‘ለሰው ሁሉ’ መመስከር
1 የተለያየ ባህል ወይም ሃይማኖታዊ ሁኔታ ያላቸው ሰዎች ስናገኝ የይሖዋ ፈቃድ ‘ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ’ መሆኑን አንዘነጋም። (1 ጢሞ. 2:4) ለተወሰነ አካባቢ ከተዘጋጁ በርካታ ትራክቶችና ብሮሹሮች በተጨማሪ የቀሰሙት ሃይማኖታዊ ትምህርት ስለ አምላክና ስለ ክርስቶስ እውነቱን እንዲያውቁ ያልረዳቸውን ሰዎች ለመጥቀም በማንኛውም ጊዜ ልንጠቀምባቸው የምንችላቸው ግሩም ጽሑፎች አሉን።
2 ለምሳሌ ያህል እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የተባለው መጽሐፍ የኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወት ጎላ አድርጎ ስለሚገልጽ አንድ ሰው በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ብዙ ሰዎች ስለ አምላክ ልጅ ጥሩ እውቀት እንዲያገኝና ወደ እርሱ እንዲቀርብ ሊረዳው ይችላል። (ዮሐ. 12:32) እኛም ማራኪ ሽፋን ያለውን የዚህ መጽሐፍ የአማርኛ እትም ለመጀመሪያ ጊዜ ማበርከት የምንችልበት አጋጣሚ አግኝተናል። ተስማሚ ሆኖ ስታገኘው ይህን መጽሐፍ ለማስተዋወቅ ቀጥሎ የቀረቡትን ሐሳቦች ለመጠቀም ትፈልግ ይሆናል።
3 “ታላቅ ሰው” የተባለውን መጽሐፍ ለማበርከት እንዲህ ብለህ መጠየቅ ትችላለህ:-
◼ “ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲነሣ ወደ ሐሳብዎ የሚመጣው ነገር ምንድን ነው? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ብዙ የታሪክ ምሁራን ኢየሱስ እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ ሰው መሆኑን ያምናሉ። [ታላቅ ሰው ከተባለው መጽሐፍ መግቢያ አንድ ምሳሌ ጥቀስ።] የኢየሱስ ሕይወት ልንከተለው የሚገባ አርአያ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጽልናል።” አንደኛ ጴጥሮስ 2:21ን ካነበብክ በኋላ ታላቅ ሰው ከተባለው መጽሐፍ መግቢያ ገጽ 13 ላይ ያለውን የመጀመሪያ አንቀጽ አንብብ። ከዚያም መጽሐፉን እንዲወስድ ጋብዘው። ከመለያየታችሁ በፊት ዮሐንስ 17:3ን አንብብና “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራውን ይህን እውቀት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?” ብለህ ጠይቅ። መልሱን ይዘህ የምትመለስበትን ቁርጥ ያለ ቀጠሮ ያዝ።
4 ሕይወት የሚያስገኘውን እውቀት እንዴት ማግኘት እንደሚቻል ለመግለጽ ተመልሰህ በምትሄድበት ጊዜ እንዲህ ማለት ትችላለህ:-
◼ “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራውን እውቀት ማግኘት የምንችልበትን መንገድ ላሳይዎት ተመልሼ እንደምመጣ ቃል ገብቼ ነበር።” እውቀት መጽሐፍን አስተዋውቅና የመጀመሪያውን ምዕራፍ በመጠቀም ጥናቱ እንዴት እንደሚካሄድ አሳየው።
5 ሌላ የመግቢያ ሐሳብ:-
◼ “ብዙ ወጣቶች ምሳሌ የሚሆናቸውን ሰው ለማግኘት ይፈልጋሉ። ሆኖም ጥሩ አርዓያ የሚሆን ሰው ማግኘት አይቻልም። ኢየሱስ ክርስቶስ ለሁላችንም ፍጹም ምሳሌ ይሆነናል። [1 ጴጥሮስ 2:21ን አንብብ።] መላ ሕይወቱ ያተኮረው ለሰማያዊ አባቱ በሚያቀርበው አምልኮ ላይ ነበር። ብዙ ሰዎች የእሱን አርአያ ለመከተል ቢጥሩ ምን ዓይነት ሁኔታ ይኖራል ብለው ያስባሉ?” መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት። ስለ ኢየሱስ ድንቅ ባሕርያት የሚገልጸውን በገጽ 447 ላይ ያለውን ሦስተኛውን አንቀጽ አሳየው። ታላቅ ሰው የተባለው መጽሐፍ ሁላችንም የተሻልን ክርስቲያኖች እንድንሆን እንዴት ሊረዳን እንደሚችል ግለጽለት።
6 እንደሚከተለው ያለ መግቢያ መጠቀም ትፈልግ ይሆናል:-
