እናንት የቤተሰብ ራሶች —ቤተሰባችሁ ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ እንዲያዳብር እርዱት
1 ዳንኤል የጣዖት አምልኮና ምግባረ ብልሹነት በተስፋፋበት በባቢሎን ለብዙ አሥርተ ዓመታት ቢኖርም ይሖዋን “ሁልጊዜ” በማገልገሉ የታወቀ ነበር። (ዳን. 6:16, 20) ዳንኤል መንፈሳዊነቱን ሊጠብቅ የቻለው እንዴት ነው? የመጽሐፍ ቅዱሱ ዘገባ እንደሚያሳየው ዳንኤል ከእውነተኛው አምልኮ ጋር የተያያዙ ነገሮችን የሚያከናውንበት ቋሚ ጊዜ ነበረው። ለምሳሌ ያህል፣ በቤቱ ጣሪያ ላይ ሆኖ በቀን ሦስት ጊዜ የመጸለይ ልማድ ነበረው። (ዳን. 6:10) በተጨማሪም ሕጉን ማንበብን ለመሳሰሉ ሌሎች መንፈሳዊ ጉዳዮችም ጊዜ መድቦ እንደሚሆን ምንም አያጠራጥርም። በዚህም የተነሳ ሕይወቱን አደጋ ላይ የሚጥል ፈተና በገጠመው ጊዜ በይሖዋ ላይ ከነበረው እምነት ፈጽሞ አላወላወለም። እንዲህ በማድረጉም ተአምራዊ ጥበቃ አግኝቷል።—ዳን. 6:4-22
2 እኛም በተመሳሳይ ‘በመጽናት ሁሉ መትጋት’ ይኖርብናል። (ኤፌ. 6:18) የምንኖርበት ዓለም ‘በክፉው ተይዟል።’ (1 ዮሐ. 5:19) ተቃውሞ ወይም ስደት ድንገት ሊነሳና እምነታችን ሊፈተን ይችላል። ታላቁ መከራ ሲጀምር የማጎጉ ጎግ በአምላክ አገልጋዮች ላይ ይህ ነው የማይባል ጥቃት ይሰነዝራል። በዚህ ወቅት ችግሩ ሳይነካን ማምለጥ አንችልም። ስለሆነም ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ላይ መታመን ይኖርብናል።—ሕዝ. 38:14-16
3 በይሖዋ ላይ ለመታመን የሚረዳው “አንዱ ወሳኝ ቁልፍ ውጤታማ የሆነን የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፣ ጥናትና ውይይት የሕይወት መንገድ ማድረግ ነው።” ይህ በ1998 ተደርጎ በነበረው የአውራጃ ስብሰባ ላይ “ቤተሰቦች—በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ የሕይወታችሁ መንገድ ይሁን!” በሚል ርዕስ የቀረበው ድራማ የመግቢያ ሐሳብ ነበር። በመቀጠልም የሚከተለውን ብሎ ነበር:- “ቤተሰቦች መጽሐፍ ቅዱስን ሕያው በሆነ መንገድ ማጥናት የሚቻልበትን ዘዴ በመቀየስ እንዲህ ዓይነቱን ፕሮግራም በቋሚነት የሚከተሉ ከሆነ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ልማድ በቤተሰቡ ላይ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። እውቀታችንን ይገነባልናል። እምነታችንን ያጠነክርልናል። በተጨማሪም መንፈሳችንን ሊያነሳሱና እውነትን አጥብቀን እንድንይዝ ሊገፋፉን የሚችሉ ጥሩ አርአያዎችን ማለትም አስደናቂ ታማኝነት ያሳዩ የጥንት ወንዶችና ሴቶችን ታሪክ ይገልጽልናል።” ከዚህ ቀጥሎ ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ማዳበር የሚቻልባቸውን መንገዶች ስንመረምር የቤተሰብ ራሶች የቤተሰባቸውን መንፈሳዊ ልማድ ማሻሻል የሚችሉባቸውን አንዳንድ ነጥቦች ልብ ማለት ይኖርባቸዋል።
