የጥያቄ ሣጥን
◼ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት በተባለው መጽሐፍ በምንጠቀምበት በአሁኑ ጊዜ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚመራው ለምን ያህል ጊዜ መሆን አለበት?
የመስከረም 1993 የመንግሥት አገልግሎታችን ከአዳዲስ ሰዎች ጋር የሚደረገው የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሁለት መጽሐፍ ተጠንቶ እስኪያልቅ ድረስ መቀጠል እንዳለበት ይናገራል። አሁን የምንጠቀመው እውቀት በተባለው መጽሐፍ ስለሆነ በጥር 15, 1996 መጠበቂያ ግንብ እትም ገጽ 13 እና 14 ላይ እንደተገለጸው በዚህ አሠራር ላይ ማስተካከያ ማድረጉ ጥሩ ነው።
እውቀት የተባለው መጽሐፍ የተዘጋጀው “ለዘላለም ሕይወት ትክክለኛ ዝንባሌ ያላቸው” ሰዎች ራሳቸውን ለይሖዋ ለመወሰንና ለመጠመቅ የሚያስፈልጋቸውን እውቀት እንዲያገኙ ለመርዳት ታስቦ ነው። (ሥራ 13:48) ስለዚህ ይህን አዲስ መጽሐፍ ከጨረሱ በኋላ ያንኑ ተማሪ ሁለተኛ መጽሐፍ ማስጠናት አያስፈልግም። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችህ እውነት እየገባቸው ሲሄድ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ በመገኘት እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስንና የተለያዩ ክርስቲያናዊ ጽሑፎችን በማንበብ እውቀታቸውን እንዲያጠናክሩ ደረጃ በደረጃ ልታበረታታቸው ትችላለህ።
አገልግሎታችንን ለመፈጸም መደራጀት በተባለው መጽሐፍ ከገጽ 175 እስከ 218 ላይ ያሉትን ጥያቄዎች ጥሩ አድርገህ ብታውቃቸው ይጠቅምሃል። ምንም እንኳ እነዚህን ጥያቄዎች መጥቀስ ወይም ጥያቄዎቹን ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪው ጋር መከለስ ባያስፈልግህም ሽማግሌዎች ከእጩ ተጠማቂዎች ጋር ሆነው ጥያቄዎቹን ሲከልሱ ተማሪው መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን በተገቢ ሁኔታ እንደተረዳ በሚያሳይ መንገድ ሐሳቡን ለመግለጽ የሚረዱትን በእውቀት መጽሐፍ ላይ የሚገኙ ነጥቦች ጠበቅ አድርጎ መግለጹ ጥሩ ነው።
በእውቀት መጽሐፍ ውስጥ ያለውን ትምህርት ማስፋት፣ ከውጪ ሌላ ሐሳብ ማምጣት ወይም ለመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ድጋፍ ለመስጠትም ሆነ የሐሰት ትምህርቶችን ለማፍረስ ተጨማሪ ማሳመኛ ነጥቦችን ማከል አያስፈልግም። እንዲህ ማድረጉ ጥናቱን ከማራዘም በስተቀር ፋይዳ የለውም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፉ በፍጥነት፣ ምናልባትም በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ሊያልቅ ይችላል ተብሎ ተስፋ ይደረጋል። ይህም ትምህርቱን ግልጽና እጥር ምጥን ባለ መንገድ ለማቅረብ እንድንችል በቅድሚያ ጠለቅ ያለ ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልገን ያጎላል። ተማሪዎቹም ቢሆኑ ቀደም ብለው እንዲዘጋጁ፣ ምዕራፋቸውና ቁጥራቸው ብቻ የተጠቀሱ ጥቅሶችን አውጥተው እንዲመለከቱና መጽሐፉ በእያንዳንዱ ምዕራፍ ላይ ለማስተማር የፈለገውን እንዲያስተውሉ መበረታታት ይኖርባቸዋል።
የይሖዋ ምሥክሮች ብዙ ቁጥር ያላቸው ውጤታማ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በአጭር ጊዜ ማስጠናት ያስፈለጋቸው ለምን እንደሆነ መጠበቂያ ግንብ ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። (ኢሳይያስ 60:22ን ተመልከት።) እውቀት በተባለው መጽሐፍ ውጤታማ በሆነ መንገድ ከተጠቀምን አዳዲሶች ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራውን እውቀት ለማግኘትና ከዚህ እውቀት ጋር ተስማምተው ለመኖር ያስችላቸዋል።— ዮሐ. 17:3