በሥርዓታማ ልማድ እያደጋችሁ መሄዳችሁን ቀጥሉ
1 ለፊልጵስዩስ ጉባኤ መመሥረት በመሣሪያነት ያገለገለው ሐዋርያው ጳውሎስ ለዚህ ጉባኤ የጠበቀ የመውደድ ስሜት ነበረው። በደግነት ላደረጉለት ሥጋዊ ስጦታ አመስጋኝ ነበር። በጥሩ ምሳሌነታቸው ጠቅሷቸዋል። — 2 ቆሮ. 8:1–6
2 ጳውሎስ የነበረው ጥልቅ ፍቅር ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ደብዳቤ እንዲጽፍ ገፋፍቶታል። ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለው መጽሐፍ በጥራዝ 2 ገጽ 631 ላይ እንዲህ በማለት ይዘግባል:- “በጠቅላላው መልእክቱ ውስጥ የፊልጵስዩስ ጉባኤ የበለጠ ማስተዋልን ለማግኘት በመጣጣር፣ የሕይወትን ቃል፣ ጠንካራ እምነትን እንዲሁም ስለመጪው ሽልማታቸው የተሰጣቸውን ተስፋ አጥብቀው በመያዝ መልካም ሥራቸውን እንዲቀጥሉበት አበረታቷቸዋል።” የሰጡት ምላሽ ሞቅ ያለና በእነርሱና በሐዋርያው መካከል ጠንካራ የፍቅር መሳሳብ የሚፈጥር ነበር። እነዚህ የጳውሎስ ቃላት ዛሬ ለእኛ ልዩ ትርጉም አላቸው። በተለይ በፊልጵስዩስ 3:15–17 ላይ የሰጠውን ምክር በጥንቃቄ እንድናስብበት የሚያደርግ ጥሩ ምክንያት ይሰጡናል።
3 የበሰለ አስተሳሰብ በጣም አስፈላጊ ነው፦ በፊልጵስዩስ 3:15 ላይ ጳውሎስ የብዙ ዓመታት ተሞክሮ ያለው ክርስቲያን ሆኖ ጽፎላቸዋል። ስለ ፊልጵስዩስ ሰዎች መንፈሳዊ እድገት ከገለጸ በኋላ ትክከለኛ አስተሳሰብ ያላቸው የጎለመሱ ክርስቲያኖች ሆነው እንዲገኙ አሳስቧቸዋል። ኢየሱስ ያሳየውን ዓይነት ትሕትናና አመስጋኝነት የሚያንጸባርቅ አስተሳሰብ እስካላቸው ድረስ ‘ያለነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች . . የሕይወትንም ቃል አጥብቀው የሚይዙ’ ሆነው ሊቀጥሉ ይችሉ ነበር። (ፊል. 2:14, 15) የጳውሎስን ቃላት ስናነብ ከእኛ ጋር እየተነጋገረ እንዳለ ሆኖ ሊሰማን ይገባል። እንዲህ ከሆነ ኢየሱስ የነበረውን ዓይነት አስተሳሰብ ለመያዝና በትሕትና ላገኘናቸው መብቶች አመስጋኝ የመሆንን ባሕርይ ለማሳየት ከልባችን እንመኛለን። በዚህና በሌሎች ጉዳዮች ረገድ ይሖዋ እንዲረዳን ወደ እርሱ ሳናቋርጥ በጸሎት እንቀርባለን። — ፊል. 4:6, 7
4 ፊልጵስዩስ 3:16 እንደሚጠቁመው ሁላችንም እድገት ለማድረግ መጣጣር ይገባናል። “እድገት” የሚለው ቃል “ወደፊት መግፋት፣ ማሻሻል” ማለት ነው። ለማደግ የሚፈልጉ ሰዎች “ስለ አዳዲስ ሐሳቦች፣ ግኝቶች ወይም አጋጣሚዎች ለማወቅ ይፈልጋሉ።” ጳውሎስ ክርስትና ባለበት ቆሞ የሚቀር እንዳልሆነና የሚከተሉትም ወደፊት መግፋታቸውን መቀጠል እንዳለባቸው የፊልጵስዩስ ሰዎች እንዲረዱ ፈልጎ ነበር። እድገት የማድረግ መንፈስ እንዳላቸው ሊታይ ይችል የነበረው ራሳቸውን ለመመርመር ፈቃደኛ በመሆናቸው፣ ደካማ ጎናቸውን አምነው በመቀበላቸውና የበለጠ ነገር ለመሥራት ወይም የሥራቸውን ጥራት ለማሻሻል አጋጣሚዎችን ለማግኘት በመጣጣራቸው ነበር። ዛሬ የይሖዋ ምድራዊ ድርጅት የእንቅስቃሴ መስኩንና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለውን እውቀት በማስፋት ማደጉን ቀጥሏል። ከዝግጅቶቹ በሙሉ ተጠቃሚዎች በመሆንና በሥራውም ሙሉ በሙሉ በመካፈል እያንዳንዳችን ከድርጅቱ ጋር እኩል መራመድ ይገባናል።