4 የአምላክን ቃል በየቀኑ አንብቡ:- “የአምላክ መንግሥት ያለ አንዳች ተቀናቃኝ በሚያስተዳድርበትና ፈቃዱ በሰማይ እንደሆነ ሁሉ በምድርም በሚሆንበት ጊዜ ጨካኝ ሰዎች አይኖሩም፤ ሌላው ቀርቶ እንስሳት እንኳ ‘አይጎዱም አያጠፉምም።’ (ኢሳ. 11:9፤ ማቴ. 6:9, 10)” እነዚህ ቃላት ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ መመርመር—2001 በተባለው ቡክሌት ላይ ለመስከረም 11 በተሰጠው ሐሳብ ውስጥ የሰፈሩ ናቸው። ይህ ማሳሰቢያ ምንኛ አጽናኝ ነበር! የቤተሰብ ራስ ከሆንክ ከቤተሰብህ ጋር የዕለቱን ጥቅስና ሐሳቡን በየዕለቱ የመመርመር ልማድ አለህ? ይህ በጣም ጠቃሚ ነው። በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ አንድ ላይ መሰባሰብ ካልቻላችሁ አመሻሹ ላይ እንዲህ ማድረግ ትችሉ ይሆናል። አንድ አባት “ማታ በእራት ሰዓት በዕለቱ ጥቅስ ላይ መወያየት ጥሩ ሆኖ አግኝተነዋል” በማለት ተናግሯል።
5 የዕለቱን ጥቅስ በቤተሰብ መልክ የመመርመር ልማድ አዳብራችሁ ከሆነ ልትመሰገኑ ይገባችኋል። ምናልባትም በዚሁ ጊዜ ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን በማንበብ ይበልጥ መጠቀም ትችሉ ይሆናል። አንዳንዶች የዕለቱ ጥቅስ የሚገኝበትን ሙሉ ምዕራፍ የማንበብ ልማድ አዳብረዋል። ሌሎች ደግሞ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ይመርጡና ምዕራፎቹን እስኪጨርሱ ድረስ በየዕለቱ ያነብባሉ። መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብ ቤተሰቦችህ ይሖዋን ላለማሳዘን ጤናማ ፍርሃት እንዲያዳብሩና ፈቃዱን የማድረግ ፍላጎታቸው ከፍ እንዲል ይረዳቸዋል።—ዘዳ. 17:18-20
6 መጽሐፍ ቅዱስ ስታነብቡና በዕለት ጥቅሱ ላይ ውይይት ስታደርጉ ያገኛችኋቸውን ነጥቦች እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደምትችሉ ጥቂት ደቂቃ ወስዳችሁ ብትወያዩ ከፍተኛ ጥቅም ታገኛላችሁ። የአገልግሎት ትምህርት ቤት መጽሐፍ ገጽ 60 የሚከተለውን ሐሳብ ይሰጣል:- “ከሳምንቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም ጥቂት ጥቅሶችን መርጠህ ትርጉማቸውን ካብራራህ በኋላ እንደሚከተለው ያሉ ጥያቄዎችን ልታነሣ ትችላለህ:- ‘ይህ ጥቅስ መመሪያ የሚሆነን እንዴት ነው? እነዚህን ጥቅሶች በአገልግሎት ልንጠቀምባቸው የምንችለው እንዴት ነው? ይህስ ለእርሱ ያለንን አድናቆት የሚጨምርልን እንዴት ነው?’” እንዲህ ዓይነቱ መንፈሳዊ ውይይት መላው ቤተሰብ ‘የጌታ ፈቃድ ምን እንደሆነ እንዲያስተውል’ ይረዳዋል።—ኤፌ. 5:17
7 የቤተሰብ ጥናት:- የቤተሰብ ራሶች የቤተሰብ ጥናቱን ሳያቋርጡ በመምራት ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚገባ ለልጆቻቸው ማሳየት ይችላሉ። አንድ ወጣት እንደሚከተለው ሲል ያስታውሳል:- “አንዳንድ ጊዜ አባቴ ከሥራ በጣም ደክሞት ስለሚመጣ በንቃት መሳተፍ ያቅተዋል። ያም ቢሆን ጥናቱ ፈጽሞ አይቋረጥም። ይህም የቤተሰብ ጥናትን አስፈላጊነት እንድንገነዘብ ረድቶናል።” ልጆችም ቢሆኑ ለዝግጅቱ መሳካት የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላሉ። ዘጠኝ ልጆች ያሉት አንድ ቤተሰብ ሌላ አመቺ ሰዓት ባለማግኘቱ የቤተሰብ ጥናት ለማድረግ ጠዋት በ11 ሰዓት ይነሳል።
