ከአምላክ የሚገኘው እውቀት ለብዙ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል
1 ትክክለኛውን የእውነት እውቀት ከማግኘትህ በፊት መልስ ልታገኝላቸው ያልቻልካቸው ሕይወትን የሚመለከቱ ብዙ ጥያቄዎች እንደነበሩህ የታወቀ ነው። ለእነዚህ ጥያቄዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ መልሶች ስታገኝ ምንኛ በደስታ ፈንድቀህ ይሆን! አሁን አንተ ራስህ ሌሎች ሰዎች ተመሳሳይ መልሶች እንዲያገኙ ለመርዳት ትችላለህ። (ከ2 ጢሞቴዎስ 2:2 ጋር አወዳድር።) ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራውን ከአምላክ የሚገኝ እውቀት ልታካፍላቸው ትችላለህ። (ዮሐ. 17:3) ይሁን እንጂ አንድ ሰው የዚህን እውቀት ጥቅም እንዲገነዘብ እንዴት ልትረዳው ትችላለህ? እውነትን በማወቅህ መልስ ያገኘህላቸውን ጥያቄዎች እስቲ ቆም በልና አስብ። እውነት ፈላጊዎች ማወቅ የሚመኙት ምንድን ነው? እነዚህን ነጥቦች በአእምሮህ መያዝ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለውን መጽሐፍ ለማበርከት ሊረዳህ ይችላል። ሆኖም ዘወትር መጽሐፍ ቅዱስን ለመጠቀም ሞክር፤ አለዚያም ቢያንስ በጽሑፎቻችን ላይ የሚገኝ አንድ ጥቅስ አንብብ። በሰኔ ወር ለምታደርገው ምሥክርነት በምትዘጋጅበት ጊዜ ከዚህ በታች ያሉት ሐሳቦች ሊጠቅሙህ ይችላሉ።
2 በዓለም ውስጥ መከራና ሥቃይ የበዛበት ምክንያት ብዙ ሰዎችን ስለሚያሳስባቸው ይህ አቀራረብ ጥሩ ምላሽ ሊያስገኝ ይችል ይሆናል:-
◼ “ብዙውን ጊዜ ሰዎች የተፈጥሮ አደጋ ሲደርስ ወይም ወንጀልና ዓመፅ እየጨመረ መሄዱን ሲመለከቱ እንደነዚህ ያሉ አሠቃቂ ነገሮች የሚከሰቱት ለምን ይሆን ብለው ይጠይቃሉ። እርስዎ ለምን ይመስልዎታል?” መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለትና ለማለት የፈለገው ነገር እንደገባህ ግለጽ። ከዚያም ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 11 አውጣና አንቀጽ 2 ላይ በሰፈረው ሐሳብ ላይ እንዲያተኩር አድርግ። ይህ መጽሐፍ ክፉ ድርጊቶች ለምን እንደሚከሰቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማብራሪያ እንደሚሰጥ ግለጽና መጽሐፉን እንዲወስድ ጋብዘው።
3 “ለዘላለም መኖር” የተባለውን መጽሐፍ ያበረከትክላቸው ሰዎች ዘንድ ተመልሰህ በምትሄድበት ጊዜ እንዲህ ልትል ትችላለህ:-