5 እድገት ለማድረግ ሥርዓታማ ልማድ ያስፈልጋል፦ ቀጥሎም ጳውሎስ ወንድሞቹ ‘በደረሱበት የእድገት ደረጃ በዚያው ልማድ በሥርዓት መመላለሳቸውን እንዲቀጥሉ’ አጥብቆ አሳስቧል። (ፊል. 3:16 አዓት) በሥርዓት መመላለስ እርስ በእርስ ባለን ግንኙነት ለሰዎችና ለሌሎች ነገሮች ተገቢውን ቦታ መስጠትን እንዲሁም የታረመ ጠባይ ማሳየትን ይጠይቅብናል። በፊልጵስዩስ የነበሩ ክርስቲያኖች ከይሖዋ ድርጅት ጋርና እርስ በእርሳቸው ተቀራርበው በመኖር ተገቢ ቦታቸውን ጠብቀዋል። ሕይወታቸው የሚመራው በፍቅር ሕግ ነበር። (ዮሐ. 15:17፤ ፊል. 2:1, 2) ጳውሎስ ‘ለወንጌሉ እንደሚገባ እንዲኖሩ’ አሳስቧቸዋል። (ፊል. 1:27) የሥርዓታማነትና የመልካም ጠባይ አስፈላጊነቱ ዛሬ ላሉት ክርስቲያኖችም ቢሆን አልቀነሰም።
6 ልማድ ማለት ዘወትር የሚደረግ ነገር ማለት ነው። እንግዲያውስ ነገሮችን በተለምዶ ከማከናወን ጋር በቅርብ የተያያዘ ነው። ልማድ እንዲኖረን ማድረጋችን ይጠቅመናል ምክንያቱም በልማድ ግፊት የምንከተለው አስቀድሞ የተቀረጸ ቋሚ ንድፍ ስላለን የሚቀጥለው እርምጃችን ምን መሆን እንዳለበት ለመወሰን ቆም ማለትና ማሰላሰል አያስፈልገንም።
7 ሥርዓታማ ቲኦክራሲያዊ ልማድ ራሳችንን በመንፈሳዊ ማነጽን፣ ሌሎችን መርዳትንና ከተቻለም በይሖዋ አገልግሎት የበለጠ ሥራ ማከናወንን ግብ በማድረግ ነጋ ጠባ የሚደረጉና የተለምዱ እንቅስቃሴዎችን ያካተተ ነው። እነዚህን ግቦች በተሳካ መንገድ ከዳር ማድረስ የግል ጥናት ለማድረግ፣ ዘወትር በስብሰባ ለመገኘትና በስብከቱ ሥራ ለመሳተፍ ዝግጅት አድርጎ በዚያ የመሥራትን ልማድ ይጠይቃል።
8 በሥርዓታማ ልማድ ውስጥ የሚካተቱ ዋና ዋና ነገሮች፦ አንዱ በጣም አስፈላጊ ነገር “ትክክለኛ እውቀትና የተሟላ ማስተዋል” ነው። (ፊል. 1:9 አዓት) የግል ጥናት እምነታችን ጥልቀት እንዲኖረው፣ ለእውነት ያለን አድናቆት እንዲጠነክርና ለመልካም ሥራ እንድንነቃቃ ያደርገናል። ይሁን እንጂ አንዳንዶች በጥናት ልማዳቸው ረገድ ጥብቅ መሆን ተስኗቸዋል። ከሚሰጡት ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ጊዜ ማጣት ነው።
9 መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ ከማንበብ የሚገኘው ጥቅም ተደጋግሞ ቢጠቀስም በዛ ሊባል አይቻልም። የሚሰጠው ትምህርት በማንኛውም መስክ “ይጠቅማል”። (2 ጢሞ. 3:16, 17) በተለመዱት ዕለታዊ እንቅስቃሴዎቻችን መሐል መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ጊዜ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? አንዳንዶች ገና አእምሮአቸው ሳይደክም ጠዋት ጥቂት ደቂቃዎች ቀደም ብሎ መነሣት የሚቻል ሆኖ አግኝተውታል። ሌሎች ደግሞ ማታ ከመተኛታቸው ጥቂት ደቂቃዎች ቀደም ብለው ማንበቡን የተሻለ ሆኖ አግኝተውታል። እቤት የሚውሉ ሚስቶች በቀኑ መካከል ምናልባትም ከሰዓት በኋላ ሌሎቹ የቤተሰቡ አባላት ከሥራ ወይም ከትምህርት ቤት ከመምጣታቸው በፊት ትንሽ ጊዜ ሊመድቡ ይችላሉ። አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስን ዘወትር ከማንበብ በተጨማሪ አዋጅ ነጋሪዎች የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ማንበብን የሳምንታዊ የጥናት ልማዳቸው ክፍል አድርገውታል።
