ጥያቄ በመጠየቅ፣ ጥቅስ በማንበብና አንድ ምዕራፍ አውጥቶ በማሳየት ጥናት ማስጀመር
ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ለማበርከት ቀላሉ መንገድ (1) የአመለካከት ጥያቄ መጠየቅ፣ (2) ተስማሚ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ማንበብና (3) ስለምትወያዩበት ጉዳይ የሚናገር ምዕራፍ ከመጽሐፉ ላይ አውጥቶ ከርዕሱ በታች ያሉትን የመግቢያ ጥያቄዎች ማንበብ ናቸው። የቤቱ ባለቤት ፍላጎት ካለው ያሳየኸውን ምዕራፍ የመጀመሪያ አንቀጾች በመጠቀም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዴት እንደሚካሄድ ማሳየት ትችል ይሆናል። በመጀመሪያው ውይይት አሊያም በተመላልሶ መጠየቅ ወቅት ጥናት ለማስጀመር ይህን ዘዴ መጠቀም ይቻላል።
◼ “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዚህ ጥቅስ ላይ እንደተገለጸው ደካማ የሆኑት የሰው ልጆች ሁሉን ቻይ የሆነውን ፈጣሪያችንን ለማወቅ የሚችሉ ይመስልዎታል?” የሐዋርያት ሥራ 17:26, 27ን አንብብና መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው። ከዚያም ምዕራፍ 1ን አሳየው።
◼ “በዛሬው ጊዜ ችግር ቢያጋጥመንም እንኳ እዚህ ላይ እንደተገለጸው መጽናኛና ተስፋ ማግኘት የሚቻል ይመስልዎታል?” ሮሜ 15:4ን አንብብና መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው። ከዚያም ምዕራፍ 2ን አሳየው።
◼ “እነዚህን ነገሮች ለማድረግ ኃይል ቢኖርዎት ኖሮ ይህን የመሰለ ለውጥ ያመጡ ነበር?” ራእይ 21:4ን አንብብና መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው። ከዚያም ምዕራፍ 3ን አሳየው።
◼ “ልጆቻችን በዚህ ጥንታዊ መዝሙር ላይ በተገለጸው ዓይነት ሁኔታ ተደስተው መኖር የሚችሉበት ጊዜ የሚመጣ ይመስልዎታል?” መዝሙር 37:10, 11ን አንብብና መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው። ከዚያም ምዕራፍ 3ን አሳየው።
◼ “እነዚህ ቃላት የሚፈጸሙበት ጊዜ ይመጣል ብለው አስበው ያውቃሉ?” ኢሳይያስ 33:24ን አንብብና መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው። ከዚያም ምዕራፍ 3ን አሳየው።
◼ “የሞቱ ሰዎች በሕይወት ያሉ ሰዎች የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች ያውቁ ይሆን ብለው አስበው ያውቃሉ?” መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው። ከዚያም መክብብ 9:5ን አንብብና ምዕራፍ 6ን አሳየው።
◼ “ኢየሱስ እዚህ ጥቅስ ላይ እንደተናገረው በሞት የተለዩንን የምንወዳቸውን ሰዎች እንደገና ማየት የምንችል ይመስልዎታል?” ዮሐንስ 5:28, 29ን አንብብና መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው። ከዚያም ምዕራፍ 7ን አሳየው።
◼ “በዚህ የታወቀ ጸሎት ላይ እንደተገለጸው የአምላክ ፈቃድ በሰማይ እንደሆነ ሁሉ በምድርም የሚሆነው እንዴት ይመስልዎታል?” ማቴዎስ 6:9, 10ን አንብብና መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው። ከዚያም ምዕራፍ 8ን አሳየው።
◼ “ዛሬ የምንኖረው በዚህ ትንቢት ላይ በተገለጸው ዘመን ውስጥ ይመስልዎታል?” ሁለተኛ ጢሞቴዎስ 3:1-4ን አንብብና መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው። ከዚያም ምዕራፍ 9ን አሳየው።
◼ “ብዙ ሰዎች፣ የሰው ልጅ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሱ የሄዱት ለምን እንደሆነ ይጠይቃሉ። በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ የሚገኘው ሐሳብ ለዚህ ሁኔታ ምክንያት እንደሆነ አስበው ያውቃሉ?” ራእይ 12:9ን አንብብና መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው። ከዚያም ምዕራፍ 10ን አሳየው።
◼ “እንደዚህ ዓይነት ጥያቄ ጠይቀው ያውቃሉ?” ኢዮብ 21:7ን አንብብና መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው። ከዚያም ምዕራፍ 11ን አሳየው።
◼ “ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በሥራ ላይ ማዋል ሰዎች የቤተሰብ ሕይወታቸው አስደሳች እንዲሆን የሚረዳቸው ይመስልዎታል?” ኤፌሶን 5:33ን አንብብና መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው። ከዚያም ምዕራፍ 14ን አሳየው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዴት እንደሚካሄድ ካሳየኸው በኋላ ሁለት ጊዜ ካጠናችሁና ጥናቱ እንደሚቀጥል ለማመን የሚያበቃ ምክንያት ካለህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ብለህ ሪፖርት ማድረግ ትችላለህ።