አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? በተባለው ብሮሹር ጥናት ማስጀመር
1 ከዓለም ዙሪያ የተገኙ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለው ብሮሹር እውነትን ለሰዎች ለማስተማር የሚጠቅም ውጤታማ መሣሪያ ነው። በዚህ ብሮሹር አማካኝነት በየሳምንቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እየተጀመሩ ነው። አምላክ ከእኛ የሚፈልገው በተባለው ብሮሹር አማካኝነት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማስጀመርና በመምራት ረገድ ተሳክቶልሃልን?
2 ብዙዎች ብሮሹሩን ማበርከት ቀላል ቢሆንላቸውም አንዳንዶች ጥናት ለማስጀመር ምን ማለት እንደሚችሉ ይቸግራቸዋል። ሌሎች አስፋፊዎች አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለውን ብሮሹር በመጠቀም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ምን ውጤታማ የሆኑ ዘዴዎች አግኝተዋል? በዚህ ረገድ ቀጥሎ የቀረቡት ሐሳቦች ጠቃሚ ሆነው እንደሚገኙ እሙን ነው።
3 ጥናቱ እንዴት እንደሚካሄድ ለማሳየት ሐሳብ አቅርብ፦ ለመጀመሪያ ጊዜ የቤቱን ባለቤት ስናነጋግር ወይም ተመላልሶ መጠየቅ ስናደርግ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምር በደፈናው ሐሳብ ከማቅረብ ይልቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ እንዴት እንደሚካሄድ ልናሳየው እንችላለን። እንዲህ ማድረጋችን “ጥናት” የሚለው ቃል በቤቱ ባለቤት አእምሮ ውስጥ የሚፈጥረውን ጥያቄና ጥርጣሬ ለማስወገድ ያስችላል። አንድ ጊዜ ጥናቱ እንዴት እንደሚካሄድ ማሳየት የምንችልበት አጋጣሚ ካገኘን ቀላል መግቢያ ብቻ ተጠቅመን በቀጥታ ጥናት መጀመር እንችላለን።
4 ዝግጅት ቁልፍ ሚና ይጫወታል፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ያለን ጉጉት ጥሩ ዝግጅት ከማድረጋችን ጋር ቀጥተኛ ዝምድና አለው። አስቀድሞ መዘጋጀት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራትን በተመለከተ የሚሰማንን ማንኛውንም የማመንታት ስሜት እንድናሸንፍ ይረዳናል። አቀራረባችንን ደጋግመን መለማመዳችን ያለ ችግር ሐሳባችንን በራሳችን አባባል እንድንገልጽ በውይይት መልክ ለመናገር ያስችለናል። እንዲህ ማድረጋችን እኛን ብቻ ሳንሆን የምናነጋግረውም ሰው ዘና እንዲል ያደርገዋል።
5 ጥናቱ እንዴት እንደሚካሄድ ለማሳየት ምን ያህል ጊዜ እንደሚፈጅብህ ለቤቱ ባለቤት መንገር እንድትችል አቀራረብህን ስትለማመድ ሰዓት መያዝህ ጠቃሚ ነው። አንድ ወንድም ራሱን ካስተዋወቀ በኋላ እንዲህ ይላል:- “ወደ ቤትዎ የመጣሁት በነፃ የምንሰጠው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራም ምን እንደሚመስል ላሳይዎ ነው። ጥናቱ እንዴት እንደሚካሄድ ለማሳየት አምስት ወይም አሥር ደቂቃ በቂ ነው። አምስት ደቂቃ ይኖርዎታል?” አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለው ብሮሹር፣ ትምህርት 1 በመጠቀም በአምስት ደቂቃ ውስጥ ማሳየት ይቻላል። እርግጥ በዚህ ጊዜ ውስጥ ማንበብ የሚቻለው የተወሰኑ ጥቅሶችን ብቻ ነው። ሆኖም የመጀመሪያውን ትምህርት በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ በመሸፈን የቤቱ ባለቤት የመጀመሪያ ጥናቱን ማድረግ ይችላል። ከዚያም ትምህርት 2ን ለማጥናት ተመልሰህ በምትመጣበት ጊዜ ጥናቱ 20 ደቂቃ ብቻ እንደሚወስድ ንገረው።
