ይሖዋ እንደሚያሳድግ እምነት ይኑራችሁ
1 “አንድ አዲስ ጉባኤ እንዲቋቋም በመርዳት የሚገኘውን ልዩ የሆነ ደስታ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀምሻለሁ። ይህም ከሁለት ዓመታት በላይ በትጋት መሥራት፣ ዘወትር መጸለይና ‘ነገሮችን በሚያሳድገው’ በይሖዋ ላይ መመካትን ጠይቆብኛል።” ይህን የጻፈው እድገት ለማግኘት በይሖዋ ላይ የመመካትን አስፈላጊነት የተገነዘበ አንድ ትጉህ አቅኚ ነበር። (1 ቆሮ. 3:5-9) እኛም በአገልግሎታችን መንፈሳዊ ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች ለማግኘት በምናደርገው ፍለጋ ፍሬ እንድናፈራ የአምላክ ድጋፍ ያስፈልገናል።—ምሳሌ 3:5, 6
2 እድገት መኮትኮት ይጠይቃል፦ የእውነት ዘር እንዲያድግ መኮትኮት ያስፈልገዋል። በመጀመሪያው ግንኙነታችን ማግስት ወይም በሁለተኛው ቀን ተመልሶ መጠየቁ ብዙውን ጊዜ ጥሩ ውጤት ያስገኛል። ሞቅ ያለ ስሜትና የወዳጅነት መንፈስ ይኑርህ። የምታነጋግረው ሰው እንዲረጋጋ አድርግ። አንተ ብቻ ተናጋሪ አትሁን። ስለ አንተ ለማወቅ እንዲችል አድርግ፤ እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ እንደምታስብለት አሳይ።
3 በነሐሴና በመስከረም፣ ለምናገኛቸው ሰዎች የተለያዩ ብሮሹሮችን በማበርከት ላይ እናተኩራለን። ይሁን እንጂ ፍላጎት ያሳዩትንና ጽሑፍ የተበረከተላቸውን ሰዎች ተከታትለን መርዳት ይኖርብናል። ይህን የምናደርገው ተመላልሶ መጠይቅ በማድረግና መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠኑ በመጋበዝ ነው። (ማቴ. 28:19, 20) ይህን ለማድረግ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለውን ብሮሹር ጥናት ለማስጀመር ልንጠቀምበት እንችላለን። ቀጥሎ የሚገኙት ሁለት ሐሳቦች ጠቃሚ ሆነው ታገኛቸው ይሆናል።
4 የዓለም ሁኔታዎች ወዴት እያመሩ ይሆን የሚለው ጉዳይ ያሳሰበውን ሰው አነጋግረህ ከነበረ እንዲህ በማለት ውይይትህን ልትቀጥል ትችላለህ:-
◼ “የሰብዓዊው ኅብረተሰብ በሥነ ምግባር እያዘቀጠ መሄድ እንደ እኔ አሳስቦዎት እንደሚሆን አምናለሁ። በቤተሰብ ውስጥ ስላለው ዓመፅ ማለትም በልጆች፣ በወላጆችና በትዳር ጓደኛ ላይ ስለተፈጸሙ በደሎች የሚገልጹ አሳዛኝ ዘገባዎችን እንሰማለን። እንዲሁም ብዙ ሰዎች የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት ሲዋሹና ሲሰርቁ ምንም የሚሰማቸው አይመስልም። ሰዎች ሕይወታቸውን የሚመሩበት መንገድ አምላክን የሚያሳስበው ይመስልዎታል? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] አምላክ ለሰዎች መመሪያ እንዲሆኑ ያወጣቸው የተወሰኑ የአቋም ደረጃዎች አሉ፤ እነሱም ከባዶች አይደሉም።” 1 ዮሐንስ 5:3ን አንብብ። ከዚያም አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለውን ብሮሹር አሳየውና ትምህርት 10ን ገልጠህ የመጀመሪያውን አንቀጽ አንብብ። ከአንቀጽ 2-6 መግቢያ ላይ ጋደል ተደርገው የተጻፉትን ቃሎችና ሐረጎች አሳይና እሱ ወይም እሷ ለኅብረተሰቡ ይበልጥ ጎጂ ናቸው የሚሏቸው ድርጊቶች የትኞቹ እንደሆኑ እንዲነግርህ ወይም እንድትነግርህ አድርግ። ከመልሳቸው ጋር የሚዛመደውን አንቀጽ አንብብና አጋጣሚው በፈቀደልህ መጠን አንድ ወይም ሁለት ጥቅሶችን ጥቀስ። አንቀጽ 7ን በማንበብ ከደመደምህ በኋላ ተጨማሪ ለማድረግ እንድትችል ተመልሰህ ለመምጣት ዝግጅት አድርግ።
5 የቤተሰባቸው ጉዳይ የሚያሳስባቸውን ሰዎች አነጋግረህ ከነበረ እንደሚከተለው ልትል ትችላለህ:-
◼ “ፈጣሪ የተሳካ የቤተሰብ ሕይወት ለመገንባት የሚያስፈልጉንን መሣሪያዎች ይሰጠናል ብሎ መጠበቁ ምክንያታዊ ይመስልዎታል?” መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት። አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተሰኘውን ብሮሹር አሳየውና ወደ ትምህርት 8 በመሄድ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል የሚጠበቅበት ምን እንደሆነ የሚያሳዩ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንደያዘ አብራራ። ከብሮሹሩ ከፍተኛ ጥቅም ለማግኘት ብሮሹሩን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ልታሳየው እንደምትፈልግ ግለጽለት። በገጽ 2 ላይ የሚገኙትን መመሪያዎች ተከተል። የጀመራችሁትን የትምህርት 8 ጥናት በሌላ ጊዜ ለመቀጠል ወይም ትምህርቱን ጨርሳችሁት ከሆነ ደግሞ የቤቱ ባለቤት የመረጠውን ሌላ ትምህርት ለማጥናት ተመልሰህ የምትሄድበትን ዝግጅት አድርግ።
