በስብሰባዎች ላይ መገኘት አክብደን ልንመለከተው የሚገባ ኃላፊነት ነው
1 በስብሰባዎች ላይ መገኘትን ምን ያህል አክብዳችሁ ትመለከቱታላችሁ? ይህ ልብን የሚመረምር ጥያቄ ነው። አይደለምን? አብዛኞቻችን ስብሰባዎችን የምናደንቅ ሆኖ እንደሚሰማን ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ አንዳንዶች ከአንዳንድ ስብሰባዎች የመቅረት ልማድ ይኖራቸው ይሆናል። ለዚህ ምክንያቱ ምን ሊሆን ይችላል? አንዳንዶቻችን አላስፈላጊ የሆኑ ዓለማዊ ሥራዎች፣ ድካም፣ የቤት ሥራዎች፣ ቀለል ያሉ ሕመሞች ወይም መጥፎ የአየር ጠባይ በስብሰባዎች አዘውትረን እንድንገኝ ያለብንን ግዴታ እንዳንፈጽም እየፈቀድንላቸው ይሆን? (ዘዳ. 31:12) ይህ ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታ ስለሆነ እያንዳንዳችን እኔ በስብሰባዎች መገኘትን ምን ያህል አክብጄ እመለከተዋለሁ? የሚለውን ጥያቄ በጥሞና ልናስብበት ይገባናል።
2 አንዳንድ ወንድሞቻችን በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ሲሉ አቧራማ በሆኑ መንገዶች ለረጅም ሰዓታት ይጓዛሉ፤ አዞ የሞላባቸውንም ወንዞች ያቋርጣሉ። በጉባኤያችሁ ውስጥም ቢሆን ከባድ የጤና ችግሮች እያሉባቸው፣ አካለ ስንኩል ቢሆኑም፣ በመሥሪያ ቤታቸው ሥራ በጣም ቢበዛባቸውም ወይም ብዙ ጊዜ የሚፈጁ የትምህርት ቤት ሥራዎች ቢኖሩባቸውም ከስብሰባ ‘በጭራሽ የማይቀሩ’ ታማኝ ወንድሞችና እኅቶች ሊኖሩ ይችላሉ። (ሉቃስ 2:37) በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ይህን ያህል የሚጥሩት ለምንድን ነው? ምክንያቱም በተለያዩ ግፊቶች የተሞላውን የዚህን ዓለም ፈተና በራሳቸው ኃይል ሊቋቋሙት እንደማይችሉ ያውቃሉ። አምላክ የሚሰጠውን ኃይል ማግኘት አለባቸው። — 2 ቆሮ. 12:9, 10
3 ለጸሎት፣ ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥና የአምላክን ቃል ለማንበብ ሲሉ አዘውትረው ይሰበሰቡ የነበሩትን የጥንት ክርስቲያኖች ምሳሌ እንከተላለን። (ሥራ 4:23–30፤ 11:4–18፤ ቆላ. 4:16) በስብሰባ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችንና መሠረተ ትምህርቶችን፣ አምላካዊ ጠባዮችንና ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባሮችን የሚመለከቱ ትምህርቶች ይቀርቡልናል። እንዲሁም ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በጥንቃቄ በተግባር በማዋል በአሁኑ ጊዜ ሕይወታችንን እንዴት ልናሻሽል እንደምንችል ወቅታዊ ማሳሰቢያዎችን እናገኛለን። (1 ጢሞ. 4:8) ከዚህም በተጨማሪ አንድ ቀን ችግርና መከራ ሁሉ እንደሚያበቃ ያለንን ተስፋ እንድናስታውስ የሚረዳ ትምህርት እናገኛለን። ይህን ተስፋ ሁልጊዜ ሕያው አድርገን መጠበቃችን በጣም አስፈላጊ ነው። — ዕብ. 6:19
4 ቤተሰባችሁ በስብሰባዎች ላይ መገኘትን ምን ያህል አክብዶ ያየዋል? ለዕለታዊ ምግብ ወይም ለዓለማዊ ሥራ የምትሰጡትን ያህል ቦታ ትሰጡታላችሁን? ስብሰባ በሚደረግባቸው ቀናት እንሂድ አንሂድ እያላችሁ ትከራከራላችሁ ወይስ ከወንድሞቻችሁ ጋር አዘውትራችሁ መሰብሰብ ለቤተሰባችሁ አማራጭ የሌለው ነገር ነው? ብዙ አስፋፊዎች ራሳቸውን የወሰኑ ወላጆቻቸው ሲያሳድጓቸው ያሳዩአቸውን ምሳሌ ያስታውሱታል። አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ትዝ የሚለውን ነገር በጥሩ ስሜት ሲናገር “አባቴ ቤተሰባችን በስብሰባ ላይ እንዲገኝ ያደርግ እንደነበረ አልረሳውም። ከመካከላችን አንዱ ቢታመም አንዳችን አብረነው እቤት ስንቀር ሌሎቻችን ግን ወደ ስብሰባ እንሄድ ነበር!” ብሏል።
5 ለእነዚህ መንፈሳዊ ዝግጅቶች ያለንን አድናቆት ለመገንባት ይረዳን ዘንድ ከዚህ ቀጥሎ በሚወጡት ተከታታይ የመንግሥት አገልግሎታችን እትሞች ላይ እያንዳንዱ የጉባኤ ስብሰባ ምን ጥቅም እንዳለው እናብራራለን። በስብሰባዎች ላይ የመገኘት ልማዳችሁ መሻሻል ልታደርጉበት የሚገባ ከሆነ እያመለጣችሁ ያለውን ነገር እንድትገነዘቡ ይረዷችኋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። እነዚህ ወደፊት የሚወጡ ትምህርቶች ስብሰባዎችን ለሚመሩ ወንድሞች ጠቃሚ ማሳሰቢያዎችም አሉባቸው። እንዲሁም ሁላችንም ለስብሰባዎች ስንዘጋጅና በስብሰባዎች ላይ ስንሳተፍ በተግባር ልናውላቸው የምንችላቸውን ሐሳቦችን የያዙ ናቸው። በስብሰባዎች ላይ በመገኘት በኩል ያላችሁን ልማድ በቤተሰብ መልክ አንድ ላይ ሆናችሁ ለምን በጸሎት አታስቡበትም? ከዚያ በኋላ በፕሮግራማችሁ ላይ አስፈላጊውን ማስተካከያ አድርጉ። አዘውትሮ በስብሰባዎች ላይ መገኘት በጣም አስፈላጊ የሆነ ቲኦክራሲያዊ ትምህርት የምንቀስምበት አንዱ ክፍል በመሆኑ በእርግጥም አክብደን ልንመለከተው ይገባናል።