በቅርብ አስቀምጡት
ለመስክ አገልግሎት የሚሆኑ መግቢያዎች
aበወሩ ውስጥ የሚበረከተውን ጽሑፍ ለማስተዋወቅ የሚያስችሉህን መግቢያዎች ስትዘጋጅ በሚከተሉት አቀራረቦች ተጠቀም።
ወደ ይሖዋ ቅረብ
“በአምላክ የሚያምኑ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ መቅረብ ይፈልጋሉ። አምላክ ራሱ ወደ እርሱ እንድንቀርብ እንደጋበዘን ያውቃሉ? [ያዕቆብ 4:8ን አንብብ።] ይህ መጽሐፍ ሰዎች በራሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ በመጠቀም ወደ አምላክ እንዲቀርቡ ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ ነው።” ከገጽ 16 ላይ አንቀጽ 1ን አንብብ።
“በጊዜያችን የፍትሕ መጓደል በብዙ ቦታዎች ይታያል። መጽሐፍ ቅዱስም ስለዚህ ሁኔታ ይናገራል። [መክብብ 8:9 ሁለተኛውን ዓረፍተ ነገር አንብብ።] እንዲያውም አንዳንዶች አምላክ ለሰው ልጆች ጨርሶ ደንታ ያለው አይመስላቸውም። [ከገጽ 119 አንቀጽ 4 ላይ የመጀመሪያዎቹን ሁለት ዓረፍተ ነገሮች አንብብ።] ይህ ምዕራፍ አምላክ ለተወሰነ ጊዜ የፍትሕ መጓደል እንዲቀጥል የፈቀደበትን ምክንያት ያብራራል።”
ነቅተህ ጠብቅ!
“ብዙ ሰዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ የመጡትን አሳሳቢ ችግሮችና አስደንጋጭ የሆኑ ክስተቶች ሲመለከቱ በጣም ያሳስባቸዋል። [በአካባቢያችሁ በስፋት የሚታወቅ አንድ ምሳሌ ጥቀስ።] እነዚህ ነገሮች የአምላክ መንግሥት በምድር ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ በመግባት እርምጃ የምትወስድበት ጊዜ መቅረቡን የሚያሳየው ዓለም አቀፋዊ ምልክት ክፍል እንደሆኑ ያውቃሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት። ከዚያም እንደ ማቴዎስ 24:3, 7, 8፤ ሉቃስ 21:7, 10, 11 ወይም 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5 ያሉትን ተስማሚ ጥቅሶች አንብብ።] ይህ ብሮሹር እነዚህ ሁኔታዎች ላላቸው ትርጉም ትኩረት መስጠታችን በጣም አጣዳፊ የሆነው ለምን እንደሆነ ያብራራል።”
“በዛሬው ጊዜ ብዙዎች በራሳቸውም ሆነ በሌሎች ላይ በሚደርሱት አሳዛኝና አስደንጋጭ ሁኔታዎች በጣም ይጨነቃሉ። አንዳንዶች አምላክ እነዚህን ነገሮች ለማስወገድ ለምን ጣልቃ አይገባም ብለው ይጠይቃሉ። ይሁንና አምላክ በቅርቡ የሰው ልጆችን ሰቆቃ ለማስወገድ እርምጃ እንደሚወስድ መጽሐፍ ቅዱስ ዋስትና ይሰጠናል። [ራእይ 14:6, 7ን አንብብ።] አምላክ የሚወስደው የፍርድ እርምጃ ለሰው ልጆች ምን እንደሚያመጣ እዚህ ላይ ይመልከቱ። [2 ጴጥሮስ 3:10, 13ን አንብብ።] በዚህ ጉዳይ ላይ ይህ ብሮሹር ሰፊ ማብራሪያ ይዟል።”
ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት
በገጽ 4ና 5 ላይ የሚገኘውን ሥዕል አሳየውና እንዲህ በል:- “ይህን በመሰለ የሚያምር ሥፍራ እንዲኖሩ ግብዣ ቢቀርብልዎት ምን ምላሽ ይሰጣሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ለዘላለም ለመኖር የሚያስፈልገውን ብቃት በሚመለከት መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ሐሳብ እዚህ ላይ ይመልከቱ። [ዮሐንስ 17:3ን አንብብ።] ይህ መጽሐፍ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራውን እውቀት እንዲያገኙ ይረዳዎታል።” በሚቀጥለው ቀጠሯችሁ ከምዕራፍ 1 ላይ በመጀመሪያዎቹ 5 አንቀጾች ላይ እንደምትወያዩ ንገረው።
በገጽ 188ና 189 ላይ የሚገኘውን ሥዕል አሳየውና በሥዕሉ መግለጫ ላይ ያለውን ሐሳብ በመጠቀም ለምታነጋግረው ሰው የሚከተለውን ጥያቄ አቅርብለት:- “ምድር አምላክ በሚሰጠው እውቀት ስትሞላ በገነት ውስጥ ለመኖር ተስፋ ያደርጋሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት። ከዚያም ኢሳይያስ 11:9ን አንብብ።] ይህ መጽሐፍ ስለ ገነትና በዚያ ለመኖር ምን ማድረግ እንዳለብን ስለሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ለማወቅ ይረዳዎታል።” በሚቀጥለው ቀጠሯችሁ ከምዕራፍ 1 ላይ ከ11-16 ባሉት አንቀጾች ላይ እንደምትወያዩ ንገረው።
ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል!
