የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ማስጀመር
1 እውነተኛ ክርስቲያኖች ካሏቸው እጅግ የሚያረኩና የሚክሱ አጋጣሚዎች አንዱ በቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት አንድን ሰው ማስተማር ነው። አንዳንዶች ግን ጥናት ለማስጀመርም ሆነ ለመምራት ብቃቱ እንደሌላቸው ስለሚሰማቸው አስፈላጊ በሆነው በዚህ የአገልግሎቱ ልዩ ገጽታ ላይካፈሉ ይችላሉ። ጐበዝ የሆኑ ብዙ አስፋፊዎችና አቅኚዎች በአንድ ወቅት እንደዚሁ ይሰማቸው ነበር። ይሁን እንጂ በይሖዋ በመታመናቸውና በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የሚወጡትን ሐሳቦች ተግባራዊ በማድረጋቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን እንዴት ማስጀመርና መምራት እንደሚቻል ተምረዋል፤ ስለዚህም በአገልግሎታችው የሚያገኙትን ደስታ ለመጨመር ችለዋል። አንተም ይህን ዓይነት ግብ ልታወጣ ትችላለህ።
2 በቀጥታ በመጠየቅ ዘዴና በትራክቶች መጠቀም፦ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ከሚያስችሉን ቀላል መንገዶች አንዱ ሰዎችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንድናደርግላቸው ይፈልጉ እንደሆነ በቀጥታ ሰዎቹን መጠየቅ ነው። አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠኑ ሞቅ ባለ መንፈስ መጋበዙ ብቻ ሊበቃቸው ይችላል። ይህም የቤቱን ባለቤት እንዲህ ብሎ በመጠየቅ ብቻ ሊፈጸም ይችላል:- “የግል የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመጀመር ስለ መጽሐፍ ቅዱስና አምላክ ለምድር ስላለው ዓላማ ያለዎትን እውቀት ከፍ ለማድረግ ይፈልጋሉን?” ወይም ደግሞ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዴት እንደሚከናወን በተግባር ልታሳየው እንደምትፈልግ ልትነግረው ትችላለህ። ይህን ግብዣ ብዙዎች ላይቀበሉት ቢችሉም የሚቀበልህ ሰው ባገኘህ ጊዜ ምን ያህል እንደምትደሰት አስብ!
3 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር የሚያስችለው ሌላው መንገድ ደግሞ ከትራክቶቻችን በአንዱ መጠቀም ነው። ትራክቶች ትንንሾች ቢሆኑም እንኳን ኃይለኛና አሳማኝ መልዕክት ይዘዋል። በትራክት አማካኝነት ጥናት ለመምራት የሚቻለው እንዴት ነው? ቀላሉ መንገድ ለሰውየው ፍላጎት ያሳድርበታል ብለህ ያመንክበትን ትራክት በመስጠት ነው። ከዚያም የመጀመሪያውን አንቀጽ አብሮህ እንዲያነብ አንተ ራስህ ጋብዘው። ምዕራፍና ቁጥራቸው ብቻ የተጠቀሱትን ጥቅሶች አውጥተህ አንብብለትና ከትምህርቱ ጋር እንዴት እንደሚያያዙ ተወያዩበት። በመጀመሪያ ጉብኝትህ አንድ ወይም ሁለት አንቀጾችን ብቻ ትወያዩ ይሆናል። ሰውየው ከመጽሐፍ ቅዱስ አስደሳች ነገሮችን እየተማረ መሆኑን እየተረዳ በሄደ መጠን የምትወያዩበትን ሰዓት ረዘም ልታደርገው ትችላላለህ።
4 በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ በመጠቀም፦ አንዳንድ ጊዜ ሰውየው መጽሐፍ ቅዱስን እያወጣህ ብታወያየው ፈቃደኛ ሊሆን ይችላል። ሆኖም መደበኛ ጥናት ለመጀመር ወይም ከጽሑፎቻችን በአንዱ ተጠቅመህ እንድታስጠናው ላይፈልግ ይችላል። በዚህ ሁኔታም ቢሆን ለዘላለም መኖር ወይም ምክንያቱን ማስረዳት በሚባሉት መጽሐፎች ውስጥ ባሉት ክፍሎች ላይ የተመሠረቱ ፍላጎቱን የሚያነሳሱ ቅዱስ ጽሑፋዊ ውይይቶችን በመዘጋጀት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ልትመራለት ትችላለህ። ሆኖም ፍላጎት ያሳየውን ሰው ተመልሰህ ስታነጋግረው የምትጠቀመው በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ይሆናል። እንደነዚህ ያሉት ውይይቶች እንደሁኔታው 15 ወይም 20 ደቂቃ ወይም ከዚያ የበለጠ ጊዜ ሊወስዱ ይችላሉ። ሳታቋርጥና ደረጃ በደረጃ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ካወያየኸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመርክለት ማለት ነው፤ ስለዚህም እንደ ጥናት ሪፖርት ልታደርገው ትችላለህ። ተስማሚ በሆነ ጊዜም ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ ልታስተዋውቀውና በዚህ መጽሐፍ በመጠቀም መደበኛ ጥናት ልትጀምርለት ትችላለህ።
5 በመስክ አገልግሎት ላይ ከምታገኛቸው ሰዎች ጋር ብቻ ሳይሆን ከጎረቤቶችህ፣ አብረውህ ከሚውሉ ሰዎች ወይም ከቤተሰብህ አባሎች ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ጥረት አድርገሃልን? ጥናት እንዲጀምሩ ካነጋገርካቸው ቆየት ብሏልን? ሰሞኑን እንደገና ልታነጋግራቸው ሞክረሃልን? አንድ ዓይነት ዘዴ ተጠቅመህ ካልተሳካልህ በሌላ መንገድ ለመጠቀም አስበሃልን?
6 እስካሁን የተሰጡትን ሐሳቦች ከሠራህባቸው፣ በመስክ አገልግሎት ሳትታክት ጥረት ማድረግህን ከቀጠልክና ይሖዋ ጥረትህን እንደሚባርክ ከተማመንክ ጥናቶችን በማስጀመር ረገድ የተሳካልህ ልትሆን ትችላለህ። እውነት ያለውን ኃይልና ይሖዋ የሚሰጥህን እርዳታ አቅልለህ አትመልከት። በዚህ መንገድ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመምራት በአገልግሎቱ የምታገኘውን ደስታ ጨምር።