የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w98 10/1 ገጽ 28-31
  • በመንፈሳዊ እድገት ማድረጋችሁን ቀጥሉ!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በመንፈሳዊ እድገት ማድረጋችሁን ቀጥሉ!
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በግል ጥናት አማካኝነት እድገት ማድረግ
  • ወደ አምላክ የመቅረብ አስፈላጊነት
  • ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና ማዳበር
  • በአገልግሎትህ መንፈሳዊ እድገት አድርግ
  • ወጣቶች—ከተጠመቃችሁ በኋላ እድገት ማድረጋችሁን ቀጥሉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022
  • አምላክን ለዘላለም ማገልገልን ዓላማህ አድርግ
    ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት
  • በሥርዓታማ ልማድ እያደጋችሁ መሄዳችሁን ቀጥሉ
    የመንግሥት አገልግሎታችን—1994
  • የይሖዋ ምሥክሮች በኢየሱስ ያምናሉ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2014
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
w98 10/1 ገጽ 28-31

በመንፈሳዊ እድገት ማድረጋችሁን ቀጥሉ!

የተጠመቅንበት ዕለት ከፍ አድርገን የምንመለከተውና የማንረሳው ዕለት ነው። ደግሞም ይህ ዕለት አምላክን ለማገልገል ራሳችንን የወሰንን መሆናችንን ለሕዝብ ያሳየንበት ዕለት ነው።

ብዙ ግለሰቦች እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ጠይቆባቸዋል። ይህም ሥር የሰደዱ መጥፎ ልማዶቻቸውን መተው፣ ከመጥፎ ባልንጀሮች መራቅና በውስጣቸው የተቀረጸውን አስተሳሰብና ባሕርይ እርግፍ አድርጎ መተው አስፈልጓቸዋል።

ምንም እንኳን ጥምቀት በአንድ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ አስደሳችና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ወቅት ቢሆንም የመጀመሪያ እርምጃ ብቻ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በይሁዳ ለነበሩ የተጠመቁ ክርስቲያኖች “የክርስቶስን ነገር መጀመሪያ የሚናገረውን ቃል ትተን ወደ ፍጻሜ እንሂድ” ብሏቸው ነበር። (ዕብራውያን 6:​1) አዎን፣ ሁሉም ክርስቲያኖች “በእምነትና ስለ አምላክ ልጅ ትክክለኛ እውቀት በማግኘት በኩል አንድ ወደ መሆን፣ ጎልማሳ ወደ መሆን፣ የክርስቶስ ሙሉነት ወደ ሆነው የዕድገት ደረጃ” መድረስ ይኖርባቸዋል። (ኤፌሶን 4:​13 NW) ‘በእውነት ውስጥ ሥር ሰድደን መቆም’ የምንችለው ወደ ጉልምስና እድገት ካደረግን ብቻ ነው።​—⁠ቆላስይስ 2:​7

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ራሳቸውን የወሰኑ አገልጋዮች ወደ ክርስቲያን ጉባኤ መጥተዋል። ምናልባት አንተም ከእነዚህ መካከል አንዱ ልትሆን ትችላለህ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ወንድሞችህ በመንፈሳዊ ሕፃን እንደሆንክ መቅረት አትፈልግም። እድገት ማድረግ ትፈልጋለህ! ግን እንዴት? በመንፈሳዊ እድገት ማድረግ የምትችልባቸው አንዳንድ አቅጣጫዎችስ የትኞቹ ናቸው?