10 የመሠረትናቸው አዳዲስ ልማዶች ከቀድሞዎቹ ልማዶቻችን ጋር መጋጨታቸው አይቀርም። ቀደም ሲል ምናልባት ያን ያህልም ጠቃሚ ያልሆኑ ሥራዎች የሚኖረንን ትርፍ ጊዜ እንዲይዙት የመፍቀድ ዝንባሌ ኖሮን ይሆናል። ከዚህ ዓይነቱ ልማድ መላቀቅ ቀላል አይደለም። የጥናት ልማዳችን እንዴት መሆን እንዳለበት የሚወስንልን የለም ወይም ደግሞ በዚህ ረገድ ስለምናደርገው ነገር ስሌት እንድናቀርብ አንጠየቅም። የጥናት ልማዳችን ቀጣይነት በእጅጉ የተመካው ‘ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑት ነገሮች’ ባለን አድናቆትና ከእነርሱ ለመጠቀም ስንል ‘ጊዜውን ለመዋጀት’ ባለን ፈቃደኝነት ላይ ነው። — ፊል. 1:10፤ ኤፌ. 5:16
11 ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አስፈላጊውን ትምህርትና ማበረታቻ በመስጠት በመንፈሳዊ እድገታችን ላይ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ። እንግዲያውስ በስብሰባዎች ላይ መገኘት ሌላው የሥርዓታማ ልማዳችን ዓቢይ ክፍል ነው። ጳውሎስ የዚህን አስፈላጊነት ጠንከር አድርጎ ገልጾታል። ይህ ለእኛው ምርጫ የተተወ ነገር አይደለም። — ዕብ. 10:24, 25
12 በሳምንቱ ውስጥ የምናከናውናቸውን ሥራዎች ፕሮግራም ስንነድፍ ሥርዓታማነትን ልናሳይ የምንችለው እንዴት ነው? አንዳንዶች የግል ጉዳያቸውን ለማስፈጸም የተወሰነ ጊዜ ይመድቡና የቀረቻቸውን ክፍት ጊዜ አጣብበው በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ይሞክራሉ። ይሁን እንጂ ነገሩ የተገላቢጦሽ መሆን ነበረበት። ሳምንታዊ ስብሰባዎቻችን አንደኛ ቦታ ሊሰጣቸው ይገባል ከዚያ በኋላ የቀሩት ሥራዎቻችን ይከተላሉ።
13 ዘወትር በስብሰባዎች ላይ መገኘት ጥሩ እቅድ ማውጣትንና የመላውን ቤተሰብ ትብብር ይጠይቃል። በሳምንቱ የሥራ ቀኖች አብዛኞቻችን የተደራረቡ የሥራ ፕሮግራሞች ስለሚኖሩን ጊዜያችን የተጣበበ ይሆናል። ይህም ማለት ቤተሰቡ ለመመገብና ለመዘገጃጀት ከዚያም ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት ለመድረስ የሚያስችለው በቂ ጊዜ እንዲኖር የእራት ሰዓቱን ቀደም ማድረግ ይገባል ማለት ነው። ይህ ተግባራዊ እንዲሆን የቤተሰቡ አባላት በየፊናቸው ሊተባበሩ ይችላሉ።