◼ “ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲነገር ብዙ ሰዎች ወደ አእምሯቸው የሚመጣው ሕፃን ልጅ ወይም በስቃይ ላይ ያለና ሊሞት የተቃረበ ሰው ነው። ስለ ኢየሱስ ያላቸው ግንዛቤ ከልደቱና ከሞቱ ጋር ብቻ የተያያዘ ነው። አብዛኛውን ጊዜ በሕይወቱ ዘመን የተናገራቸውና ያደረጋቸው አስደናቂ ነገሮች ሳይስተዋሉ ይቀራሉ። እሱ ያከናወናቸው ነገሮች በዚህች ምድር ላይ የኖረን ማንኛውንም ሰው ይነካል። ለእኛ ሲል ስላደረገልን አስደናቂ ነገሮች የቻልነውን ያህል መማራችን አስፈላጊ የሆነው ለዚህ ነው።” ዮሐንስ 17:3ን አንብብ። ታላቅ ሰው በተባለው መጽሐፍ መግቢያ የመጀመሪያ ገጽ ላይ ያለውን አራተኛ አንቀጽ አንብብ። መጽሐፉን እንዴት ማግኘት እንደሚችልና ለግል ጥናት እንዴት እንደሚጠቅመው ግለጽለት።
7 ሌላም አማራጭ አለ:-
◼ “ብዙዎች ኢየሱስ ሰው ሆኖ በዚህ ምድር ላይ ሲኖር ምን ዓይነት ሁኔታ እንደነበረው ለማወቅ ይፈልጋሉ። ከሌሎች ሰዎች የተለየ የነበረው በምን መንገዶች ነው ብለው ያስባሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የተባለው ይህ ማራኪ መጽሐፍ የኢየሱስን ሕይወትና አገልግሎት ዐበይት ገጽታዎች የሚነግረን ከመሆኑም ሌላ ምን ዓይነት ሰው እንደነበረ እንድናውቅ ያስችለናል። አንዳንዶች መጽሐፉን ካነበቡ በኋላ እሱን በአካል ለማግኘት፣ ስቃዩን ለመካፈልና አገልግሎቱን ሲያከናውን በቀጥታ ለመመልከት አጋጣሚ እንዳገኙ ያህል ሆኖ ተሰምቷቸዋል።” የመጽሐፉን ርዕስ የሚያጎላውን የመጀመሪያውን ስዕል አሳየው። ከዚያም መግቢያውን ገልጠህ “ስለ እሱ በመማር የሚገኝ ጥቅም” በሚለው ንዑስ ርዕስ ስር ያለውን ሁለተኛውን አንቀጽ አንብብ። ከዚያ መጽሐፉን እንዲወስድ ጋብዘው።
8 መጽሐፉን ወዳበረከትክለት ሰው ተመልሰህ በምትሄድበት ጊዜ እንዲህ ማለት ትችላለህ:-
◼ “ባለፈው ጊዜ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ያሳለፈው ሕይወት ምን እንደሚመስል ተወያይተን ነበር። እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የተባለውን መጽሐፍ በመውሰድዎ ደስ ብሎኛል። ከኢየሱስ ትምህርቶችና ካሳያቸው ባሕሪዎች መካከል በጣም የማረከዎት የትኛው ነው?” መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት። ምዕራፍ 113ን አውጣና ኢየሱስ ስላሳየው የላቀ የትሕትና ምሳሌ አወያየው። ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስ ላሳየው የትሕትና ባሕርይ ምን ዓይነት አመለካከት እንደነበረው ለመግለጽ ፊልጵስዩስ 2:8ን አንብብ። ከዚያም ቋሚ በሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት ምን ያህል እውቀት ማግኘት እንደሚቻል ግለጽለት።
9 የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምር ሐሳብ ማቅረብ፦ ለቤቱ ባለቤት ታላቅ ሰው የተባለውን መጽሐፍ ካበረከትንለት ወይም አስቀድሞ አንድ ቅጂ አግኝቶ ከነበረ ምዕራፍ 111ን በመጠቀም የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዴት እንደሚካሄድ ማሳየቱ ጥሩ ይሆናል። ጥናቱን የምትመራው እንዴት ይሆናል? ከአንድ ንዑስ ርዕስ ሥር ያለውን ሐሳብ (ወይም ምዕራፉን በሙሉ) ካነበብክ በኋላ በምዕራፉ መጨረሻ ላይ ካሉት ጥያቄዎች መካከል ከተነበበው አንቀጽ ጋር የሚዛመዱትን ጥያቄዎች ጠይቅ። መልሶቹ ሁልጊዜ በምዕራፉ ውስጥ በቅደም ተከተል እንደማይገኙ አስታውስ። ጥናቱ ከቀጠለ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ወደተባለው ብሮሹር ወይም ወደ እውቀት መጽሐፍ ማሻገር እንችላለን።
10 ቅን ልብ ያላቸው ሁሉም ዓይነት ሰዎች ስለ አምላክና ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን እውነት ለማግኘት ፍለጋ ላይ ናቸው። እነዚህን ሰዎች በምሥክርነቱ ሥራችን አማካኝነት ልንረዳቸው እንችላለን። እንግዲያውስ ‘መታገላችንንና በሥራ መድከማችንን’ እንቀጥል ‘ተስፋ የምናደርገው ሰዎችን ሁሉ በሚያድን በሕያው አምላክ ስለሆነ ጠንክረን መሥራታችንን እንቀጥል።’—1 ጢሞ. 4:10 የ1980 ትርጉም