የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ እንዴት ማበርከት ይቻላል?
ይህ አባሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ለማበርከት የሚረዱ የተለያዩ መግቢያዎችን ይዟል። መግቢያዎቹን በራስህ አባባል ከተናገርካቸው፣ አቀራረብህን በክልልህ ውስጥ እንደሚገኙት ሰዎች ሁኔታ ከለዋወጥክና መጽሐፉን አንብበህ ጥሩ የመወያያ ርዕስ ሊሆኑ የሚችሉ ነጥቦችን ካወጣህ ይበልጥ ውጤታማ ልትሆን ትችላለህ። ለአገልግሎት ክልልህ ተስማሚ የሆኑ ሌሎች አቀራረቦችንም መጠቀም ትችላለህ።—ጥር 2005 የመንግሥት አገልግሎታችን ገጽ 6ን ተመልከት።
አርማጌዶን
◼ “ብዙ ሰዎች ‘አርማጌዶን’ የሚለውን ቃል ሲሰሙ ጅምላ ጨራሽ የሆነ ጥፋት ወደ አእምሯቸው ይመጣል። ይሁንና አርማጌዶን በጉጉት ልንጠብቀው የሚገባ ነገር እንደሆነ ቢያውቁ ምን ይሰማዎታል? [መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው። ከዚያም ራእይ 16:14, 16ን አንብብ።] ከአርማጌዶን በኋላ የሰው ልጆች የሚመሩትን ሕይወት በተመለከተ እዚህ ላይ የሰፈረውን ሐሳብ ይመልከቱ።” ገጽ 82-84 አውጥተህ አንቀጽ 21ን አንብብ።
መጽሐፍ ቅዱስ
◼ “ብዙውን ጊዜ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል እንደሆነ ሲናገሩ እንሰማለን። በሰዎች የተጻፈ መጽሐፍ ሆኖ ሳለ የአምላክ ቃል ተብሎ ሊጠራ የቻለው እንዴት ነው ብለው ጠይቀው ያውቃሉ? [መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው። ከዚያም 2 ጴጥሮስ 1:21ን እንዲሁም ገጽ 19ና 20 ላይ የሚገኘውን አንቀጽ 5ን አንብብ።] ይህ ጽሑፍ ለእነዚህ ጥያቄዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ መልሶችን ይሰጣል።” ገጽ 6 ላይ ያሉትን ጥያቄዎች አሳየው።
◼ “በዛሬው ጊዜ ሰዎች ከዚህ ቀደም ታይቶ የማያውቅ ብዙ መረጃ ማግኘት ይችላሉ። ይሁን እንጂ ደስተኛና ስኬታማ ሕይወት ለመምራት የሚያስችል አስተማማኝ ምክር ከየት የሚገኝ ይመስልዎታል? [መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው። ከዚያም 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17ን እንዲሁም ገጽ 23 አንቀጽ 12ን አንብብ።] ይህ ጽሑፍ አምላክን በሚያስደስትና እኛን በሚጠቅም መንገድ ሕይወታችንን እንዴት መምራት እንደምንችል ያብራራል።” ገጽ 122 እና 123 ላይ የሚገኘውን ሣጥንና ፎቶግራፍ አሳየው።
ሞት/ትንሣኤ
◼ “ብዙዎች ‘ሰው ሲሞት ምን ይሆናል?’ በማለት ይጠይቃሉ። የዚህን ጥያቄ መልስ ማወቅ እንደምንችል ይሰማዎታል? [መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው። ከዚያም መክብብ 9:5ን እንዲሁም ገጽ 58-59 ላይ የሚገኙትን አንቀጽ 5ና 6ን አንብብ።] በተጨማሪም ይህ ጽሑፍ መጽሐፍ ቅዱስ ለሞቱ ሰዎች የሚሰጠውን የትንሣኤ ተስፋ ያብራራል።” ገጽ 75 ላይ የሚገኘውን ሥዕል አሳየው።
◼ “አንድ የምንወደው ሰው ሲሞትብን ያንን ሰው ዳግመኛ ለማየት እንደምንናፍቅ የታወቀ ነው። በዚህ አይስማሙም? [መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው።] ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጠው የትንሣኤ ተስፋ መጽናኛ አግኝተዋል። [ዮሐንስ 5:28, 29ን እንዲሁም ገጽ 72 አንቀጽ 16ና 17ን አንብብ።] ይህ ምዕራፍ ለእነዚህ ጥያቄዎችም መልስ ይሰጣል?” ገጽ 66 ላይ የሚገኙትን የመግቢያ ጥያቄዎች አሳየው።
