አጣዳፊ ለሆነው ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ የበለጠ ትኩረት መስጠት
1 ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት “አሕዛብን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት” እንዲያደርጉ ተከታዮቹን አዟቸው ነበር። ይህም የተጧጧፈ የስብከትና የማስተማር ዘመቻ ማካሄድንና እንቅስቃሴያቸውን ሰው ወደሚኖርበት የምድር ክፍል ሁሉ ማስፋትን ይጠይቅባቸው ነበር። (ማቴ. 28:19, 20፤ ሥራ 1:8) ይህን ተልዕኮ ሊወጡት እንደማይችሉት ከባድ ሸክም አድርገው ተመልክተውት ነበርን? ሐዋርያው ዮሐንስ እንደዚያ አድርገው እንዳልተመለከቱት ይነግረናል። ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ 65 ዓመት ካሳለፈ በኋላ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም።”—1 ዮሐ. 5:3
2 ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በጥድፊያ ስሜት እንዳከናወኑ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች እንቅስቃሴ ያረጋግጣል። (2 ጢሞ. 4:1, 2) ይህንን ያደረጉት እንዲያው ግድ ሆኖባቸው ሳይሆን አምላክን ለማወደስና ሌሎች የመዳን ተስፋ እንዲኖራቸው ለማድረግ ከነበራቸው ከፍቅር የመነጨ ፍላጎት የተነሳ ነው። (ሥራ 13:47-49) ደቀ መዛሙርት የሆኑት ሁሉ ከዚያ በኋላ እነርሱ ራሳቸው ደቀ መዝሙር አድራጊዎች በመሆናቸው በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የክርስቲያን ጉባኤ በፍጥነት ያድግ ነበር።—ሥራ 5:14፤ 6:7፤ 16:5
3 ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ በመፋጠን ላይ ነው፦ በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መጠን በመከናወን ላይ ይገኛል! እስከ አሁን ድረስ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ምሥራቹን ተቀብለው ተገቢውን እርምጃ ወስደዋል። (ሉቃስ 8:15) ይህ የነገሮች ሥርዓት የቀረው ጊዜ በፍጥነት እየተሟጠጠ ስለሆነ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች እውነትን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲማሩ ለማድረግ የሚያስችሉ መሣሪያዎችን አቅርቦልናል።—ማቴ. 24:45
4 በ1995 ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለ መጽሐፍ ያገኘን ሲሆን ከዚያም በ1996 አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለ ብሮሹር አግኝተናል። እውቀት የተባለውን መጽሐፍ በማስመልከት የጥር 15, 1996 መጠበቂያ ግንብ እትም ገጽ 14 ላይ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ይህ 192 ገጾች ያሉት መጽሐፍ አጠር ባለ ጊዜ ውስጥ ተጠንቶ ሊያልቅ ከመቻሉም በላይ ‘ለዘላለም ሕይወት ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች’ መጽሐፉን በማጥናት ራሳቸውን ለይሖዋ እንዲወስኑና እንዲጠመቁ የሚያስችላቸውን እውቀት ለማግኘት ይችላሉ።”—ሥራ 13:48 NW
5 “እውቀት በተባለው መጽሐፍ አማካኝነት ደቀ መዛሙርት ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?” በሚል ርዕስ የወጣው የሰኔ 1996 የመንግሥት አገልግሎታችን አባሪ የሚከተለውን ግብ እንድናወጣ ሐሳብ አቅርቦ ነበር:- “እንደ ተማሪው ሁኔታና ችሎታ በአንድ ሰዓት ወይም ከዚያ ብዙም በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ ሳትጣደፉ አንድ ምዕራፍ መጨረስ ትችሉ ይሆናል። አስተማሪውም ሆነ ተማሪው በየሳምንቱ የጥናት ፕሮግራማቸውን አክብረው ሲገኙ ተማሪዎች የተሻለ እድገት ያደርጋሉ።” በመቀጠልም ጽሑፉ እንዲህ ይላል:- “አንድ ሰው እውቀት በተባለው መጽሐፍ ጥናቱን ሲያጠናቅቅ አምላክን ለማገልገል የሚኖረው ልባዊ ፍላጎትና ጥልቅ ምኞት በግልጽ መታየቱ የሚጠበቅ ነገር ነው።” በጥቅምት 1996 የመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የወጣው የጥያቄ ሣጥን እንዲህ በማለት ያብራራል:- “አንድ ውጤታማ አስተማሪ መጠነኛ ችሎታ ያለውን በፍላጎት የሚያጠና ተማሪ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይሖዋን ለማገልገል የጥበብ ውሳኔ እንዲያደርግ የሚያስችለውን በቂ እውቀት ሊያስታጥቀው ይችላል ተብሎ ይታመናል።”