በግል ጥናት አማካኝነት እድገት ማድረግ

ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ለነበሩ ክርስቲያኖች ሲጽፍ “ፍቅራችሁ [“በትክክለኛ፣” NW] እውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ ይህን እጸልያለሁ” ብሏቸው ነበር። (ፊልጵስዩስ 1:​9) “ትክክለኛ እውቀት” መጨመር ለመንፈሳዊ እድገትህ ወሳኝ የሆነ ነገር ነው። ‘ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት መሰብሰብ’ ከጥምቀት በኋላ የሚያቆም ነገር ሳይሆን ቀጣይነት ያለው ሂደት ነው።​—⁠ዮሐንስ 17:​3

አሌክሳንድራ ብለን የምንጠራት አንዲት ክርስቲያን እህት የተጠመቀችው በ16 ዓመቷ ሲሆን ይህን የተገነዘበችው ከተጠመቀች ከአሥር ዓመት በኋላ ነው። ያደገችው በእውነት ቤት ውስጥ ሲሆን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ሳታሰልስ ትገኝ እንዲሁም አዘውትራ በስብከቱ ሥራ ትካፈል ነበር። እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “ከተወሰኑ ወራት ወዲህ አንድ ትልቅ ችግር እንዳለ ተገነዘብኩ። ለእውነት ምን እንደሚሰማኝ፣ በእውነት ውስጥ ለምን እንደምኖር በጥሞናና በሃቀኝነት ራሴን ለመመርመር ወሰንኩ።” ምን አገኘች? እንዲህ ስትል ትቀጥላለች:- “በእውነት ውስጥ እንድቆይ የሚያደርጉኝ ምክንያቶች እንደሚረብሹኝ ተረዳሁ። ልጅ በነበርኩበት ጊዜ ለስብሰባዎችና ለመስክ አገልግሎት ከፍተኛ አጽንዖት ይሰጥ እንደ ነበር አስታውሳለሁ። የግል ጥናትና የጸሎት ልማዶች ግን ምንም ጥረት ሳይደረግ እንዲሁ በራሳቸው የሚመጡ ነገሮች እንደሆኑ አስብ ነበር። ሆኖም የእኔን ሁኔታ ሳጤነው እንደዚህ እንዳልሆነ ተገነዘብኩ።”

ሐዋርያው ጳውሎስ “በደረስንበት የዕድገት ደረጃ በዚያው ልማድ በሥርዓት መመላለሳችንን እንቀጥል” በማለት አጥብቆ መክሯል። (ፊልጵስዩስ 3:​16 NW) አንድ ልማድ ወደፊት የሚደረግን ወጥ የሆነ እንቅስቃሴ ሊቀይስ ይችላል። ከመጠመቅህ በፊት ብቃት ካለው አስተማሪ ጋር በየሳምንቱ መጽሐፍ ቅዱስን የማጥናት ልማድ እንደነበረህ ምንም አያጠራጥርም። አድናቆትህ እያደገ ሲሄድ በየሳምንቱ ለምታደርገው ጥናት ቀደም ብሎ መዘጋጀትን፣ ጥቅሶችን ከመጽሐፍ ቅዱስ አውጥቶ መመልከትና ሌሎች ነገሮችንም ማካተት ጀመርክ። አሁንስ ከተጠመቅህ አንስቶ ‘በዚያው ልማድ በሥርዓት መመላለስህን’ ቀጥለሃል?

ካልሆነ ‘የሚሻሉትን ነገሮች ፈትነህ ማወቅ ትችል ዘንድ’ ቅድሚያ ስለምትሰጣቸው ነገሮች እንደገና ማጤን ያስፈልግህ ይሆናል። (ፊልጵስዩስ 1:​10) ሕይወታችን ጥድፊያ የሞላበት በመሆኑ የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብና ጥናት ለማድረግ የሚያስችል ጊዜ ለመመደብ ራስን መግዛት ይጠይቃል። ይሁን እንጂ የሚያስገኘው ጥቅም ሲታይ ቢደከምለት ምንም አያስቆጭም። የአሌክሳንድራን ምሳሌ እንደገና እንመልከት። “ያለፉትን 20 ወይም ከዚያ የሚበልጡ ዓመታት በእውነት ቤት ውስጥ ያሳለፍኩት ወደ ስብሰባዎች በመሄድና በመስክ አገልግሎት በመካፈል ብቻ ነበር ብዬ መናገር እችላለሁ” በማለት ሐቁን ሳትሸሽግ ተናግራለች። ሆኖም በመቀጠል እንዲህ ብላለች:- “ምንም እንኳ እነዚህ ነገሮች አስፈላጊ ቢሆኑም ሁኔታዎች አስቸጋሪ እየሆኑ ሲሄዱ እነዚህ ብቻ ጠብቀው ሊያቆሙኝ እንደማይችሉ ተገነዘብኩ። የግል ጥናት ልማዴ ጨርሶ ተቋርጦ ስለነበረና የማቀርበውም ጸሎት እንዲያው ለይስሙላ ያክል አልፎ አልፎ ስለነበረ እነዚህ ልማዶች ወሳኝ እንደሆኑ ተገነዘብኩ። ይሖዋን በትክክል ማወቅና መውደድ እንድችል እንዲሁም ልጁ የሰጠንን ሁሉ ማድነቅ እችል ዘንድ አሁኑኑ አስተሳሰቤን ማስተካከልና ትርጉም ያለው የጥናት ፕሮግራም ማውጣት እንዳለብኝ ተገነዘብኩ።”

