የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ደቀ መዛሙርት ማድረግ በሚያስችል መንገድ ማስጠናት
1 ፊልጶስ ‘ስለ ኢየሱስ ወንጌል ከሰበከለት’ በኋላ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ “እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድን ነው?” በማለት ጠይቋል። (ሥራ 8:27-39) ጃንደረባው በመንፈስ አነሳሽነት ለተጻፉት የአምላክ መጻሕፍት ቀድሞውንም ፍቅር ነበረው። በመሆኑም ከፊልጶስ መንፈሳዊ እገዛ ካገኘ በኋላ ደቀ መዝሙር ለመሆን ዝግጁ ሆኖ ነበር። ሆኖም ቅዱሳን መጻሕፍትን በግላቸው መመርመር እንዳለባቸው አምነው የሚቀበሉ ሁሉም ሰዎች አይደሉም።
2 መጽሐፍ ቅዱስ ለጊዜያችን የያዘውን መልእክት ሰዎች እንዲመረምሩ ለማበረታታት የይሖዋ ድርጅት ጽሑፎች አዘጋጅቷል። የተማሩ ቢሆኑም እንኳ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙም እውቀት ለሌላቸው ቅን ሰዎች የሚቀርብላቸው ማብራሪያ ማራኪ መሆን አለበት። ጽሑፎቹ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን የመመርመር ፍላጎት እንዲያድርባቸው በሚያደርግ መንገድ የተዘጋጁ ናቸው።
3 አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በምንጀምርበት ጊዜ በሰኔ 1996 የመንግሥት አገልግሎታችን ላይ አባሪ ሆኖ የወጣውን በእውቀት መጽሐፍ ውጤታማ ጥናት እንዴት መምራት እንደሚቻል የሚገልጸውን ጥሩ ሐሳብ መከለሱ ይረዳናል። ጥናቱ በሚካሄድበት ወቅት ተማሪው የሚያደርገውን እድገት ማስተዋልህ በየትኞቹ መስኮች ተጨማሪ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ለማወቅ ያስችልሃል። ጥቅሶቹን እያወጣ ትምህርቶቹን አስቀድሞ እንዲዘጋጅ ተማሪውን አበረታታው። በራሱ አባባል የሚሰጣቸው ሐሳቦች ለእውነት ያለውን ልባዊ አድናቆት ሊያንጸባርቅ ይችላል። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረው የሚገኙና ሌሎቹንም የማኅበሩን ጽሑፎች የሚያነቡ ተማሪዎች አብዛኛውን ጊዜ ፈጣን እድገት ያደርጋሉ። እየተማረ ያለውን ነገር መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለሌሎች እንዲናገር አበረታታው። መንፈሳዊ እድገት እንዲያሳይ ምን ማድረግ እንደሚገባው በደግነት ግለጽለት። እርምጃ ከማይወስዱ ሰዎች ጋር ለረዥም ጊዜ ጥናት መምራት የለብንም። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ለመማር፣ ለእውነት ጽኑ አቋም ለመያዝና ራስን ወደ መወሰንና መጠመቅ ደረጃ ለመድረስ በራሳቸው መነሳሳት አለባቸው።
4 በአንዳንድ ቤተሰቦች የቤተሰቡ አባላት ለየብቻ ስለሚያጠኑ ከአንድ በላይ ጥናት እየተመራ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ግን ቤተሰቡ አንድ ላይ ሆኖ የሚያጠናበት ፕሮግራም ቢኖር ጥሩ ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም ይህ ቤተሰቡን በመንፈሳዊ ለማቀራረብ ይረዳል።
5 ኢየሱስ ወደ ሰዎች በመሄድ ደቀ መዛሙርት እንድናፈራ አዞናል። (ማቴ. 28:19) ይህን ለማድረግ፣ “እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድን ነው?” ብለው የሚጠይቁበት ደረጃ ላይ እስኪደርሱ ድረስ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ለመርዳት የሚያስችሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መምራት አለብን።