“የሚመራኝ ሳይኖር . . . እንዴት ይቻለኛል?”
1 ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ከአምላክ ቃል የሚያነበውን ይረዳው እንደሆነ ወንጌላዊው ፊልጶስ በጠየቀው ጊዜ “የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል?” ሲል መልሷል። ከዚያም ፊልጶስ ደስ እያለው ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን ምሥራች እንዲያስተውል ስለረዳው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ወዲያው ተጠመቀ። (ሥራ 8:26-38) ፊልጶስ እንዲህ በማድረግ “አሕዛብን ሁሉ . . . እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ሲል ክርስቶስ የሰጠውን ትእዛዝ ፈጽሟል።—ማቴ. 28:19, 20
2 ፊልጶስ እንዳደረገው ሁሉ እኛም ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ የተሰጠንን ትእዛዝ መፈጸም ይኖርብናል። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ የምናስጠናቸው ሰዎች ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ያደረገው ዓይነት ፈጣን መንፈሳዊ እድገት ሲያደርጉ አይታይም። ወደ ይሁዲነት የተለወጠው ይህ ሰው ከቅዱሳን ጽሑፎች ጋር ጥሩ ትውውቅ ያለው ከመሆኑም በላይ ተቀባይ የሆነ ልብ ነበረው። ስለዚህ ያስፈለገው ነገር ቢኖር ኢየሱስ ተስፋ የተደረገበት መሲህ መሆኑን መቀበል ብቻ ነበር። የምናስጠናቸው ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ምንም ትውውቅ የሌላቸው፣ በሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶች የተጠላለፉና በከባድ የግል ችግሮች የተዋጡ ከሆኑ ትግሉ ቀላል አይሆንም። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ራሳቸውን ወደ መወሰንና ወደ መጠመቅ እንዲደርሱ በመምራት ረገድ ውጤታማ እንድንሆን ምን ሊረዳን ይችላል?
3 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪውን መንፈሳዊ ፍላጎት አስተውሉ:- የነሐሴ 1998 የመንግሥት አገልግሎታችን አባሪ ገጽ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለውን ብሮሹርና እውቀት መጽሐፍን ተጠቅሞ ሌሎችን ማስጠናት ሊወስድ ስለሚችለው የጊዜ ርዝመት ማብራሪያ ሲሰጥ እንዲህ ብሎ ነበር:- “የጥናቱን ፍጥነት እንደ ተማሪው ሁኔታና ችሎታ ማድረግ አስፈላጊ ነው። . . . ተማሪው ጥናቱን በቶሎ እንዲጨርስ ለማድረግ ሲባል የሚደረገው ሩጫ ሊያገኝ የሚገባውን የተጣራ እውቀት እንዲያጨልምበት ማድረግ አይገባም። እያንዳንዱ ተማሪ ከአምላክ ቃል ውስጥ ያገኘው አዲስ እምነት በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነባ ሊሆን ይገባዋል።” በመሆኑም እውቀት መጽሐፍን በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ አጥንቶ ለመጨረስ ሲባል አለመጣደፉ ይመረጣል። አንዳንዶችን ወደ ጥምቀት እንዲደርሱ ለመርዳት ከስድስት ወር የበለጠ ጊዜ ያስፈልግ ይሆናል። ጥናቱን በምትመሩበት በእያንዳንዱ ሳምንት ተማሪው ከአምላክ ቃል የሚማራቸውን ነገሮች እንዲያስተውልና እንዲቀበል ለመርዳት አብራችሁት በቂ ጊዜ አሳልፉ። አንዳንድ ጊዜ ከእውቀት መጽሐፍ አንድ ምዕራፍ ለመሸፈን ሁለት ወይም ሦስት ሳምንት ያስፈልግ ይሆናል። ይህም ቁጥራቸው ብቻ የተጠቀሱትን ብዙ ጥቅሶች ለማንበብና ለማብራራት በቂ ጊዜ እንዲኖር ያስችላል።—ሮሜ 12:2