የዘላለም ሕይወት
◼ “አብዛኛው ሰው ጥሩ ጤንነትና ረጅም ዕድሜ ቢኖረው ደስ ይለዋል። ይሁን እንጂ ቢችሉ ኖሮ ለዘላለም መኖር ይፈልጋሉ? [መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው። ከዚያም ራእይ 21:3, 4ን እንዲሁም ገጽ 54 አንቀጽ 17ን አንብብ።] ይህ መጽሐፍ የዘላለም ሕይወት ማግኘት የምንችለው እንዴት እንደሆነ የሚያስረዳ ከመሆኑም በላይ ተስፋው ከተፈጸመ በኋላ ምን ዓይነት ሕይወት እንደምንመራም ያብራራል።”
ቤተሰብ
◼ “ሁላችንም አስደሳች የቤተሰብ ሕይወት እንዲኖረን እንፈልጋለን ቢባል አይስማሙም? [መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው።] እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ፍቅር በማሳየት ረገድ የአምላክን ምሳሌ በመኮረጅ ለቤተሰቡ ደስታ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚችል መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።” ኤፌሶን 5:1, 2ን እንዲሁም ገጽ 135 አንቀጽ 4ን አንብብ።
መኖሪያ ቤት
◼ “በብዙ ቦታዎች እንደየሰዉ የአቅም መጠን ተስማሚ መኖሪያ ቤት ማግኘት በጣም አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል። ሁሉም ሰው ተስማሚ መኖሪያ ቤት የሚኖረው ጊዜ ይመጣል ብለው ያስባሉ? [መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው። ከዚያም ኢሳይያስ 65:21, 22ን እንዲሁም ገጽ 34 አንቀጽ 20ን አንብብ።] ይህ ጽሑፍ አምላክ የሰጠው ይህ ተስፋ ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።”
ይሖዋ አምላክ
◼ “በአምላክ የሚያምኑ ብዙ ሰዎች ይበልጥ ወደ እርሱ መቅረብ ይፈልጋሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ወደ አምላክ እንድንቀርብ የሚጋብዘን መሆኑን ያውቃሉ? [መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው። ከዚያም ያዕቆብ 4:8ሀን እንዲሁም ገጽ 16 አንቀጽ 20ን አንብብ።] ይህ ጽሑፍ ሰዎች የራሳቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅመው ስለ አምላክ ይበልጥ እንዲያውቁ ለመርዳት የተዘጋጀ ነው።” በገጽ 8 ላይ የሚገኙትን የመግቢያ ጥያቄዎች አሳየው።
◼ “ብዙ ሰዎች የአምላክ ስም እንዲቀደስ ይጸልያሉ። የአምላክ ስም ማን እንደሆነ ጠይቀው ያውቃሉ? [መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው። ከዚያም ዘፀአት 6:3ን እንዲሁም ገጽ 195 አንቀጽ 2ና 3ን አንብብ።] ይህ ጽሑፍ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ አምላክና እርሱ ለሰው ልጆች ስላለው ዓላማ ምን እንደሚያስተምር ያብራራል።”
ኢየሱስ ክርስቶስ
◼ “በምድር ዙሪያ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የማያውቅ ሰው የለም ለማለት ይቻላል። አንዳንዶች ታዋቂነትን ካተረፉ ሰዎች መካከል አንዱ እንደሆነ አድርገው ሲመለከቱት ሌሎች ደግሞ ሁሉን የሚችል አምላክ ነው ብለው ያመልኩታል። ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚኖረን እውቀት ለውጥ ያመጣል ብለው ያስባሉ?” መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው። ከዚያም ዮሐንስ 17:3ን እንዲሁም ገጽ 37ና 38 ላይ የሚገኘውን አንቀጽ 3ን አንብብ። ከምዕራፉ ሥር ባሉት የመግቢያ ጥያቄዎች ላይ እንዲያተኩር አድርግ።
