ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራውን እውቀት ማሠራጨት
1 ‘ለሰው እውቀትን የሚያስተምረው’ ይሖዋ ነው። (መዝ. 94:10) እርሱን ተቀባይነት ባለው መንገድ እንዴት ማገልገል እንደሚቻል ለማያውቁ ሰዎች ስለ እርሱ የሚገልጸውን ሕይወት አድን እውቀት ለማዳረስ በእኛ ይጠቀማል። ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት እና በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባሉት መጻሕፍት ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በጽሑፍ ከሠፈረው የአምላክ ቃል ማለትም ከመጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲያገኙ የሚረዱ ጥሩ የማስተማሪያ መሣሪያዎች ናቸው። (1 ጢሞ. 2:3, 4) ስለ እውነት የቀረበው ግልጽና ምክንያታዊ የሆነ ማብራሪያ ሰዎች ይሖዋ ሊያስተምራቸው የፈለገውን ነገር በቀላሉ እንዲጨብጡ ይረዳቸዋል። በዚህ ወር ሰዎች ከእነዚህ መጻሕፍት መካከል አንዱን እንዲያነቡ የሚያነሳሳ ውይይት ማድረግ እንፈልጋለን። ከዚህ ቀጥሎ አንዳንድ ሐሳቦች ቀርበዋል። እነዚህን መግቢያዎች በቃልህ ለመሸምደድ ከመሞከር ይልቅ ቁልፍ የሆኑትን ነጥቦች በራስህ አገላለጽ ለማስቀመጥ ከጣርክ ውይይቱ ይበልጥ ማራኪ ይሆናል።
2 አብዛኞቹ ሰዎች የሚወዱትን ሰው በሞት ያጡ በመሆናቸው እንደሚከተለው በማለት ስለ ትንሣኤ ተስፋ ውይይት መጀመር ትችላለህ:-
◼ “አብዛኞቻችን የምንወደውን ሰው በሞት አጥተናል። እነዚህን ሰዎች እንደገና አገኛቸው ይሆን? ብለው ጠይቀው ያውቃሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ሞት አምላክ በመጀመሪያ ለሰው ልጆች የነበረው ዓላማ ክፍል አይደለም። ኢየሱስ የምናፈቅራቸው ሰዎች ከሞት ሊዋጁ እንደሚችሉ አረጋግጧል። [ዮሐንስ 11:11, 25, 44ን አንብብ።] ይህ ነገር የተከናወነው ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት ቢሆንም አምላክ ወደፊት ምን ሊያደርግልን ቃል እንደገባ የሚያሳይ ነው። [ለዘላለም መኖር በተባለው መጽሐፍ ላይ በገጽ 162 ግርጌ የሚገኘውን ስዕል ካሳየኸው በኋላ በገጽ 166 ላይ ወደሚገኘው የምዕራፍ 20 ርዕስ ውሰደው። እውቀት በተባለው መጽሐፍ ደግሞ በገጽ 85 ላይ ያለውን ስዕል ከነመግለጫው ካሳየኸው በኋላ በገጽ 86 ላይ ወዳለው ስዕል ትወስደዋለህ።] ስለዚህ የሚያጽናና የትንሣኤ ተስፋ ይበልጥ ለማወቅ ከፈለጉ ይህን መጽሐፍ ብተውልዎት ደስ ይለኛል።”
3 ስለ ትንሣኤ ተስፋ ካደረጋችሁት የመጀመሪያ ውይይት በኋላ ከዚያው ሰው ጋር የሚቀጥለውን ውይይት በዚህ መንገድ ልትጀምር ትችላለህ:-