4 ይሁን እንጂ እውቀት መጽሐፍን አስጠንታችሁ ከጨረሳችሁ በኋላ ተማሪው ስለ እውነት ያለው ግንዛቤ የተሟላ መሆን እንደሚያስፈልገው ወይም ለእውነት የጸና አቋም ለመውሰድና ራሱን ለአምላክ ለመወሰን ከልቡ እንዳልተነሳሳ ብታስተውሉስ? (1 ቆሮ. 14:20) ተማሪው ወደ ሕይወት በሚወስደው መንገድ ላይ እንዲጓዝ ለመርዳት ምን ተጨማሪ ነገር ማድረግ ትችላላችሁ?—ማቴ. 7:14
5 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችሁን መንፈሳዊ ፍላጎት አሟሉ:- አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለውን ብሮሹር እና እውቀት መጽሐፍን ካስጠናችሁ በኋላ ተማሪው በአዝጋሚ ሁኔታም ቢሆን እድገት እያደረገ እንዳለና ለሚማረው ነገር አድናቆት እያዳበረ እንደሆነ በግልጽ ከተመለከታችሁ ሌላ ሁለተኛ መጽሐፍ ተጠቅማችሁ ጥናቱን ቀጥሉ። እንዲህ ማድረጉ ሁልጊዜ አስፈላጊ ላይሆን ይችላል። አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ግን እውነተኛ ሰላም (እንግሊዝኛ)፣ የአምልኮ አንድነት ወይም መጽሐፍ ቅዱስ—የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? ከተባሉት መጽሐፎች አንዱን በመጠቀም ጥናቱን ቀጥሉ። ጉባኤው እነዚህ መጽሐፎች ባይኖሩት እንኳን ብዙዎቹ አስፋፊዎች የግል ቅጂ አላቸው። ከማኅበሩ በትእዛዝ ማግኘት የሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስ—የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የሚለውን መጽሐፍ ብቻ ነው። ሆኖም በማናቸውም ሁኔታ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለው ብሮሹርና እውቀት መጽሐፍ መጀመሪያ መጠናት አለባቸው። ተማሪው ሁለተኛውን መጽሐፍ አጥንቶ ከመጨረሱ በፊት ቢጠመቅም ጥናት ተብሎ ይቆጠራል። ጥናቱን ለመቀጠል የዋለው ጊዜና ተመላልሶ መጠየቅም ሪፖርት መደረግ አለበት።
6 ይህ ማለት አንድ መጽሐፍ ብቻ አጥንተው በቅርቡ የተጠመቁ ሰዎች ሌላ ሁለተኛ መጽሐፍ እንደገና እንዲያጠኑ መደረግ አለበት ማለት ነውን? የግድ እንደዚያ ማለት ላይሆን ይችላል። ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ ቀዝቅዘው ወይም በእውነት ውስጥ እድገት ሳያደርጉ ቀርተው ይሆናል። ከዚህ የተነሣ እውነትን በተሻለ ሁኔታ በሕይወታቸው ውስጥ ለመተርጎም የግል እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ይሰማቸው ይሆናል። ከአንድ ከተጠመቀ አስፋፊ ጋር ጥናት እንደገና ከመጀመሩ በፊት የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹን ማማከር ያስፈልጋል። ይሁን እንጂ ቀደም ሲል እውቀት መጽሐፍን ቢያጠኑም ራሳቸውን ለመወሰንና ለመጠመቅ የሚያበቃ እድገት እንዳላደረጉ የምታውቋቸው ሰዎች ካሉ ጥናታቸውን መቀጠል ይፈልጉ እንደሆነ ቀዳሚ ሆናችሁ ለመጠየቅ ታስቡ ይሆናል።
7 ለምናስጠናው ለእያንዳንዱ ፍላጎት ያለው ሰው በግላችን የቅርብ ክትትልና ትኩረት መስጠታችን የክርስቲያናዊ ፍቅር መግለጫ ነው። ዓላማችን ተማሪው ስለ አምላክ ቃል እውነት የተሻለ ማስተዋል እንዲያገኝ መርዳት ነው። ይህ ከሆነ ተማሪው ለእውነት ቁርጠኛና በእውቀት ላይ የተመሠረተ አቋም በመውሰድ ራሱን ለአምላክ ሊወስንና ይህንን ውሳኔውን በውኃ ጥምቀት ሊያሳይ ይችላል።—መዝ. 40:8፤ ኤፌ. 3:17-19
8 ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ከተጠመቀ በኋላ የሆነውን ታስታውሳላችሁ? አዲስ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ሆኖ ‘ደስ ብሎት መንገዱን ሄዷል።’ (ሥራ 8:39, 40) እኛም ሆንን ወደ እውነት መንገድ የምንመራቸው ሰዎች ይሖዋ አምላክን አሁንም ሆነ ለዘላለም በማገልገል ታላቅ ደስታ ለማግኘት ያብቃን!