ምሥራች በተባለው ብሮሹር ተጠቅሞ ማስጠናት
1. ምሥራች የተባለው ብሮሹር የተዘጋጀው በምን መንገድ ነው?
1 በሐምሌ የመንግሥት አገልግሎታችን ላይ እንደተገለጸው አዘውትረን ከምንጠቀምባቸው የማስተማሪያ መሣሪያዎቻችን መካከል አንዱ ከአምላክ የተላከ ምሥራች! የተባለው ብሮሹር ነው። ጥቅሶቹ ምዕራፍና ቁጥራቸው ብቻ መጠቀሳቸው የምናነጋግረው ሰው በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ እንዲያነብ ያስችለዋል። አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ማስጠኛ ጽሑፎቻችን የተዘጋጁት ግለሰቡ ጽሑፎቹን በግሉም ለማጥናት በሚያስችለው መንገድ ነው፤ ይህ ብሮሹር የተዘጋጀው ግን ከአንድ አስጠኚ ጋር በውይይት እንዲጠና ተደርጎ ነው። በመሆኑም ብሮሹሩን ስናበረክት እንዴት እንደሚጠና ማሳየታችን የምናነጋግረው ግለሰብ መጽሐፍ ቅዱስ የያዘውን ምሥራች መማር በጣም አስደሳች መሆኑን እንዲገነዘብ ሊረዳው ይችላል።—ማቴ. 13:44
2. አንድን ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ አግኝተን ስናነጋግረው ምሥራች የተባለውን ብሮሹር መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
2 ሰዎችን ለመጀመሪያ ጊዜ ስናነጋግር፦ እንዲህ ማለት ትችላላችሁ፦ “ብዙ ሰዎች የዓለማችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በጣም ያሳስባቸዋል። የዓለም ሁኔታ እየተሻሻለ የሚሄድ ይመስልዎታል? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ተስፋ የሚፈነጥቅ ምሥራች ይዟል። መጽሐፍ ቅዱስ ለየትኞቹ ጥያቄዎች መልስ እንደሚሰጥ ላሳይዎት።” ብሮሹሩን ስጡትና በጀርባ ሽፋኑ ላይ ካሉት ጥያቄዎች መካከል በየትኛው ላይ መወያየት እንደሚፈልግ ጠይቁት። ከዚያም እሱ በመረጠው ርዕስ ሥር የሚገኘውን የመጀመሪያውን አንቀጽ በመጠቀም እንዴት ማጥናት እንደምትችሉ አሳዩት። ሌላው አማራጭ ደግሞ የምታነጋግሩትን ግለሰብ እናንተ በመረጣችሁት ትምህርት ላይ የተመሠረተ ፍላጎቱን ሊያነሳሳ የሚችል ጥያቄ መጠየቅ ነው፤ ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መልስ ከብሮሹሩ ላይ እንዴት ማግኘት እንደሚችል አሳዩት። አንዳንድ አስፋፊዎች ከትምህርቱ ጋር የሚሄድ ቪዲዮ jw.org ላይ ካለ ቪዲዮውን ለግለሰቡ የማሳየት ልማድ አላቸው።
3. ምሥራች የተባለውን ብሮሹር በመጠቀም ጥናት መምራት የሚቻለው እንዴት ነው?
3 በብሮሹሩ ጥናት መምራት የሚቻልበት መንገድ፦ (1) የምታነጋግሩት ግለሰብ ትኩረቱን በዋናው ነጥብ ላይ እንዲያደርግ በቅድሚያ በተራ ቁጥር የሰፈሩትንና በደማቅ የተጻፉትን ጥያቄዎች አንብቡለት። (2) ከዚያ አንቀጹን አንብቡ። (3) በሰያፍ የተጻፉትን ጥቅሶች አንብቡ፤ የታሰበባቸው ጥያቄዎች በመጠየቅ የምታነጋግሩት ሰው ጥቅሶቹ ጥያቄውን ለመመለስ የሚረዱት እንዴት እንደሆነ እንዲገነዘብ እርዱት። (4) በዚያው ጥያቄ ሥር ሌላ አንቀጽ ካለ ከላይ በ2ኛውና በ3ኛው ነጥብ ላይ የተጠቀሱትን ሐሳቦች በድጋሚ ተግባራዊ አድርጉ። ከጥያቄው ጋር የሚሄድ ቪዲዮ ካለና ግለሰቡ አይቶት የማያውቅ ከሆነ በውይይታችሁ መሃል ቪዲዮውን አሳዩት። (5) በመጨረሻ ግለሰቡ ሐሳቡን ተረድቶት እንደሆነ ለማወቅ በደማቅ የተጻፈውን ጥያቄ አቅርቡለት።
4. ይህን ግሩም መሣሪያ በተሻለ መንገድ እንድንጠቀምበት ምን ማድረጋችን ጠቃሚ ሊሆን ይችላል?
4 በቅድሚያ እናንተ ራሳችሁ ይህን ግሩም ብሮሹር በሚገባ አጥኑት። ባገኛችሁት አጋጣሚ ሁሉ ተጠቀሙበት። ከእያንዳንዱ ጥናት በፊት ስለ ግለሰቡ ሁኔታ አስቡ፤ እንዲሁም በትምህርቱ ላይ የሚገኙትን ጥቅሶች ተጠቅማችሁ እንዴት ብታወያዩት የተሻለ እንደሚሆን ለማሰብ ሞክሩ። (ምሳሌ 15:28፤ ሥራ 17:2, 3) ይህን ብሮሹር በመጠቀም ረገድ ልምድ እያገኛችሁ ስትሄዱ ብሮሹሩ ለሰዎች እውነትን ለማስተማር ጠቃሚ መሣሪያ እንደሆነ መገንዘባችሁ አይቀርም።