6 እውቀት የተባለው መጽሐፍ ውጤት እያስገኘ ነው፦ አንዲት ወጣት ሴት በተጠመቀችበት ጊዜ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ስለማጥናቷ የተሰማትን ስሜት ተናግራ ነበር። ለተወሰነ ጊዜ ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ አጥንታ ነበር። እውቀት የተባለው መጽሐፍ ሲወጣ ጥናቱን ትመራላት የነበረችው እህት አዲሱን መጽሐፍ እንድታጠና አደረገች። ተማሪዋም ይህ ጥናት በእርሷ በኩል አንድ ዓይነት ውሳኔ ማድረግ እንደሚጠበቅባት እንድትገነዘብ አደረጋት። በዚህም ምክንያት ፈጣን እድገት እንድታደርግ አነሳሳት። አሁን እህታችን የሆነችው ይህች ወጣት ሴት ስትናገር “ለዘላለም መኖር የተባለው መጽሐፍ ይሖዋን እንድወድ ረድቶኛል፤ እውቀት የተባለው መጽሐፍ ግን እርሱን ለማገልገል እንድወስን ረዳኝ” ትላለች።
7 አንዲት ሌላ ሴትም በአጭር ጊዜ ውስጥ እውነትን እንዴት እንደተማረች ተመልከቱ። ለሁለተኛ ጊዜ ካጠናች በኋላ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ በሚጎበኝበት ወቅት በመንግሥት አዳራሹ በሚደረገው ስብሰባ ላይ ተገኘች። በዚያው ሳምንት ለሦስተኛ ጊዜ ጥናቷን ባጠናችበት ወቅት ራሷን ለይሖዋ እንደወሰነችና ያልተጠመቀች አስፋፊ መሆን እንደምትፈልግ ነገረችው። ከሽማግሌዎች ጋር ከተነጋገረች በኋላ አስፋፊ ለመሆን ብቁ እንደሆነች ነገሯት። ከዚያም በቀጣዩ ሳምንት በመስክ አገልግሎት መካፈል ጀመረች። በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቷ በጣም በመደሰቷ የተነሳ በሳምንት ውስጥ ሁለት ወይም ሦስት ጊዜ ለማጥናትና በአገልግሎት ረዘም ያለ ጊዜ ለማሳለፍ ትችል ዘንድ የሥራ ፈቃድ ወሰደች። አንዳንድ ጊዜ በእያንዳንዱ የጥናት ክፍለ ጊዜ ሁለት ወይም ሦስት ምዕራፎችን ይሸፍኑ ነበር። የምትማራቸውን ነገሮች በሁሉም የኑሮዋ ዘርፎች በሥራ ላይ ማዋል ጀመረች፣ በአራት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ አጥንታ ጨረሰችና ተጠመቀች!
8 የአንዲት እህት ባል ቀድሞ ስለነበረበት ሁኔታ ሲገልጽ “ጨርሶ የማያምን ሰው” እንደነበረ ተናግሯል። አንድ ቀን አንድ ወንድም እውቀት በተባለው መጽሐፍ አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና ግብዣ አቀረበለት። ሆኖም የመጀመሪያውን ጥናት ካደረገ ወይም ከዚያ በኋላ በማንኛውም ጊዜ ጥናቱን ማቆም እንደሚችል ገለጸለት። ባልየው ልጅ በነበረበት ጊዜ ይሄን ያህል ጎበዝ ተማሪ ያልነበረና ከ20 ለሚበልጡ ዓመታት የትኛውንም ሃይማኖታዊ ጽሑፍ አንብቦ የማያውቅ ቢሆንም እንኳን እስቲ ልሞክረው በማለት ለማጥናት ተስማማ። እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ለማጥናት የነበረው ፍላጎት ምን ያህል ነበር? እንዲህ በማለት ይናገራል:- “መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚያግዝ በቀላሉ ሊገባ የሚችል እንዲህ ያለ መጽሐፍ ማግኘት በጣም የሚያስደስት ነው። ትምህርቱ በጣም ግልጽና አሳማኝ በሆነ መንገድ የተዘጋጀ በመሆኑ ብዙም ሳልቆይ ቀጥሎ የምናጠናበትን ጊዜ በከፍተኛ ጉጉት መጠባበቅ ጀመርኩኝ። አስተማሪዬ ማኅበሩ ያወጣውን ደቀ መዛሙርት ለማድረግ የሚያስችሉ ዘዴዎችን በጥንቃቄ ይከተል ነበር። እንዲሁም በይሖዋ መንፈስ እርዳታ ከአራት ወራት በኋላ ተጠመቅሁ። ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ ከልብ የምንወድ ከሆነ፣ በመስክ አገልግሎት ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች መፈለጋችንን ከቀጠልን፣ እውቀት የተባለውን መጽሐፍና ማኅበሩ የሚያቀርባቸውን ሌሎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ጽሑፎች በጥሩ መንገድ የምንጠቀምባቸው ከሆነና ከሁሉም በላይ ደግሞ የይሖዋን መመሪያ ለማግኘት የምንጸልይ ከሆነ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ከፍተኛ እርዳታ የማበርከት ልዩ አጋጣሚ ይኖረናል ብዬ በድፍረት መናገር እችላለሁ።” ከላይ የሰፈሩት ተሞክሮዎች ሁልጊዜ ሊያጋጥሙ የሚችሉ አይደሉም። አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን እንዲህ ባለ አጭር ጊዜ ውስጥ ወደ እውነት አይመጡም።
