ሌሎች ሰዎች የጽሑፎቻችንን ዋጋማነት እንዲገነዘቡ መርዳት
1 “የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፣ የሚሠራም፣ . . . ነው።” (ዕብ. 4:12) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱት ጽሑፎቻችን ሰዎች የአምላክ ቃል ካለው ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ስለሚረዱ መደበኛ ባልሆነ መንገድም ይሁን ከቤት ወደ ቤት ስንመሰክር ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ለመቀስቀስ እንጠቀምባቸዋለን።
2 በጥር ወር የምናበረክተው መጽሐፍ ከጊዜ ብዛት በሚወይብ ወይም ቀለሙ እየደበዘዘ በሚሄድ ወረቀት የተዘጋጀ ወይም ከ1980 በፊት የታተሙትን ማንኛውንም ባለ 192 ገጽ መጻሕፍት ይሆናል። እንደነዚህ ዓይነት መጻሕፍት በጉባኤያችሁ የሚገኙ ከሆነ የሰዎችን ትኩረት በምታበረክተው መጽሐፍ ውስጥ ወደሚገኝ አንድ የተወሰነ ሐሳብ በመምራት የመንግሥቱን መልእክት ለመቅረብ የሚያስችልህን መንገድ ተለማመድ። ይህንን እንዴት ማድረግ ይቻላል?
3 እንዴት መዘጋጀት ትችላለህ? በመጀመሪያ ከምታበረክተው መጽሐፍ ውስጥ በአገልግሎት ክልልህ ውስጥ የሚገኙትን ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ይስባል ብለህ የምታስበውን ዓረፍተ ነገር ምረጥ። ከዚያም የቤቱን ባለቤት ትኩረት በመረጥኸው መጽሐፍ ውስጥ ወዳለው ዓረፍተ ነገር ከማዞርህ በፊት በአጭሩ ልታወያየው የምትችለውን የአብዛኛውን ሰው ትኩረት የሳበ አንድ ወቅታዊ ሁኔታ ወይም ርዕሰ ጉዳይ አስብ። ምናልባትም የተናገርከውን ሐሳብ የሚደግፍ ከመጽሐፍ ቅዱስ አውጥተህ እንድታነበው የተጠቀሰ ወይም ሐሳቡ እዛው መጽሐፉ ላይ የተጻፈ ጥቅስ ካለ ልታነበው ትችላለህ። የተለመደውን መዋጮ በመጠየቅ መጽሐፉን ልታበረክትለት ትችላለህ። ከዚያም ተመልሰህ ለመጠየቅ ስትሄድ መሠረት የሚሆንህ አንድ ጥያቄ ወይም ሐሳብ በማንሳት አንጠልጥለኸው ሂድ።
4 ብዙ ጉባኤዎች ወጣትነትህን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ተጠቀምበት እንዲሁም ታላቁን አስተማሪ ማዳመጥ የተባሉት መጻሕፍት አሏቸው። እነዚህ መጻሕፍት ካሏችሁ ለምን በአገልግሎት ክልልህ ውስጥ ከምታገኛቸው ወጣቶች ጋር ለመወያየት የሚያስችልህን ዝግጅት አታደርግም? ከእነዚህ ድንቅ መጽሐፎች መካከል አንዱን እንዲያነቡ አበረታታቸው። የምታበረክተው ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት የተባለውን መጽሐፍ ከሆነ ከላይ ባለው ዘዴ ተጠቅመህ በዚህ ግሩም የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ መጽሐፍ ውስጥ ካሉት ብዙ መሠረተ ትምህርቶች በአንዱ ላይ ለመወያየት ዝግጅት ለማድረግ ትችላለህ።
5 የሰው ልጅ አምላክን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ የተባለውን መጽሐፍ አበርክት፦ የሰዎችን ትኩረት ሃይማኖት በዓለም ጉዳይ ውስጥ ያደረገውን ጣልቃ ገብነት የሚያጎላ ወይም ደግሞ ሃይማኖት በሰዎች ሕይወት ላይ ያለውን ተጽዕኖ የሚያሳይ ዜና ጠቅሰህ ውይይት ለመክፈት ትችል ይሆናል።
ከዚያም እንደሚከተለው ያለ ጥያቄ ልታነሳ ትችላለህ፦
◼ “ዛሬ ባሉት የዓለም ሁኔታዎች ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን አምላክ እንዴት የሚመለከታቸው ይመስልዎታል? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] የእነዚህ ሁሉ ሃይማኖቶች መሠረታዊ ትምህርቶች በጣም ተመሳሳይ እንደሆኑና ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችም ጋር እጅግ የሚቃረኑ እንደሆኑ ቢነገርዎ አዲስ ነገር ይሆንብዎታልን?” የቤቱ ባለቤት ለማዳመጥ ፈቃደኛ ከሆነ የአርዕስት ማውጫውን አሳየውና አንድ ሰው ሃይማኖታዊ ሆነም አልሆነ ሕይወቱ ከፍተኛ ግፊት በሚያደርጉ ሃይማኖታዊ ተጽዕኖዎች እየተነካ እንደሆነ በአጭሩ ግለጽለት። የሰው ልጅ አምላክን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ እውነተኛውን ሃይማኖት ማወቅ ከሚቻልበት መንገድ ርቆ እንደዚህ የተለያየ አቅጣጫ የያዘው ለምን እንደሆነ በማወቁ ሊጠቀም እንደሚችል አስረዳው።
6 መጽሔቶችን ወይም ትራክት ማበርከት ይበልጥ ተስማሚ የሚሆንበት ጊዜም ይኖራል። የአምላክ ቃል ለሚሰጠው መመሪያ ምላሽ በመስጠት ከቃሉ በሚገኘው ኃይል በሕይወታቸው ለመጠቀም እንዲችሉ ሰዎች ጽሑፎቻችንን እንዲያነቧቸው ሞቅ ባለ ስሜትና በቅንዓት የምናበረታታበት ብዙ ምክንያት አለን።