ጠቃሚ የሆነ የግል ጥናት ልማድ እንዲኖርህ እርዳታ የምትፈልግ ከሆነ በጉባኤ ያሉ ሽማግሌዎችና ሌሎች የጎለመሱ ክርስቲያኖች በደስታ ይረዱሃል። በተጨማሪም ግንቦት 1, 1995፣ ነሐሴ 15, 1993 እና 5–107 የመጠበቂያ ግንብ እትሞች ላይ የወጡት ርዕሶች ጠቃሚ ሐሳቦችን ይዘዋል።

ወደ አምላክ የመቅረብ አስፈላጊነት

እድገት ለማድረግ መጣጣር የሚኖርብህ ሌላው መስክ ደግሞ ከአምላክ ጋር ስለሚኖርህ የግል ዝምድና ነው። በአንዳንድ ወቅቶች የዚህ አስፈላጊነት አጣዳፊ የሚሆንበት ጊዜ አለ። በልጅነቱ የተጠመቀውን የአንቶኒን ሁኔታ ተመልከት። “ከቤተሰባችን ልጆች መካከል በመጀመሪያ የተጠመቅኩት እኔ ነበርኩ” በማለት ይናገራል። “ከተጠመቅሁ በኋላ እናቴ ሞቅ ባለ ስሜት እቅፍ አድርጋ ሳመችኝ። እንደዚያ ቀን ተደስታ አይቻት አላውቅም። ደስታችን እጥፍ ድርብ ነበር። እኔም ጥንካሬ ተሰማኝ።” ይሁን እንጂ ሁኔታው ሌላ መልክም ነበረው። “ለተወሰኑ ጊዜያት በጉባኤያችን ውስጥ የተጠመቀ አንድም ወጣት አልነበረም” በማለት አንቶኒ ይናገራል። “በዚህም የተነሳ ኩራት ተሰማኝ። በስብሰባዎች ላይ በምሰጣቸው ሐሳቦችና በማቀርባቸው ንግግሮች ኩራት ኩራት ይለኝ ነበር። ለይሖዋ ክብር ከመስጠት ይልቅ ለራሴ የሰዎችን ውዳሴና አድናቆት ማግኘቱን አስበልጬ ማየት ጀመርኩ። ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና አልነበረኝም።”

እንደ አንቶኒ ሁሉ አንዳንዶች ይሖዋን የማስደሰት ምኞት አድሮባቸው ሳይሆን ሌሎች ሰዎችን ለማስደሰት ሲሉ ብቻ ራሳቸውን ለአምላክ ይወስኑ ይሆናል። ራሳቸውን የወሰኑት በዚህ መንገድ ቢሆንም እንኳ አምላክን ለማገልገል የገቡትን ቃል እንዲያከብሩ አምላክ ይጠብቅባቸዋል። (ከመክብብ 5:​4 ጋር አወዳድር።) ሆኖም እነዚህ ግለሰቦች ከአምላክ ጋር የቅርብ ትስስር እስካልፈጠሩ ድረስ እንዲህ ማድረጉ ቀላል እንደማይሆንላቸው ግልጽ ነው። አንቶኒ እንዲህ በማለት ያስታውሳል:- “በተጠመቅኩ ጊዜ የተሰማኝ ከፍተኛ የደስታ ስሜት እንደ ጉም በኖ ጠፋ። ከባድ ስህተት ላይ ወድቄ የጉባኤ ሽማግሌዎች ተግሳጽ ሲሰጡኝ ከተጠመቅኩ አንድ ዓመት አልሞላኝም ነበር። በተደጋጋሚ በፈጸምኩት ጥፋት ምክንያት ከጉባኤ ተወገድኩ። ራሴን ለይሖዋ ከወሰንኩ ከስድስት ዓመት በኋላ በነፍስ ግድያ ወንጀል ተያዝኩና እስር ቤት ገባሁ።”

ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና ማዳበር

ያለህበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ሁሉም ክርስቲያኖች “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ የሚያቀርበውን ግብዣ በደስታ ሊቀበሉት ይችላሉ። (ያዕቆብ 4:​8) መጽሐፍ ቅዱስን ለመጀመሪያ ጊዜ ማጥናት ስትጀምር ከአምላክ ጋር በተወሰነ መጠን መቀራረብ እንደ ጀመርክ አይካድም። አምላክ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ እንደሚመለከው ዓይነት ረቂቅ የሆነ ነገር ሳይሆን ይሖዋ የሚል መጠሪያ ስም ያለው ሕያው አካል መሆኑን አውቀሃል። በተጨማሪም አምላክ ማራኪ የሆኑ ባሕርያት ያሉት መሆኑን ማለትም “መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለ ብዙ ቸርነት” እንደሆነ ተምረሃል።​—⁠ዘጸአት 34:​6

ይሁን እንጂ አምላክን ለማገልገል ስትል ካደረግከው ውሳኔ ጋር ተስማምተህ ለመኖር ወደ እርሱ ይበልጥ መቅረብ ይኖርብሃል! እንዴት? መዝሙራዊው “ፍለጋህንም አስተምረኝ። አንተ የመድኃኒቴ አምላክ ነህና” በማለት ጸልዮአል። (መዝሙር 25:​4) መጽሐፍ ቅዱስንና የማኅበሩን ጽሑፎች በግል ማጥናት ከይሖዋ ጋር በተሻለ መንገድ እንድትቀራረብ ሊረዱህ ይችላሉ። ከልብ በመነጨ ስሜት አዘውትሮ መጸለይም ሌላው ጠቃሚ የሆነ ነገር ነው። “ልባችሁንም በፊቱ አፍስሱ” በማለት መዝሙራዊው ያበረታታል። (መዝሙር 62:​8) ለጸሎትህ መልስ ስታገኝ አምላክ ትኩረቱን በአንተ ላይ እንዳደረገ ይሰማሃል። ይህም ወደ እርሱ ይበልጥ እንደቀረብክ እንዲሰማህ ያደርግሃል።

የሚገጥሙን ፈተናዎችና ችግሮች ወደ አምላክ ለመቅረብ የሚያስችሉ ተጨማሪ አጋጣሚዎች ናቸው። እንደ ሕመም፣ በትምህርት ቤትና በሥራ ቦታ የሚያጋጥሙ ተጽእኖዎች ወይም የኢኮኖሚ ችግርን የመሳሰሉ እምነትህን የሚፈታተኑ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ይገጥምህ ይሆናል። ምናልባትም በአገልግሎት እንደ መካፈል፣ በስብሰባዎች ላይ እንደ መገኘት ወይም ከልጆችህ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ማጥናት ያሉ የተለመዱ ቲኦክራሲያዊ ልማዶችን ማከናወኑ ራሱ ከባድ ሆኖብህ ሊሆን ይችላል። እንደነዚህ ያሉትን ችግሮች ለብቻህ አትጋፈጣቸው! አምላክ አመራር እንዲሰጥህና አቅጣጫውን እንዲያመለክትህ በመጠየቅ እርዳታውን እንዲለግስህ ተማጸነው። (ምሳሌ 3:​5, 6) መንፈስ ቅዱሱን እንዲሰጥህ ለምነው! (ሉቃስ 11:​13) የአምላክን ፍቅራዊ እገዛ ባገኘህ መጠን ወደ እርሱ ይበልጥ እየቀረብክ ትሄዳለህ። መዝሙራዊው ዳዊት “እግዚአብሔር ቸር እንደ ሆነ ቅመሱ እዩም፤ በእርሱ የሚታመን ሰው ምስጉን ነው” በማለት ሁኔታውን ገልጿል።​—⁠መዝሙር 34:​8