8 የቤተሰቡ ራስ የቤተሰብ ጥናቱን ውጤታማ ለማድረግ ‘ለትምህርቱ የማያቋርጥ ትኩረት’ መስጠት አለበት። (1 ጢሞ. 4:16 NW ) የአገልግሎት ትምህርት ቤት መጽሐፍ ገጽ 32 ላይ እንዲህ ይላል:- “ውጤታማ የቤተሰብ ጥናት የሚጀምረው የቤተሰብህን ሁኔታ በማጥናት ነው ሊባል ይችላል። የቤተሰብህ አባላት መንፈሳዊ እድገት ምን ይመስላል? . . . ከልጆችህ ጋር በአገልግሎት ስትካፈል ምን አስተውለሃል? በእኩዮቻቸው ፊት የይሖዋ ምሥክሮች ሆነው በመታወቃቸው አይሸማቀቁም? በቤተሰብ መልክ መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብና ለማጥናት ባወጣችሁት ፕሮግራም ደስ ብሏቸው ይካፈላሉ? በእርግጥ በይሖዋ መንገድ እየተመላለሱ ነውን? እነዚህን ነገሮች ልብ ብለህ መከታተልህ የቤተሰብ ራስ እንደመሆንህ መጠን በእያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ውስጥ መንፈሳዊ ባሕርያትን ለመገንባት ምን እንደሚያስፈልግ ለመገንዘብ ይረዳሃል።”
9 የጉባኤ ስብሰባዎች:- ለስብሰባዎች መዘጋጀትና በስብሰባዎቹ ላይ መገኘት በሳምንቱ ውስጥ በምታከናውኗቸው እንቅስቃሴዎች መካከል መመደብ ይኖርባቸዋል። (ዕብ. 10:24, 25) አልፎ አልፎ በቤተሰብ መልክ ለስብሰባ መዘጋጀት ትችሉ ይሆናል። እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ ከመቆየት ይልቅ አስቀድማችሁ መዘጋጀት ትችሉ ይሆን? በዚህ ረገድ የተደራጃችሁ መሆናችሁ የዝግጅታችሁን ጥራትና ከስብሰባዎች የምታገኙትን ጥቅም ይጨምርላችኋል።—ምሳሌ 21:5
10 ከአንድ መንፈሳዊ ልማድ ጥሩ ውጤት ለማግኘት ጥራት ያለውና የሚዘወተር መሆን አለበት። ለሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች ለመዘጋጀት ሁኔታህ ባይፈቅድልህስ? የአገልግሎት ትምህርት ቤት መጽሐፍ ገጽ 31 የሚከተለውን ሐሳብ ይሰጣል:- “እንዲሁ ተዘጋጅቻለሁ ለማለት ያህል ብቻ በጥድፊያ ትምህርቱን ለመሸፈን አትሞክር። ሁሉንም ተዘጋጅቼ ልጨርሰው አልችልም በሚል አንዱንም ሳይጀምሩ መቅረት ደግሞ ከዚህ የከፋ ነው። ከዚህ ይልቅ ምን ያህሉን ልታጠና እንደምትችል ወስንና ያንኑ ጥሩ አድርገህ ተዘጋጅ። በየሳምንቱ እንደዚያ አድርግ። ቀስ በቀስ ሌሎች ስብሰባዎችንም በዝግጅትህ ለማካተት ጥረት አድርግ።”
11 ቤተሰቦች ቀደም ብለው በስብሰባ ላይ መገኘታቸው ይሖዋን ለማወደስ የሚያስችል ትክክለኛ የአእምሮ ዝንባሌ እንዲይዙና እርሱ ከሚሰጠው መመሪያ ጥቅም እንዲያገኙ ይረዳቸዋል። ቤተሰብህ እንዲህ የማድረግ ልማድ አለው? ይህ ጥሩ እቅድ ማውጣትንና የእያንዳንዱን የቤተሰብ አባል ትብብር ይጠይቃል። ቤተሰብህ ስብሰባ በሚደረግበት ሰዓት የሚጣደፍና ውጥረት የሚበዛበት ከሆነ በሳምንታዊ እንቅስቃሴዎቻችሁ ላይ ጥቂት ማስተካከያዎችን ማድረግ ትችሉ ይሆን? ቀደም ብለው ሊሠሩ የሚችሉ ነገሮች ይኖሩ ይሆን? የሥራ ጫና ያለበትን አንድ የቤተሰብ አባል ሌሎች መርዳት ይችሉ ይሆን? ሁሉም የቤተሰብ አባል ስብሰባው ከመጀመሩ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ለመውጣት ቢዘጋጅ ውጥረቱን ይቀንስ ይሆን? በጥሩ ሁኔታ መደራጀት በጉባኤውም ሆነ በቤተሰቡ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋል።—1 ቆሮ. 14:33, 40