◼ “በዓለም ውስጥ ይኼን ያህል ሥቃይ የኖረበትን ምክንያት በሚመለከት የደረሱበትን መደምደሚያ ባውቅ ደስ ይለኛል። በመጽሐፉ ውስጥ በተጠቀሰው የመጽሐፍ ቅዱስ መልስ ይስማማሉ?” መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት። ለዘላለም መኖር ከተባለው መጽሐፍ ገጽ 99 አንቀጽ 3ን አንብብና ጊዜ በፈቀደልህ መጠን በአንቀጽ 4-9 በሚገኙት ነጥቦች ላይ ሐሳብ ስጥ። ከዚያም እንዲህ በል:- “አምላክ ፍትህ በጎደለው መንገድ እንድንታመምና እንድንሰቃይ እንደማያደርግ ማወቅ ያስደስታል። እሱ ሰላምና ደስታ የሰፈነበት ዘላለማዊ ሕይወት እንደሚሰጠን ቃል ገብቷል። የዚህ መጽሐፍ የመጀመሪያው ርዕስ ‘ለዘላለም መኖር ሕልም አይደለም’ የሚል ነው። ይህ ለእርስዎም ሆነ ለሚያፈቅሯቸው ሰዎች እውነት ሊሆን የሚችለው እንዴት እንደሆነ ባብራራልዎ ደስ ይለኛል።” ምዕራፍ 1ን አውጣና ጥናቱ የሚመራው እንዴት እንደሆነ አሳይ። እንደሁኔታው ከምዕራፉ የቻልከውን ያክል ሸፍን።
4 “ማመራመር” በተባለው መጽሐፍ ገጽ 14 ላይ በሚገኘው “እርጅና/ሞት” በሚለው ርዕስ ሥር ያሉትን መግቢያዎች ለመጠቀም ትመርጥ ይሆናል:-
◼ “‘የሁሉም ነገሮች መጨረሻ ሞት ነው ወይስ ከዚያ በኋላ ሌላ ነገር ይኖር ይሆን’ የሚለውን ጥያቄ ራስዎን ጠይቀው ያውቃሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] መጽሐፍ ቅዱስ ሞትን በሚመለከት ለሚኖረን ማንኛውም ጥያቄ ማብራሪያ ይሰጠናል። [መክብብ 9:5, 10 አንብብ።] በተጨማሪም እምነት ላላቸው ሁሉ እውነተኛ ተስፋ እንዳለ ያሳያል። [ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 166 እና 168 አውጥተህ ዮሐንስ 11:25 ላይ የሚገኙትን የኢየሱስ ቃላት አንብብና አብራራ።] የምንወዳቸው በሞት የተለዩን ሰዎች ምን ይሆናሉ? ለሚለው ጥያቄ መላው ምዕራፍ አጥጋቢ መልስ ይሰጣል። ይህን መጽሐፍ ልተውልዎት እችላለሁ።”
5 ተመላልሶ መጠየቅ በምታደርግበት ጊዜ የወዳጅነት ሰላምታ ካቀረብክ በኋላ እንዲህ ልትል ትችላለህ:-
◼ “ባለፈው ጊዜ አንድ ሰው ሲሞት ምን እንደሚሆን ተነጋግረን ነበር። ብዙ ሰዎች ሰው ሲሞት ወደ ሰማይ ወይም ወደ ሲኦል ይሄዳል ብለው ያምናሉ። ከዚህ ቀደም ሙታን በዚሁ ምድር ላይ እንደገና ሕይወት አግኝተው የመኖር አጋጣሚ ይኖራቸዋል ብለው አስበው ያውቃሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] በመጽሐፍ ቅዱስ አባባል መሠረት በትንሣኤ የሚነሱት ሰዎች ምድርን ከሚወርሱት ቅኖች መካከል ይሆናሉ። [መዝሙር 37:11, 29 አንብብና ለዘላለም መኖር በተባለው መጽሐፍ ገጽ 12, 13 ላይ በሚገኘው ሥዕል አወያየው።] ይህ ተስፋ በሞት ፍርሃት ይኖሩ ለነበሩ በሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች መጽናኛ ሆኗል። ይህ መጽሐፍ ነገሩ በይበልጥ እንዲገባዎ ሊረዳዎት ይችላል። የሚረዳዎት እንዴት እንደሆነ ላሳይዎ?”
6 አስፈላጊ የሆኑ የሕይወት ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችል እውቀት ከአምላክ አግኝተናል። ትጋት የተሞላበት ዝግጅት አድርግ፤ ይህን ሕይወት ሰጪ የሆነ መልእክት እውነትን ለሚፈልጉ ሰዎች ለማካፈል የምታደርገውን ጥረት ይሖዋ ይባርክልሃል።