በዚህ የአገልግሎት ዓመት ምን ለማከናወን አስበናል?
1 የ1994 የአገልግሎት ዓመት መስከረም 1 ላይ ይጀምራል። ስለዚህ የይሖዋ ሕዝቦች ለሆንን ሁሉ በግለሰብም ሆነ በድርጅት ደረጃ በአዲሱ የአገልግሎት ዓመት ምን ለማከናወን እንደምንሻ በአእምሮአችን በግልጽ ለመወጠን የምንችልበት ተስማሚው ጊዜ አሁን ነው።
2 በመንፈሳዊ ማደግህን ቀጥል፦ ወደ እውነት የመጣነው በቅርቡ ከሆነ በእምነት የጠነከርን ለመሆን ፍላጎት ሊኖረን ይገባል። (ዕብ. 6:1–3) መንፈሳዊ ጥንካሬን ቀደም ብለን ያዳበርን ከሆንንም መርዳት የሚኖርብን አዲሶችንና እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሌሎችን ብቻ አይደለም፤ ይልቁን አስፈላጊው የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀትና የክርስቲያናዊ አኗኗር ተሞክሮዎች ሁሉ አሉኝ ሳንል የራሳችንን መንፈሳዊነት በንቃት መከታተል አለብን። የዕለት ጥቅስ እናደርጋለንን? በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚወጣው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም ጋር እኩል እንሄዳለንን? ለጉባኤ የመጽሐፍ ጥናትና ለመጠበቂያ ግንብ ጥናትስ እንዘጋጃለንን? ቢያንስ ቢያንስ እነዚህን ማድረግ የሁላችን ግብ ሊሆን ይገባል። ከዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ጥፋት ተርፈን አምላክ ላዘጋጀው አዲስ ዓለም ለመብቃት በመንፈሳዊ ማደጋችንን መቀጠል አለብን። — ከፊልጵስዩስ 3:12–16 ጋር አወዳድር።
3 መንፈሳዊ ንጽሕናህን ጠብቅ፦ በይሖዋ ዘንድ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ለማግኘት “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር” ሁሉ የነጻን መሆን አለብን። (2 ቆሮ. 7:1) አንዴ ከነጻን በኋላ አሮጌና ክፉ በሆነው በዚህ ዓለም ‘ማጥ ውስጥ ለመንከባለል’ መፈለግ ይገባናልን? (ከ2 ጴጥሮስ 2:22 ጋር አወዳድር።) በመንፈሳዊ ንጹሖችና ጠንካሮች ሆነን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ አለብን። እንዲህ ካደረግን የሰይጣንን ደባ በመዘንጋት ተታለን ለመውደቅ፣ ኃጢአት ለመሥራትና ከይሖዋ ሞገስ ለመራቅ አንዳረግም። — 2 ቆሮ. 2:11
4 ጥበብ ያለበትን ምክር ስማ፦ ምሳሌ 15:22 “ምክር ከሌለች ዘንድ የታሰበው ሳይሳካ ይቀራል፤ መካሮች በበዙበት ዘንድ ግን ይጸናል” ይላል። ሆኖም ከላይ ያሉትን ቃላት የተናገረው ሰሎሞን ከባዕዳን አገሮች ሴቶችን እንዳያገቡ ከአምላክ የተሰጠውን ምክር ባለ መስማቱ ‘ሚስቶቹ ሌሎችን አማልክት ይከተል ዘንድ ልቡ እንዲያዘነብል’ እንዳደረጉት አስታውስ። (1 ነገ. 11:1–4) ታዲያ እኛ በግላችን ጥበብ ያለበትን ምክር ካልሰማን በይሖዋ አገልግሎት ውጤታማ እንሆናለን ወይም ሌሎች ሊከተሉት የሚገባ አርዓያ እንተዋለን ብለን እንዴት ልንጠብቅ እንችላለን? (1 ጢሞ. 4:15) የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ልባችንን እንድንጠብቅ ይረዳናል። (ምሳሌ 4:23) ይሖዋ የሚወደውን መውደዳችን፣ የሚጠላውን መጥላታችን፣ አመራሩን ያለማቋረጥ መፈለጋችንና እሱን የሚያስደስተውን ነገር ማድረጋችን አስተማማኝ ጥበቃ ይሆንልናል። — ምሳሌ 8:13፤ ዮሐ. 8:29፤ ዕብ. 1:9
5 ለይሖዋ የምናቀርበው አምልኮ እንዲያው ለደንቡ ያህል ብቻ የሚደረግ ወይም በዓለም ያሉ ክርስቲያን ነን ባዮች ለአምላክ ያደሩ መስሎ ለመታየት እንደሚያደርጉት ዓይነት ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው እውነት ጋር የሚስማማ የመንፈስ ግለት ያለው፣ በተግባር የሚገለጽና ሕያው ነው።
6 የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ያለን ቁርጥ ውሳኔ በየዕለቱ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙት ይችላል። “በዓለም ያሉት” ወንድሞቻችን ሁሉ ተመሳሳይ ፈተና እንደሚደርስባቸውና የሚያጠነክረን ይሖዋ መሆኑን ማወቃችን ሊያበረታን ይገባል። (1 ጴጥ. 5:9, 10) በዚህ መንገድ በ1994 የአገልግሎት ዓመት አገልግሎታችንን ሙሉ በሙሉ ለመፈጸም እንችላለን። — 2 ጢሞ. 4:5