚያ በኋላ ከወጣቱ ጋር አብሮ እየሠራ ያለው ትልቅ አስፋፊ የቤቱ ባለቤት በሰጠው መልስ ላይ በመመርኮዝ ተጨማሪ ሐሳቦች ወይም አስተያየቶችን ለመስጠት ይቻል እንደሆነ ይወስናል።
5 የቤቱ ባለቤት ፍላጎት ካሳየ ትልቁ አስፋፊ እንዲህ ሊል ይችላል፦
◼ “መጽሐፍ ቅዱስ ባል፣ ሚስትና ልጆች በቤተሰብ ዝግጅት ውስጥ ሊጫወቱት ስለሚገባቸው ሚና መመሪያዎችን ይሰጣል። ቤተሰብ የሚባለው ነገር የመጣው ከአምላክ እንደመሆኑ መጠን ቤተሰብ እንዴት መሥራት እንዳለበት ከማንም በተሻለ ሁኔታ ሊነግረን የሚችለው እርሱ ነው ቢባል አይስማሙምን? መጽሐፍ ቅዱስ ለቤተሰብ አባሎች በሚሰጠው ግልጽ ምክር ላይ ያለዎትን አስተያየት ብሰማ ደስ ይለኛል።” ከዚያም ኤፌሶን 5:22, 23, 28–31ን አንብብ።
6 ራእይ ታላቁ መደምደሚያው የተባለውን መጽሐፍ የምታበረክቱ ከሆነ በራእይ 21:3, 4 ላይ የተገለጸውን ስለ ወደፊቱ የሚያመለክተውን መልካም ገጽታ ለምን አታጎሉም? ከዚያም በዚህ መጽሐፍ ገጽ 303 ላይ ያለውን አንቀጽ 7ን አንብቡ። አምላክ እነዚህን ተስፋዎች ያሟላልናል ብሎ ማመን ትክክል ይመስለው እንደሆነ የቤቱን ባለቤት ጠይቁት። እስካሁን በተፈጸሙት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ላይ አጠር ያለ ውይይት ማድረግ የቤቱ ባለቤት አምላክ የሰውን ዘሮች ለመባረክ ባለው ችሎታ ላይ ያለውን እምነት ያጠነክርለታል።
7 ሁሉም የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በሚቻልበት ቦታ የእውነትን ዘር በመዝራትና ቀደም ሲል የታየውን ፍላጎት በመኮትኮት ቲኦክራቲካዊ ጥቅሞችን በማራመዱ ሥራ ለመካፈል ይፈልጋሉ። እኛ የበኩላችንን በማድረግ ማንኛውንም ወደፊት ሊመጣ የሚችል ዕድገት በይሖዋ እጅ ላይ ልንተወው እንችላለን። ለጎረቤቶቻችን ልናካፍላቸው የምንችለው ከሁሉ የተሻለ ዜና አለን። ሁልጊዜ የተዘጋጀን በመሆን የመንግሥቱን መልእክት በማቅረብና ጽሑፎቻችንን እንዲወስዱ በመጠየቅ በኩል ስልታችንን የምንቀያይር ልንሆን እንችላለን።