ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑት ነገሮች ቅድሚያ ስጡ
1 ለመንፈሳዊ ደህንነታችን ወሳኝ የሆኑ አንዳንድ አስፈላጊ ነገሮች ምንድን ናቸው? የግል ጥናት፣ በስብሰባ መገኘት፣ የማያቋርጥ ጸሎት፣ ገንቢ ጓደኝነትና ክርስቲያናዊ አገልግሎት በዚህ ውስጥ የሚካተቱ ነገሮች እንደሆኑ ምንም አያጠራጥርም። በሕይወታችን ውስጥ አስፈላጊ የሆኑትን ጉዳዮች የላቀ ቦታ ካልሰጠናቸው ጥሩ መንፈሳዊ ጤንነት ሊኖረን አይችልም።
2 ሆኖም ሁላችንም ከሥጋዊ ፍላጎቶች ጋር ትግል የምናደርግ በመሆኑ ራሳችንን መገሠጽ ያስፈልገናል። (ገላ. 5:17) የራስ ወዳድነት ፍላጎቶችን ለማሟላት በምናደርገው ጥረት ብዙ ጥቅም እንደምናገኝ አድርገን በጭራሽ ማሰብ የለብንም። (ኤር. 17:9) ስለዚህ ልባችንን ለመጠበቅ እንድንችልና እንዳንታለል ራሳችንን አዘውትረን መመርመራችን በጣም አንገብጋቢ ነው።—ምሳሌ 4:23፤ 2 ቆሮ. 13:5
3 የራሳችሁን ልብ መርምሩ፦ ይህን ማድረግ የምትችሉት ራሳችሁን በሐቀኝነት አንዳንድ ጥያቄዎች በመጠየቅ ነው:- የአምላክን ቃል ለማንበብ እጓጓለሁ? (1 ጴጥ. 2:2) በሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች የመገኘትን አስፈላጊነት ተገንዝቤያለሁ? (ዕብ. 10:24, 25) በጸሎት እጸናለሁ? (ሮሜ 12:12) መንፈሳዊ አስተሳሰብ ካላቸው ሰዎች ጋር መወዳጀት እፈልጋለሁ? (ሮሜ 1:11, 12) ምስራቹን ለመስበክ በግል ግዴታ እንዳለብኝ ይሰማኛል? (1 ቆሮ. 9:16) የምትሰጧቸው አዎንታዊ ምላሾች ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች የማስቀደም ፍላጎት እንዳላችሁ ያሳያሉ።
4 የዘወትር ልማድህን መርምር፦ በጊዜ አጠቃቀማችሁ ረገድ ቅድሚያ የምትሰጧቸውን ነገሮች በመመደብ የልባችሁን ፍላጎት መመርመራችሁን መቀጠል ይኖርባችኋል። ይህ ዘወትር መጽሐፍ ቅዱስንና እያንዳንዱን የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶች እትም ለማንበብ እንዲሁም ለስብሰባዎች ለመዘጋጀት ጊዜ መመደብን ያጠቃልላል። ከዚህም በተጨማሪ ቤተሰቡ አብሮ የሚያጠናበትም ሆነ የሚጸልይበት ጊዜ መመደብ ያስፈልጋል። ለቴሌቪዥን ወይም ለኮምፒዩተር የምታውሉት ጊዜ ምን ያህል መሆን እንዳለበት ወስኑ። በሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ፤ ሌሎች ጉዳዮቻችሁንም ከጉባኤ ስብሰባዎች ጋር በማይጋጭ ሁኔታ አመቻቹ። የቤተሰባችሁ አባላት በሙሉ በየሳምንቱ በመስክ አገልግሎት እንዲሳተፉ ዕቅድ አውጡ።
5 በሕይወታችን ውስጥ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ጉዳዮች ማስቀደማችን ደስታ እንደሚያስገኝልን ጥርጥር የለውም።