6 ቀጥሎ ያለው አቀራረብ ውጤታማ ሆኖ ተገኝቷል:- “አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? በተባለው በዚህ ብሮሹር አማካኝነት በጣም ቀላልና አጠር ያለ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዴት እንደሚካሄድ ባሳይዎ ደስ ይለኛል። ብዙዎች ለ16 ሳምንታት ያህል በሳምንት ከ20–30 ደቂቃ በመመደብ ለእነዚህ ዐበይት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች አጥጋቢ የሆኑ ቅዱስ ጽሑፋዊ መልስ ማግኘት እንደሚቻል ተገንዝበዋል።” የአርዕስት ማውጫውን ባጭሩ አሳየው። ትምህርት 1ን ገልጠህ እንዲህ ማለት ትችላለህ:- “አምስት ደቂቃ ገደማ ከፈቀዱልን ጥናቱ እንዴት እንደሚካሄድ ልናሳይዎ እንችላለን። ትምህርት 1 ‘አምላክ ምን እንደሚፈልግብህ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?’ የሚል ርዕስ ይዟል።” ከዚያም ሦስቱን ጥያቄዎች አንብብና በቅንፍ ውስጥ ስላሉት ቁጥሮች ግለጽለት። አንቀጽ 1ን አንብብና ሰውየው መልሱን እንዴት ማግኘት እንደሚችል ንገረው። የቤቱ ባለቤት አንቀጽ 2ን እንዲያነብ ልትጠይቀው ትችላለህ። ከዚያም እንዲህ ማለት ትችላለህ:- “በዚህ አንቀጽ መሠረት ለዚህ ጥያቄ ምን መልስ ይሰጣሉ? [ጥያቄውን በድጋሚ አንብብና የቤቱ ባለቤት ሐሳብ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ከእያንዳንዱ አንቀጽ ጋር ተያይዘው የቀረቡ ጥቅሶች እንዳሉ ያያሉ። እነዚህ ጥቅሶች መጽሐፍ ቅዱስ ለጥያቄዎቹ በሚያቀርበው መልስ ላይ እንድናተኩር ያደርጉናል። ለምሳሌ ያህል 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17ን እናንብብና ጥቅሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲን በሚመለከት እርስዎ የሰጡትን መልስ ይደግፍ እንደሆነ እንመልከት።” አንቀጽ 3 ተነብቦ በጥያቄው ላይ ከተወያያችሁና ዮሐንስ 17:3 ከተነበበ በኋላ የቤቱ ባለቤት ትምህርት 1ን በማጥናት ያገኘውን (ወይም ያገኘችውን) እውቀት እንዲያገናዝብ እርዳው። ከዚህ በኋላ ትምህርት 2ን ገልጠህ “ስለ አምላክ ልንማር የምንችልባቸው ሁለት መንገዶች ምንድን ናቸው?” የሚለውን የመጨረሻ ጥያቄ ማንበብ ትችላለህ። ከዚያም እንዲህ ብለህ ጠይቀው:- “ትምህርት 2ን በማጥናት መልሱን ማግኘት እንድንችል ሌላ ጊዜ ከ20–30 ደቂቃ ማግኘት የሚችሉት መቼ ነው?”
7 ውይይቱን ቀላል ማድረግና ተስማሚ ሲሆን ደግሞ የቤቱን ባለቤት ማመስገን አስፈላጊ ነው። ሌላ ቀጠሮ ለመያዝ ስትነጋገሩ ጥናቱን መቀጠል ይፈልግ እንደሆነ ከመጠየቅ ይልቅ ለሚቀጥለው ጥናት ተመሳሳይ የሆነ ዝግጅት እንዲያደርግ ብቻ አበረታታው። በድጋሚ የምትገናኙበትን ጊዜ በጉጉት እንደምትጠባበቅ ግለጽለት። አንዳንድ አስፋፊዎች ቀጠሮ መያዝ አስቸጋሪ በሚሆንበት ጊዜ አንድ ትምህርት በስልክ ለማጥናት ሐሳብ ያቀርባሉ። ለሚቀጥለው ጥናት ስትገናኙ ብሮሹሩን በቀላሉ ማግኘት እንዲችል አመቺና ጥሩ ቦታ ላይ እንዲያስቀምጠው ተማሪውን ልታበረታታው ትችላለህ።
8 ቁርጥ ውሳኔ አድርግ:- ስኬታማ ለመሆን ቁልፉ ዝግጅት ቢሆንም ግባችንን ዳር ለማድረስ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ አለብን። በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ አንድን ትምህርት መሸፈን ተፈታታኝ ሊሆን ስለሚችል ጥናቱን እንዴት እንደሚካሄድ በምታሳይበት ጊዜ ቅልጥፍና እንዲኖርህ አቀራረቡን እንደ አስፈላጊነቱ ደጋግመህ ለመዘጋጀት ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ከቤት ወደ ቤት፣ መደበኛ ያልሆነ እንዲሁም በስልክ ምሥክርነት ስትሰጥ ለምታገኛቸው ሰዎች ሁሉ ጥናቱ የሚካሄድበትን መንገድ ለማስረዳት ሞክር። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር አስቸጋሪ ከሆነብህ ተስፋ አትቁረጥ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በማስጀመር ረገድ ስኬታማ መሆን ቁርጥ ውሳኔ ማድረግንና ለሌሎች እውነትን ለማካፈል ልባዊ ፍላጎት መያዝ ይጠይቃል።—ገላ. 6:9
9 እነዚህን ሐሳቦች ሥራ ላይ በማዋል አንተም አምላክ ከእኛ የሚፈልገው በተባለው ብሮሹር አማካኝነት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመጀመርና በመምራት አንድ ሰው በሕይወት መንገድ ላይ እንዲጓዝ የመርዳት መብት ታገኝ ይሆናል።—ማቴ. 7:14