12 የመስክ አገልግሎት:- በአገልግሎት ለመሳተፍ የሚያስችል ጊዜ መመደብም የጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ሌላው ክፍል ነው። ጄሰን የተባለ አንድ ወጣት እንደሚከተለው በማለት ያስታውሳል:- “ሁልጊዜ ቅዳሜ ጠዋት የቤተሰባችን ፕሮግራም አገልግሎት ነበር። ይህ እኔን በጣም ጠቅሞኛል። ምክንያቱም በአገልግሎት ይበልጥ በተካፈልኩ መጠን አገልግሎቱ የሚያስገኛቸውን መልካም ነገሮች ይበልጥ እየተመለከትኩና ይበልጥ ደስታ እያገኘሁበት መጣሁ።” ምሥክር በሆኑ ቤተሰቦች ውስጥ ያደጉ ሌሎች በርካታ ወጣቶችም በሳምንቱ ውስጥ ለአገልግሎት የሚሆን ቋሚ ጊዜ መመደቡ በክርስቲያን አገልጋይነታቸው እድገት እንዲያደርጉ እንደረዳቸው ተገንዝበዋል።
13 በተጨማሪም ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ቤተሰብህ በመስክ አገልግሎት የሚያሳልፈውን ጊዜ ይበልጥ አስደሳችና ውጤታማ እንዲሆን ይረዳዋል። እንዲህ ዓይነቱን ውጤት ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው? የሐምሌ 1, 1999 መጠበቂያ ግንብ በገጽ 21 ላይ የሚከተለውን ሐሳብ ሰጥቶ ነበር:- “የቤተሰብህን አባላት በሳምንቱ ውስጥ ለሚደረጉት የመስክ አገልግሎት ስብሰባዎች ዝግጁ ለማድረግ ከቤተሰብ ጥናታችሁ ላይ አልፎ አልፎ የተወሰነ ጊዜ ትመድባለህ? እንዲህ ማድረጉ በጣም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። (2 ጢሞ. 2:15) አገልግሎታቸው ትርጉም ያለውና ውጤታማ እንዲሆን ሊረዳቸው ይችላል። አልፎ አልፎ መላውን የጥናት ክፍለ ጊዜ የዚህ ዓይነቱን ዝግጅት ለማድረግ ልታውሉት ትችሉ ይሆናል። የቤተሰብ ጥናታችሁን ስትጨርሱ ወይም በሳምንቱ መካከል ባለ በአንዱ ቀን ላይ የመስክ አገልግሎትን የተለያዩ ዘርፎች የሚመለከቱ ውይይቶችን ልታደርጉ ትችላላችሁ።” ቤተሰብህ ይህንን ሞክሯል?
14 እድገት ማድረጋችሁን ቀጥሉ:- ከላይ ያለውን አባባል ግምት ውስጥ በማስገባት ቤተሰብህ እየሠራበት ያለውን አቅጣጫ ማስተዋል ችለሃል? አስተውለህ ከሆነ አመስግናቸው። እንዲሁም ማሻሻያ ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ አበረታታቸው። መሻሻል የሚያስፈልጋቸው በርካታ ዘርፎች ካሉ በመጀመሪያ አንዱን ወይም ሁለቱን እንዲያሻሽሉ ለመርዳት ጥረት አድርግ። እነዚህ የመንፈሳዊ ልማዳችሁ ክፍል ሲሆኑላችሁ በሌላ በአንድ ወይም በሁለት ነጥቦች ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ጥረት አድርጉ። አዎንታዊ አመለካከት ያለህና ምክንያታዊ ሁን። (ፊልጵ. 4:4, 5 NW ) ቤተሰብህ ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ እንዲያዳብር መርዳት ጥረት ይጠይቃል። ይሁን እንጂ ከሚያስገኘው ጥቅም አንጻር ቢደከምለት አይቆጭም። ይሖዋ “እኔን የሚታዘዙትን ሁሉ አድናቸዋለሁ” በማለት ቃል ገብቷል።—መዝ. 50:23፣ የ1980 ትርጉም