14 በሥርዓታማ ልማድ እያደግን መሄዳችንን እንድንቀጥል ከተፈለገ ዘወትር በመስክ አገልግሎት መሳተፋችን የግድ አስፈላጊ ነው። ሁላችንም የመንግሥቱን መልእክት ለመስበክ ያለብንን ከባድ ኃላፊነት በግልጽ እንረዳለን። የይሖዋ ምሥክሮች የሚያሰኘንም ይኸው ነው። (ኢሳ. 43:10) ዛሬ ከሚሠሩት ሥራዎች ሁሉ በጣም አስቸኳይና ጠቃሚ የሆነው ሥራ ይህ በመሆኑ ከሌሎቹ የዘወትር እንቅስቃሴዎቻችን አሳንሰን የምንመለከትበት ምንም ምክንያት አይኖርም። ጳውሎስ እንዲህ ሲል አሳስቦናል:- “እንግዲህ ዘወትር ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት፣ ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ፣ በእርሱ እናቅርብለት።” — ዕብ. 13:15
15 በሳምንቱ ውስጥ ለምናከናውናቸው ሥራዎች ፕሮግራም ስናወጣ ለመስክ አገልግሎትም የተወሰነ ጊዜ መመደብ ይኖርብናል። ጉባኤው በሳምንቱ ውስጥ የአገልግሎት ስብሰባ የሚደረግባቸው ቀናት እንደሚያዘጋጅ የታወቀ ነው። ከዚህ በኋላ የሚቀረው ነገር በየትኛው ቀን ስብሰባ ላይ ለመገኘት እንደምንችል የምናደርገው ውሳኔ ብቻ ይሆናል። በእያንዳንዱ የአገልግሎት ዘርፍ ይኸውም በመጽሔቶችና በሌሎች ጽሑፎች በመጠቀም ከቤት ወደ ቤት በመሄድ፣ ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ እንዲሁም የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በመምራት ለመካፈል መጣጣራችን ጥሩ ይሆናል። ጽሑፎችን ይዘን በመሄድና ውይይት ለመጀመር የሚያስችሉትን አጋጣሚዎች ለመጠቀም ንቁ በመሆን መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ለመስጠትም አስቀድመን ልንዘጋጅ እንችላለን። አብዛኛውን ጊዜ ወደ መስክ አገልግሎት የምንሄደው ከሌሎች ጋር በመሆኑ ለሁለታችንም የሚመች ዝግጅት ለማድረግ የእነርሱን ፕሮግራም መጠየቅ ያስፈልገናል።
16 በአገልግሎት ክልሉ ውስጥ ያሉት ሰዎች ለመልእክቱ ፍላጎት የሌላቸው ቢሆኑም እንኳ የስብከት ልማዳችን መተጓጎል የለበትም። ጥሩ ምላሽ የሚሰጡን ሰዎች ጥቂት እንደሚሆኑ አስቀድመን የምናውቀው ነገር ነው። (ማቴ. 13:15፤ 24:9) ሕዝቅኤል ‘ዓመፀኛ፣ እልከኛና ልበ ደንዳና’ ለሆነ ሕዝብ እንዲሰብክ ተልኮ ነበር። ይሖዋ ለሕዝቅኤል ‘ግንባሩን እንደ እነርሱ ግንባር’ በማጠንከር “ከአለትና ከዐልማዝ ይልቅ የጠነከረ” እንደሚያደርገው ቃል ገብቶለት ነበር። (ሕዝ. 2:3, 4፤ 3:7–9 የ1980 ትርጉም ) እንግዲያውስ የማያቋርጥ የአገልግሎት ልማድ በትዕግሥት መጽናትን ይጠይቃል።
17 ልንመስላቸው የሚገቡ መልካም ምሳሌዎች፦ አብዛኞቻችን ቀዳሚ ሆኖ የሚመራን ሰው ስናገኝ በመስክ አገልግሎት የተሻለ እንቅስቃሴ እናደርጋለን። ጳውሎስና ጓደኞቹ ጥሩ ምሳሌ ነበሩ። ሌሎችም እርሱን እንዲመስሉት ጳውሎስ አጥብቆ አሳስቧል። (ፊል. 3:17) የጳውሎስ ልማድ በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆኖ ለመቀጠል የሚያስፈልጉትን ነገሮች ሁሉ ያካተተ ነበር።
