በተደጋጋሚ በተሸፈኑ የአገልግሎት ክልሎች መሥራት
1 ብዙ ጉባኤዎች የአገልግሎት ክልላቸውን በተደጋጋሚ እየሸፈኑት እንዳሉ የሚገልጹ ሪፖርቶች ሲደርሱን ደስ ይለናል። (ማቴ. 24:14፤ 1 ጢሞ. 2:3, 4) ምንም እንኳን ይህ ለየት ያለ ፈታኝ ሁኔታ የሚያስከትል ቢሆንም ሊነሱ የሚችሉትን ልዩ ልዩ ሁኔታዎች ለመወጣት በደንብ የተዘጋጀንና የታጠቅን ከሆንን ሊሳካልን እንደሚችል ተሞክሮዎች አሳይተዋል።
2 ቁልፉ ውጤታማ በሆኑ መግቢያዎች መጠቀም ነው፦ አንድ ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑ በደንብ የታሰበባቸው መግቢያዎች ለመጠቀም መዘጋጀት በጣም አስፈላጊ ነው። መግቢያዎቻችን በተደጋጋሚ ወደ ቤታቸው የምንሄድባቸውን ዐበይት ምክንያቶች ጥርት አድርገው የሚገልጹ ቀጥተኛ ዐረፍተ ነገሮች ሊኖሩባቸው ይገባል።
3 ምክንያቱን ማስረዳት የተባለው መጽሐፍ ልንጠቀምባቸው ስለምንችላቸው ተስማሚ የሆኑ መግቢያዎች ጥሩ ጥሩ ምሳሌዎችን ይሰጣል። በገጽ 15 ላይ “ብዙ ጊዜ በተሠራባቸው የአገልግሎት ክልሎች” በሚለው ርዕስ ሥር ሦስት የመግቢያ ምሳሌዎች አሉ። በአገልግሎት ክልልህ ውስጥ ልትጠቀምባቸው የምትፈልጋቸውን መግቢያዎች ተለማመድባቸው።
4 በተደጋጋሚ በተሸፈኑ የአገልግሎት ክልሎች ውስጥ የሚያገለግሉ አንዳንድ አስፋፊዎች በአካባቢው ከሚወጣ ጋዜጣ ላይ ያገኟቸውን ዜናዎች ውይይት ለመጀመር ተጠቅመውባቸው የተሳካ ውጤት አግኝተዋል። ምክንያቱን ማስረዳት የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ማድረግ የምንችልባቸውን ሦስት ምሳሌዎች ይሰጣል። በገጽ 10 ላይ “ወንጀል/ደኅንነት” በሚለው ርዕስ ሥር ያለውን ሁለተኛ መግቢያና በገጽ 10ና 11 ላይ ያሉትን “ወቅታዊ ሁኔታዎች” በሚለው ርዕስ ሥር የሚገኙትን የመጀመሪያዎቹን ሁለት መግቢያዎች ተመልከት።
5 የምታዘጋጃቸው መግቢያዎች፦ ምክንያቱን ማስረዳት በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ከቀረቡት ጋር የሚመሳሰሉ ተገቢ የመግቢያ ሐሳቦች ፈጥረህ ለመጠቀም አታመንታ። መግቢያዎቹን በወትሮ አነጋገርህ በራስህ አባባል ተናገራቸው። መግቢያዎቹን በመስክ አገልግሎት ላይ ከመጠቀምህ በፊት ልምድ ካለው አንድ አስፋፊ ጋር ልትለማመድባቸው ትችላለህ።
6 ለምሳሌ ያህል ከዚህ በታች ካለው ጋር የሚመሳሰል ነገር ለማለት ትችል ይሆናል፦
◼ “ባለፈው መጥተን ካነጋገርንዎ በኋላ [በሰፈሩ ያሉ ሰዎች የሚነጋገሩበትን ሰሞኑን የተፈጸመ አንድ ነገር ጥቀስ።] ሁላችንም በአንድ ወይም በሌላ መልኩ በነገሩ መነካታችን ስለማይቀር ብዙ ጎረቤቶቻችን በጣም እንደተጨነቁ ይናገራሉ። ምናልባት እርስዎንም አሳስቦዎት ይሆናል። [ሰውየው ሐሳብ ሊሰጥ ስለሚችል ትንሽ ቆም በል።] ዛሬ ካለው የዓለም ሁኔታ አንፃር ነቢዩ ኤርምያስ በምዕራፍ 10 ቁጥር 23 ላይ ከጻፈው ሐሳብ ጋር አይስማሙም?” ጥቅሱን ካነበብክለት በኋላ ሰውየው የሚሰጠውን አስተያየት አዳምጥና ያነሳችሁትን ችግር ይሖዋ እንዴት እንደሚያስወግደው በሚገልጽ አንድ ጥቅስ ላይ እንዲያተኩር አድርግ።
7 ወይም እንዲህ ልትል ትችላለህ፦
◼ “በዛሬው ዜና ላይ [ወንጀልን ወይም የተፈጥሮ አደጋን አስመልክቶ የተፈጸመን አንድ ነገር ጥቀስ። ስለ ፖለቲካ አታንሳ።] እንደሰሙ አልጠራጠርም። ይህ ሁላችንንም የሚነካ ነገር ነው ቢባል ሳይስማሙ አይቀሩም። [ትንሽ ቆም በልና ሰውየው ሊሰጥ የሚችለውን ምላሽ አዳምጥ።] መንግሥት ለጊዜው የሚሆን መፍትሔ ሊያገኝለት እንደሚችል ተስፋ እናደርጋለን፤ ይሁን እንጂ ችግሩ ዘላቂ መፍትሔ እንዴት እንደሚያገኝ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል።” አምላክ ምን እንደሚያደርግ የሚያብራራ አንድ ጥቅስ አሳየው።
8 “ብዙ ጊዜ ደጋግማችሁ የምትመጡት ለምንድን ነው?” ምክንያቱን ማስረዳት በተባለው መጽሐፍ ገጽ 20 ላይ “ወደ ቤታችን አዘውትራችሁ የምትመጡት ለምንድን ነው?” በሚለው ርዕስ ሥር ውይይት ለማስቆም ለሚሰነዘር ለእንዲህ ዓይነቱ አስተያየት ልትሰጥ የምትችላቸው ተገቢ መልሶች ቀርበዋል። ባይጠይቁንም እንኳን አመቺ አጋጣሚ ባገኘን ጊዜ ሁሉ የቻልነውን ያህል ደጋግመን ወደ ቤታቸው በመሄድ እንድናናግራቸው የሚገፋፋን ለአምላክና ለጎረቤቶቻችን ያለንን ፍቅር መሆኑን እንዲገነዘቡ የሚረዳቸውን ጥሩ ምስክርነት ልንሰጣቸው እንችላለን። በዚህ ረገድ በዮሐንስ 21:15–17 ላይ በሚገኙት የኢየሱስ ቃላት ላይ ውይይት ማድረጉ በጣም ጠቃሚ ሆኖ ልናገኘው እንችል ይሆናል።
9 ይሖዋ በቃ እስኪል ድረስ በተደጋጋሚ በተሸፈነ የአገልግሎት ክልል ውስጥ ስንሠራ የሚያጋጥሙንን ፈታኝ ሁኔታዎች መቋቋማችንን እንቀጥል። እንዲህ ዓይነት ቁርጥ ውሳኔ ካለን የእርሱ መመሪያ፣ ጥበቃና በረከት እስከ መጨረሻው እንደማይለየን ልንተማመን እንችላለን። — ማቴ. 28:19, 20