6 ሰዎች ብሮሹሮችን እንዲወስዱ በመጋበዝ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለማቅረብ የሚያስችሉ አቀራረቦች እነሆ:-
◼ “ዛሬ ወደ እርስዎ የመጣነው ለጥቂት ደቂቃዎች አንድ በጣም አስፈላጊ የሆነ ትንቢት ልናነብልዎት ስላሰብን ነው። ትንቢቱን የጻፈው ሐዋርያው ዮሐንስ ሲሆን በራእይ ምዕራፍ 12 ከቁጥር 7 እስከ 12 ላይ ይገኛል። [ጥቅሱን አንብብ ወይም ቢያንስ ዋና ዋና ነጥቦቹን ጥቀስ።] ይህ ለእኛ ምን ትርጉም እንዳለው ያውቃሉ? [ቆም በል።] ይህ ጦርነት በሰማይ ተከናውኗል። የሰይጣን ታላቅ ቁጣ ያስከተላቸውን ውጤቶች በሕይወታችን ውስጥ በየዕለቱ እናያለን። [አንዳንድ ምሳሌዎችን ጥቀስ። የአምላክ መንግሥት ከተባለው ብሮሹር ገጽ 22 ላይ የሚገኘውን ሥዕል ወይም በደስታ ኑር! ከተሰኘው ብሮሹር ሥዕል ቁጥር 22 እና 23ን ልታሳየው ትችላለህ።] በሌላ ጊዜ አምላክ በሕይወታችን የሚገጥሙንን እነዚህን ችግሮች በተመለከተ ምን እንደሚያደርግ ላሳይዎት እፈልጋለሁ። እስከዛው ድረስ ግን እነዚህን ሁለት ብሮሹሮች 2 ብር ብቻ ከፍለው በመውሰድ ቢያነቧቸው ደስ ይለኛል።” [አንድ ብሮሹር ብቻ ለመስጠትም ትችል ይሆናል።] ከላይ ባለው አቀራረብ ላይ አንዳንድ ለውጦች በማድረግ የሙታን መናፍስት የተባለውን ብሮሹር ለማበርከት ይቻላል። ገጽ 10ን ገልጠህ በማሳየት ብሮሹሩን እንዲወስድ ልትጋብዝ ትችላለህ።
7 “የሙታን መናፍስት” የተባለውን ብሮሹር በመጠቀም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ትንሣኤ በሚናገረው ምሥራች ላይ ለማትኮር ከፈለግህ እንዲህ ልትል ትችላለህ:-
◼ “ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ሰዎች በአሳዛኝ ሁኔታዎች በመሞታቸው ምክንያት ብዙ ድንኳኖች ተጥለው አይተናል። አንድ የሚያጽናና ሥዕል ላሳይዎት እፈልጋለሁ። [የሙታን መናፍስት በተባለው ብሮሹር በገጽ 29 በሚገኘው ሥዕል ላይ ሐሳብ ስጥ።] ሥዕሉ የተመሠረተው በዚህ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ በሚገኙት የኢየሱስ ቃላት ላይ ነው። [ዮሐንስ 11:11-14ን ወይም 5:28, 29ን አንብብ።] ሌሎች ተጨማሪ በረከቶች አሉ፤ ነገር ግን ስለ እነርሱ በሚቀጥለው ጊዜ እንወያያለን። እስከዛው ድረስ ግን ራሳችንን ከሰይጣን ጥቃት እንዴት ልንከላከል እንደምንችልና አምላክ ምድርን እንዴት ገነት እንደሚያደርጋት የሚናገረውን ይህን ብሮሹር ወስደው ቢያነቡትስ? [ብሮሹሩን እንዲወስድ ጋብዘው።]”
8 ልጆቻችን ጭምር ሊጠቀሙበት የሚችሉ ቀላል አቀራረብ:-
◼ “ወጣቶችንም ሆነ በዕድሜ የገፉ ሰዎችን ወደ አምላክ እንዲቀርቡ እያበረታታን ነው። ሆኖም ፈጣሪያችን ስም እንዳለው እንኳን የማያውቁ ብዙ ሰዎች መኖራቸውን ለመገንዘብ ችለናል። ኢየሱስ ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ’ ብለን እንድንጸልይ ባስተማረበት ወቅት ስለ ስሙ ተናግሯል። ስሙን በተመለከተ ከዚህ ብሮሹር ብዙ ለመማር ይችላሉ።” [መለኮታዊው ስም በተባለው ብሮሹር ገጽ 31 ላይ “የአምላክን ስም ከማወቅ የሚገኙ በረከቶች” የሚለውን ንዑስ ርዕስ በማሳየት ብሮሹሩን እንዲወስድ ጋብዘው።]
9 ከቤት ወደ ቤት በመሄድ ክልላችንን መሸፈን፣ ሕዝብ በብዛት በሚገኝባቸው ቦታዎች ከሰዎች ጋር በትጋት መነጋገር፣ ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት የሚኖረውን ተፈታታኝ ሁኔታ በደስታ መቀበል ከአምላክ ጋር ‘አብረን የመሥራታችን’ ክፍል ነው። (1 ቆሮ. 3:9) ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ፈልገን ለማግኘት እንዲሁም ፍላጎታቸውን ኮትኩተን ለማሳደግ ጠንክረን ስንሠራና ነገሮችን በሚያሳድገው በይሖዋ ላይ ስንደገፍ ማንኛውም ሌላ ሥራ ሊሰጠን የማይችለውን እውነተኛ እርካታ እናገኛለን።