18 ዛሬም ቢሆን መልካም ምሳሌዎችን በማግኘት ተባርከናል። በዕብራውያን 13:7 ላይ ጳውሎስ “ . . . ዋኖቻችሁን [ቀዳሚ የሆኑትን] አስቡ፣ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው” በማለት አሳስቧል። እርግጥ ምሳሌያችን ክርስቶስ ነው፤ ይሁን እንጂ መሪ የሆኑ ወንድሞች የሚያሳዩትን እምነትም መምሰል እንችላለን። እንደ ጳውሎስ ሁሉ ሽማግሌዎችም ለሌሎች ጥሩ ምሳሌ የመሆናቸው አስፈላጊነት ጎልቶ ሊታያቸው ይገባል። የግል ሁኔታዎቻቸው የተለያዩ ሊሆኑ ቢችሉም እያንዳንዳቸው የመንግሥቱን ፈቃድ በማስቀደም በሥርዓታማ ልማድ መመላለሳቸውን እንደቀጠሉ ማሳየት መቻል አለባቸው። ዓለማዊ ሥራና የቤተሰብ ኃላፊነቶች ቢኖሩባቸውም ሽማግሌዎች በግል ጥናት፣ በስብሰባዎች ላይ በመገኘት እንዲሁም በአገልግሎት አዘውታሪዎች በመሆን የተደላደለ ልማድ ሊኖራቸው ይገባል። ሽማግሌዎች ‘የራሳቸውን ቤት በመልካም እንደሚያስተዳድሩ’ የሚያሳይ ነገር ሲያደርጉ በጉባኤ ውስጥ ያሉት ሁሉ በሥርዓታማ ልማድ መመላለሳቸውን እንዲቀጥሉበት ይበረታታሉ። — 1 ጢሞ. 3:4, 5
19 ለአዲሱ የአገልግሎት ዓመት የምናወጣቸው ግቦች፦ አዲሱ የአገልግሎት ዓመት የሚጀምርበት ጊዜ ስለ ግል ልማዳችን ትኩረት ለመስጠት ተስማሚ የሆነ ወቅት ነው። ያለፈውን ዓመት እንቅስቃሴ መለስ ብለን ስንቃኘው ምን ያሳያል? የእንቅስቃሴ ደረጃችንን ጠብቀን ለመቆየት፣ የሚቻል ከነበረም ለማሻሻል ችለናልን? የግል ጥናታችንን በበለጠ ጥልቀት ለማከናወን ችለን ይሆናል። ይበልጥ አዘውታሪዎች በመሆን በስብሰባዎች ላይ ተገኝተን ወይም ደግሞ ረዳት አቅኚዎች ሆነን በመሥራት የመስክ አገልግሎት እንቅስቃሴያችንን ከፍ ለማደረግ ችለን ይሆናል። ምናልባትም በጉባኤያችን ወይም በቤተሰባችን ውስጥ ላሉ ሌሎች ሰዎች ክርስቲያናዊ ደግነት ያሳየንባቸውን የተወሰኑ ነገሮች ልንጠቅስ እንችል ይሆናል። እንዲህ ከሆነ አምላክን በሚያስደስት መንገድ ስለተመላለስን ደስ ሊለን ይገባል። እንዲሁም ‘ከዚህ በፊት ካደረግነው ይበልጥ’ ለማድረግ ጥሩ ምክንያት ይኖረናል። — 1 ተሰ. 4:1 የ1980 ትርጉም።
20 ልማዳችን ወጥነት የጎደለውና አልፎ አልፎ የሚቋረጥ ከነበረስ? መንፈሳዊነታችን እንዴት ተነክቷል? እድገታችንን የገቱት አንዳንድ ነገሮች ነበሩን? ማሻሸል ማድረግ የሚጀመረው የይሖዋን እርዳታ በመጠየቅ ነው። (ፊል. 4:6, 13) የልማዶቻችሁን አንዳንድ ዘርፎች በማስተካከል ረገድ ከቀረው ቤተሰብ ድጋፍ እንድታገኙ ምን እንደሚያስፈልጋችሁ ተወያዩበት። ችግሮች ከገጠሟችሁ ሽማግሌዎች እንዲረዷችሁ ጠይቋቸው። ልባዊ ጥረት የምናደርግና የይሖዋን አመራር የምንከተል ከሆነ ‘ሥራ ፈትነትንና ፍሬ ቢስነትን’ ለማስወገድ እንችላለን። — 2 ጴጥ. 1:5–8
21 በሥርዓታማ ልማድ መመላለስ ድካማችን ከንቱ እንዳልቀረ የሚያሳዩ በረከቶችን ያመጣልናል። በሥርዓታማ ልማድ እያደጋችሁ መሄዳችሁን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ ስታደርጉ “ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ፤ በመንፈስ የምታቀጠሉ ሁኑ፤ ለጌታ ተገዙ።” (ሮሜ 12:11) በዚህ ርዕስ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለማግኘት ግንቦት 1, 1985 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 13–17 ያለውን ተመልከት።