◼ “ሞት አምላክ በመጀመሪያ ለሰው ልጅ የነበረው ዓላማ ክፍል አይደለም እንዳልኩዎት ሳያስታውሱ አይቀሩም። ታዲያ ይህ ነገር እውነት ከሆነ የምናረጀውና የምንሞተው ለምንድን ነው? አንዳንድ ኤሊዎች ከ100 ዓመት በላይ ሲኖሩ በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት የኖሩ ዛፎችም አሉ። ታዲያ ሰዎች 70 ወይም 80 ዓመት ብቻ የሚኖሩት ለምንድን ነው? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] እኛ የምንሞተው የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት አምላክን ሳይታዘዙ በመቅረታቸው ነው።” ሮሜ 5:12ን አንብብ። ለዘላለም መኖር በተባለው መጽሐፍ ገጽ 10 እና ገጽ 74 የሚገኙትን ንዑስ ርዕሶች ወይም እውቀት በተባለው መጽሐፍ ገጽ 53 የሚገኘውን ርዕስ አንብብለት። የቀረቡትን ጥያቄዎች መልስ እንዲያተኩርባቸው በማድረግ በሁለት ወይም ሦስት አንቀጾች ላይ ተወያዩ። በቀረው የምዕራፉ ክፍል ላይ ለመወያየት ሌላ ጊዜ ተመልሰህ የምትሄድበትን ቀጠሮ ያዝ። እስከዚያ ድረስ በግሉ ምዕራፉን አንብቦ እንዲጨርስ አበረታታው።
4 ሃይማኖተኛ ከሚመስል ሰው ጋር ስትነጋገር እንዲህ ልትል ትችላለህ:-
◼ “በዛሬው ጊዜ በጣም ብዙ ሃይማኖቶች አሉ። አንዱ ከሌላው ጋር የሚቃረኑ ብዙ ትምህርቶችን ያስተምራሉ። አንዳንድ ሰዎች ሁሉም ሃይማኖቶች ጥሩ ስለሆኑ በየትኛውም ሃይማኖት ብናምን ምንም ለውጥ አያመጣም ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ሁሉም ሰው መከተል የሚኖርበት በአካባቢው የሚገኘውን ጥንታዊና ባሕላዊ ሃይማኖት ነው ይላሉ። እርስዎስ ምን ይላሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ኢየሱስ እውነተኛውን ሃይማኖት ካስተማረ በኋላ ሌላ ዓይነት አምልኮዎች በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንደሌላቸው ገልጿል። [ማቴዎስ 7:21-23ን አንብብ።] አምላክን ለማስደሰት ከፈለግን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ መንገድ ልናመልከው ይገባል።” ለዘላለም መኖር በተባለው መጽሐፍ ገጽ 25 ወይም እውቀት በተባለው መጽሐፍ ገጽ 43 ላይ የሚገኘውን 5ኛ ምዕራፍ ገልጠህ ርዕሱን ካነበብህለት በኋላ አንዳንዶቹን ንዑስ ርዕሶች ጠቁመው። በምዕራፉ ውስጥ ያለው ሐሳብ አንድ ሰው አምላክን እንዴት ማስደሰት እንደሚችል እንዲማር የሚረዳ መሆኑን ግለጽለት። መጽሐፉን እንዲወስድ ጋብዘው።
5 ሃይማኖቶች በጣም በመብዛታቸው ምክንያት ግራ የተጋቡ ሰዎች በተመላልሶ መጠየቅ ወቅት ለሚከተለው ጥያቄ የምትሰጣቸው መልስ ሳያስደስታቸው አይቀርም:-
◼ “ዛሬ ካሉት ከእነዚህ ሁሉ ሃይማኖቶች መካከል ትክክለኛው የቱ እንደሆነ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? እርስዎ ከእውነተኛ ሃይማኖት ምን ይጠብቃሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ኢየሱስ የእርሱን እውነተኛ ተከታዮች እንዴት ለይተን ማወቅ እንደምንችል ነግሮናል።” ዮሐንስ 13:35ን አንብብ። ለዘላለም መኖር በተባለው መጽሐፍ ገጽ 184 ላይ የሚገኘውን የምዕራፍ 22 ርዕስ ከተመለከታችሁ በኋላ በገጽ 189 ላይ በሚገኙት አንቀጽ 16 እና 17 ላይ ተወያዩ። (እውቀት በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 5 አንቀጽ 18 እና 19 ላይ ይገኛል።) አንድ ሰው ልዩ ልዩ ሃይማኖቶችን በአእምሮው ይዞ በእነዚህ ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች መሠረት በመገምገም እውነተኛውን ሃይማኖት ለይቶ ማወቅ እንደሚችል ጠቁመው። የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ ባላቸው እውነተኛ ፍቅርና ከፍተኛ የሥነ ምግባር አቋም እንደሚታወቁ ንገረው። በዚህ መጽሐፍ አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን አምልኮ ለይቶ ለማወቅ የሚረዳው እንዴት እንደሆነ ግለጽለት።
6 ወላጅ ካገኘህ የሚከተለውን አቀራረብ ውጤታማ ሆኖ ታገኘው ይሆናል:-
◼ “ባለጌ ወጣቶች ስለሚያሳዩት ያልታረመ ጠባይ በየዕለቱ እንሰማለን። አንዳንድ አዋቂዎች ትምህርት ቤቶች ትክክልና ስህተት በሆነው ነገር መካከል ያለውን ልዩነት ለልጆች አላስተማሩም ብለው ያማርራሉ። እርስዎ ይህን ሥልጠና መስጠት ያለበት ማን ነው ይላሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠውን መልስ ልብ ይበሉ። [ኤፌሶን 6:4ን አንብብ።] ይህም በልጆች ውስጥ ጥሩ ሥነ ምግባር የመትከሉ ኃላፊነት የወላጆች ነው ማለት ነው።” ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 248ን ገልጠህ አንቀጽ 30ን አንብብ። ከዚያም በገጽ 245 ላይ በሚገኙት ስዕሎች እንዲሁም በአንቀጽ 20 እና 21 ላይ ሐሳብ ስጥ። (እውቀት በተባለው መጽሐፍ ደግሞ ገጽ 145-147 አንቀጽ 16-18 ላይ ይገኛል።) ይህን የመሰለውን ጥናት ከቤተሰቦች ጋር እንዴት እንደምናደርግ ልታሳየው እንደምትፈልግ ግለጽለት።
7 በመጀመሪያው ጉብኝትህ ላይ በአሁኑ ጊዜ ያሉት ሁኔታዎች ከሚያስጨንቁት ወላጅ ጋር ጥናት ጀምረህ ከነበረ በተመላልሶ መጠየቅ ወቅት እንደሚከተለው በማለት መቀጠል ትችል ይሆናል:-
◼ “ዛሬ ባለንበት ዓለም ውስጥ በወጣቶቻችን ፊት ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎች ተደቅነዋል። ይህም እያደጉ ሲሄዱ አምላክን የሚፈሩ እንዳይሆኑ እንቅፋት ይፈጥርባቸዋል። ባለፈው ጊዜ ስንወያይ ሁለት መሠረታዊ ሥርዓቶችን አንስተን እንደነበር ያስታውሱ ይሆናል። አምላካዊ አክብሮት ያለን ወላጆች በመሆን ለልጆቻችን መልካም ምሳሌ መሆን ያስፈልገናል፤ እንዲሁም ዘወትር ለእነርሱ ያለንን ፍቅር መግለጽ ይኖርብናል። ልጆች ከወላጆች የሚፈልጉት ሌላም ነገር እንዳለ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።” ምሳሌ 1:8ን አንብብ። ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 246 ገልጠህ (ወይም እውቀት በተባለው መጽሐፍ ገጽ 148) ከ22-26 ባሉት (ወይም እውቀት በተባለው መጽሐፍ ከ19-23) አንቀጾች ጥናቱን ቀጥል። ከመላው ቤተሰብ ጋር ከምዕራፍ 1 ጀምሮ ለማጥናት ተመልሰህ መምጣት እንደምትፈልግ ግለጽለት።