9 ተማሪዎች እድገት የሚያደርጉበት ፍጥነት ይለያያል፦ የአምላክ ቃል አስተማሪዎችም ሆኑ ተማሪዎች ያላቸው ችሎታ የአንዳቸው ከሌላው እንደሚለይ መታወቅ አለበት። መንፈሳዊ እድገት አዝጋሚ ወይም ፈጣን ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ተማሪዎች በጥቂት ወራት ውስጥ የሚደርሱበት የእድገት ደረጃ ለሌሎች ረዘም ያለ ጊዜ ሊያስቆጥርባቸው ይችላል። አንድ ሰው በመንፈሳዊ የሚያደርገው እድገት መጠን በትምህርት ደረጃው፣ ለመንፈሳዊ ነገሮች ባለው የአድናቆት መጠንና ለይሖዋ ባለው የጠለቀ ፍቅር በእጅጉ ይነካል። በጥንት ጊዜ አማኝ የሆኑት የቤርያ ሰዎች እንዳደረጉት ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ ለማጥናት ‘በሙሉ ፈቃድ የሚቀበሉት’ ሁሉም ጥናቶች አይደሉም።—ሥራ 17:11, 12
10 ለዚህም ነው በሚያዝያ 1998 የመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የወጣው “ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እንዲኖሩ ይፈለጋል” የሚለው አባሪ የሚከተለውን እውነታ ያሰፈረው። “እርግጥ ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እኩል እድገት አያደርጉም። አንዳንድ ሰዎች ለመንፈሳዊ ነገር እንደሌሎች ዝንባሌ አይኖራቸው ይሆናል አለዚያም የሚማሩትን ነገር በቶሎ አይረዱ ይሆናል። ሌሎች ሰዎች ደግሞ በሥራ የተወጠረ ሕይወት ስለሚመሩ በየሳምንቱ አንድ ሙሉ ምዕራፍ ለመጨረስ ጊዜ ላያገኙ ይችላሉ። ስለዚህ ባሉት አንዳንድ ሁኔታዎች አንዱን ምዕራፍ ለመሸፈን ከአንድ በላይ የጥናት ክፍለ ጊዜ መጠቀም እንዲሁም መጽሐፉን ለመጨረስ ተጨማሪ ወራት ያስፈልገን ይሆናል።”
11 ደቀ መዛሙርት አድራጊዎች ሚዛናዊ አመለካከት ይይዛሉ፦ የጥናቱን ፍጥነት እንደ ተማሪው ሁኔታና ችሎታ ማድረግ አስፈላጊ ነው። አምላክ ከእኛ የሚፈልገው በተባለው ብሮሹር ጥናት እንድናስጀምር ማበረታቻ ስለ ተሰጠን ብሮሹሩን ጨርሰን ወደ እውቀት መጽሐፍ ለመሸጋገር ከሁለት እስከ ሦስት ወራት ሊወስድ ይችላል። በሰኔ 1996 የመንግሥት አገልግሎታችን አባሪ ላይ የቀረቡትን ሐሳቦች በሙሉ ከተጠቀምንባቸው እውቀት የተባለውን መጽሐፍ አጥንቶ ለመጨረስ ተጨማሪ ከስድስት እስከ ዘጠኝ ወር ሊወስድ ይችላል። የእውቀት መጽሐፍን ገና ማጥናት የጀመረ ጥናት ያላቸው አንዳንዶች ተማሪው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሠፈሩትን መሠረታዊ እውነቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲገነዘብ ለመርዳት ሲሉ ጥናቱን አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ወደተባለው ብሮሹር እንዲዘዋወር አድርገዋል። ከዚያም ወደ እውቀት መጽሐፍ ተመልሰዋል። በእውቀት መጽሐፍ ጥናት ጀምሮ ብዙ የገፋ ጥናት ካለ ደግሞ መጽሐፉን አጥንቶ ከጨረሰ በኋላ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለውን ብሮሹር ማስጠናቱ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። በዚህ መንገድ መሠረታዊ የሆኑትን የአምላክ ቃል እውነቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ መከለስ ይቻላል። ከሁለቱ ዘዴዎች የትኛውንም እንጠቀም ተማሪው ጥናቱን በቶሎ እንዲጨርስ ለማድረግ ሲባል የሚደረገው ሩጫ ሊያገኝ የሚገባውን የተጣራ እውቀት እንዲያጨልምበት ማድረግ አይገባም። እያንዳንዱ ተማሪ ከአምላክ ቃል ውስጥ ያገኘው አዲስ እምነት በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነባ ሊሆን ይገባዋል።
12 በጊዜ ሂደት ውስጥ የት ቦታ ላይ እንዳለን ማወቃችን ሌሎች እውነትን እንዲማሩ መርዳት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ አሁን አጣዳፊ ነው። አዳዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ለማግኘት መጸለያችንን ከመቀጠላችንም ባሻገር ከእኛ ጋር እያጠኑ ስላሉትም እንጸልይ። እንዲህ በማድረግ “እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ” ተጨማሪ ደቀ መዛሙርት እንዲጠመቁ በማድረጉ ሥራ መካፈላችን ደስታ ይጨምርልናል።—ማቴ. 28:20