ጸሎት
◼ “አምላክ የሰው ልጆች ለሚያቀርቡት ጸሎት መልስ የሚሰጠው በምን መንገድ እንደሆነ ጠይቀው ያውቃሉ? [መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው። ከዚያም 1 ዮሐንስ 5:14, 15ን እንዲሁም ገጽ 170-171 አንቀጽ 16-18ን አንብብ።] በተጨማሪም ይህ ምዕራፍ ወደ አምላክ መጸለይ ያለብን ለምን እንደሆነና ጸሎታችንንም እንዲሰማን ምን ማድረግ እንደሚኖርብን ያብራራል።”
ሃይማኖት
◼ “ብዙ ሰዎች በዓለም ላይ የሚገኙ ሃይማኖቶች ለሰው ዘር ችግሮች መፍትሔ የሚያመጡ ሳይሆኑ የችግሮቹ መንስኤ እንደሆኑ አድርገው መመልከት ጀምረዋል። ሃይማኖት የሰው ልጆችን በትክክለኛው መንገድ እየመራቸው እንዳለ ይሰማዎታል? [መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው። ከዚያም ማቴዎስ 7:13, 14ን እንዲሁም ገጽ 146 አንቀጽ 5ን አንብብ።] ይህ ምዕራፍ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን አምልኮ ለመለየት የሚረዱ ስድስት ገጽታዎችን ይመረምራል።” ገጽ 147 ላይ የሚገኘውን ዝርዝር አሳየው።
አሳዛኝ ችግር/ሥቃይ
◼ “አንድ ዓይነት አሳዛኝ ሁኔታ ሲከሰት ብዙዎች ‘አምላክ ለሰው ልጆች በእርግጥ ያስባል? ሥቃያቸውንስ ይመለከታል?’ ብለው ይጠይቃሉ። እርስዎስ እንዲህ ብለው አስበው ያውቃሉ? [መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው። ከዚያም 1 ጴጥሮስ 5:7ን እንዲሁም ገጽ 11 አንቀጽ 11ን አንብብ።] ይህ ጽሑፍ አምላክ የሰው ልጆችን ሥቃይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዴት ጠራርጎ እንደሚያጠፋ ያብራራል።” በገጽ 106 ላይ የሚገኙትን የመግቢያ ጥያቄዎች አሳየው።
ጦርነት/ሰላም
◼ “በሁሉም አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ሰላም ለማግኘት ይናፍቃሉ። በምድር ላይ ሰላም የማስፈኑ ተስፋ ሕልም እንደሆነ ይሰማዎታል? [መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው። ከዚያም መዝሙር 46:8, 9ን አንብብ።] ይህ ጽሑፍ አምላክ ዓላማውን ወደ ፍጻሜ በማድረስ ዓለም አቀፋዊ ሰላም የሚያመጣው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።” ገጽ 35 ላይ ያለውን ሥዕል አሳየው። ከዚያም በገጽ 34 አንቀጽ 17-21 ላይ ተመርኩዘህ አወያየው።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የገንዘብ መዋጮ እንዲያደርጉ መጋበዝ የሚቻልባቸው መንገዶች
“በዓለም ዙሪያ የምናከናወነውን ሥራ በገንዘብ ለመደገፍ አነስተኛ መዋጮ ማድረግ የሚፈልጉ ከሆነ በደስታ እቀበልዎታለሁ።”
“ለጽሑፎቻችን ክፍያ ባንጠይቅም እንኳ ሰዎች በዓለም ዙሪያ የምናከናውነውን ሥራ ለመደገፍ የሚሰጡትን መጠነኛ መዋጮ በደስታ እንቀበላለን።”
“ይህን ሥራ ለማከናወን የሚያስፈልገውን ገንዘብ የሚያገኙት ከየት ነው ብለው ይጠይቁ ይሆናል። በዓለም ዙሪያ የምናከናውነው ሥራ በፈቃደኝነት በሚደረጉ መዋጮዎች የሚደገፍ ነው። አቅምዎ የፈቀደውን ያህል መዋጮ ማድረግ የሚፈልጉ ከሆነ ልቀበልዎት ፈቃደኛ ነኝ።”