“ስለዚህ [አንድ የዜና ርዕስ ጥቀስለት] አሳዛኝ ዜና ሳይሰሙ አይቀሩም። የሰዎች ሕይወት በአሳዛኝ ሁኔታ ሲጠፋ ሲመለከቱ ብዙዎች የሟቾቹን ቤተሰብ እንዴት ማጽናናት እንደሚቻል ግራ ይገባቸዋል። እርስዎ ስለዚህ ጉዳይ ምን አመለካከት አለዎት?” መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት። ከዚያም ገጽ 299ን ግለጥና ስለ ትንሣኤ የሚያሳየውን ሥዕል አሳያቸው። ከዚያም እንዲህ በማለት ቀጥል:- “ብዙዎች ወደፊት ጻድቃንም ሆኑ ኃጢአተኞች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለመኖር ትንሣኤ እንደሚያገኙ ሲያውቁ ይገረማሉ። [በገጽ 297 አንቀጽ 9 ላይ የተጠቀሰውን የሐዋርያት ሥራ 24:15ን አንብብለት። ከዚያም በአንቀጽ 10 ላይ የሚገኘውን ማብራሪያ ተናገር።] ይህ መጽሐፍ አምላክ ወደፊት ለመፈጸም ቃል የገባቸውን የተለያዩ ተስፋዎች ይዟል።” መጽሐፍ ቅዱስ—የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው?
“በምንኖርበት ጊዜ ሁሉም ሰው ለማለት ይቻላል ከባድ የሆኑ ችግሮች ያጋጥሙታል። ብዙዎች መመሪያ ለማግኘት ወደተለያዩ አማካሪዎች ዞር ይላሉ። አንዳንዶች ደግሞ ከሰው በላይ የሆነ የማወቅ ችሎታ እንዳላቸው የሚናገሩ ባለሞያዎችን ያማክራሉ። እርስዎስ ለችግራችን መፍትሔ ሊያስገኝ የሚችል አስተማማኝ ምክር ከየት የምናገኝ ይመስልዎታል? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] መጽሐፍ ቅዱስ ሁላችንም ልንገነዘበው የሚገባ አንድ ሐቅ ይዟል። [2 ጢሞቴዎስ 3:16ን አንብብ። ከዚያም ከመጽሐፉ ላይ ገጽ 187ን ግለጥና አንቀጽ 9ን አንብብ።] ይህ መጽሐፍ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ምክር መከተል ምንጊዜም የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኝልን እንዲገነዘቡ ይረዳዎታል።”
እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
“በገና በዓል ሰሞን ብዙዎች ስለ ኢየሱስ ያስባሉ። ይሁን እንጂ በዓለማችን ላይ ብዙ መጥፎ ነገሮች እየተፈጸሙ ስለሆነ አንዳንዶች ኢየሱስ ስለ እኛ በእርግጥ የሚያስብ አይመስላቸውም። እርስዎ ምን ይሰማዎታል?” መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት። ከዚያም ምዕራፍ 24ን ግለጥና ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበትን ዓላማ በአጭሩ ተናገር። ከዚያም ዮሐንስ 15:13ን አንብብና ኢየሱስ ለሌሎች ያለውን ከልብ የመነጨ ፍቅር አብራራ።
“ስለ ኢየሱስ ሲነሳ ብዙ ሰዎች ወደ አእምሯቸው የሚመጣላቸው አንድ ሕፃን ልጅ ወይም ተሰቅሎ በማጣጣር ላይ ያለ ሰው ነው። ስለ ኢየሱስ ያላቸው ግንዛቤ በልደቱና በሞቱ ላይ ብቻ ያተኮረ ነው። ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት የተናገራቸውና ያደረጋቸው ድንቅ ነገሮች ብዙም ትኩረት አይሰጣቸውም። ኢየሱስ ያደረገው ነገር በምድር ላይ የኖረውን የእያንዳንዱን ሰው ሕይወት ይነካል። ኢየሱስ ለእኛ ሲል ስላከናወናቸው ድንቅ ነገሮች የቻልነውን ያህል ማወቃችን የግድ አስፈላጊ የሆነው በዚህ ምክንያት ነው።” ዮሐንስ 17:3ን አንብብ። የመጽሐፉን መግቢያ ግለጥና አራተኛውን አንቀጽ አንብብ።
አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው?
“በጊዜያችን የሚያጋጥሙን ዓይነት ችግሮች በሞሉበት አካባቢ እንድንኖር የአምላክ ዓላማ ይመስልዎታል? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት። ከዚያም ማቴዎስ 6:10ን አንብብ።] የአምላክ መንግሥት በእርግጥ ምንድን ነው? ብለው አስበው ያውቃሉ?” ትምህርት 6ን አውጣና በትምህርቱ መጀመሪያ ላይ የሰፈሩትን ጥያቄዎች አንብብ። ከዚያም ከአንቀጽ 1 አንስቶ መወያየት ጀምሩ፤ ወይም በሚቀጥለው ጉብኝት ለመወያየት ቀጠሮ ያዝ።
“ዘመናዊው ኅብረተሰብ በቴክኖሎጂ እየተራቀቀ ቢሄድም በሽታና ሞት በሰው ልጆች ላይ መከራና ሐዘን ማስከተላቸው አልቀረም። ኢየሱስ ወደፊት ለሕሙማን፣ ለአረጋውያን አልፎ ተርፎም ለሞቱ ሰዎች ምን እንዳዘጋጀላቸው ያውቃሉ?” መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት። ግለሰቡ ለጥያቄው መልስ ለማግኘት ፈቃደኛ ከሆነ ትምህርት 5ን ግለጥና ለአንቀጽ 5ና 6 የቀረቡትን ጥያቄዎች አንብብ። ከዚያም በአንቀጾቹ ላይ ተወያዩ፤ ወይም በሚቀጥለው ጉብኝት ለመወያየት ቀጠሮ ያዝ።