የአንቶኒ መጨረሻ ምን ሆነ? “የይሖዋን ፈቃድ ከማድረግ ጋር የተያያዙ በርካታ ግቦች ያወጣሁበትን ጊዜ መለስ ብዬ ማስታወስ ጀመርኩ” በማለት ያስታውሳል። “ይህን ማሰቡ ሥቃይ ነበር። በከፍተኛ ስቃይና ብስጭት ላይ እያለሁ የይሖዋን ፍቅር አስታወስኩ። ወደ ይሖዋ ለመጸለይ ጊዜያት ወስደውብኛል። ይሁን እንጂ በጸሎት ልቤን አፍስሼ ይቅር እንዲለኝ ጠየቅኩት። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ጀመርኩና ምን ያህል እንደረሳሁና ስለ ይሖዋ የማውቀው ምን ያህል ጥቂት እንደሆነ ሳውቅ በጣም ተገረምኩ።” አንቶኒ በፈጸመው ወንጀል ምክንያት የተበየነበትን ፍርድ እስር ቤት ውስጥ ሆኖ ገና መጨረስ ቢኖርበትም አካባቢው የሚገኙ ምሥክሮች እርዳታ እያገኘ በመንፈሳዊ በማገገም ላይ ነው። አንቶኒ በአመስጋኝነት መንፈስ እንዲህ ይላል:- “ለይሖዋና ለድርጅቱ ምስጋና ይግባቸውና አሮጌውን ሰውነት ማስወገድ ችዬአለሁ፤ እንዲሁም በየቀኑ አዲሱን ሰውነት ለመልበስ ከፍተኛ ጥረት አደርጋለሁ። በአሁኑ ጊዜ ከሁሉ ይበልጥ ከፍተኛውን ቦታ የምሰጠው ከይሖዋ ጋር ያለኝን ዝምድና ነው።”

በአገልግሎትህ መንፈሳዊ እድገት አድርግ

ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮቹ ‘የመንግሥቱ ምሥራች’ ሰባኪዎች እንዲሆኑ አዟል። (ማቴዎስ 24:​14) በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አዲስ የምሥራቹ አስፋፊ እንደመሆንህ መጠን በአገልግሎቱ ያለህ ተሞክሮ ውስን ሊሆን ይችላል። ታዲያ ‘አገልግሎትህን ሙሉ በሙሉ ለመፈጸም’ ትችል ዘንድ እድገት ልታደርግ የምትችለው እንዴት ነው?​—⁠2 ጢሞቴዎስ 4:​5

አንዱ መንገድ አዎንታዊ ዝንባሌ ማዳበር ነው። የስብከቱ ሥራ “ውድ ሀብት” እና መብት እንደሆነ አድርገህ መመልከትን ተማር። (2 ቆሮንቶስ 4:​7) ለይሖዋ ፍቅር፣ ታማኝነትና የጸና አቋም እንዳለን የምናሳይበት አጋጣሚ ነው። በተጨማሪም ለጎረቤቶቻችን አሳቢነታችንን እንድናሳይ አጋጣሚ ይከፍትልናል። በዚህ መንገድ ያለምንም ስስት ራሳችንን ማቅረባችን ደስታችንን እጥፍ ድርብ ሊያደርግልን ይችላል።​—⁠ሥራ 20:​35

ኢየሱስ ራሱ ለስብከቱ ሥራ አዎንታዊ አመለካከት ነበረው። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለሌሎች ማካፈል ለእርሱ እንደ “መብል” ነበር። (ዮሐንስ 4:​34) ሌሎችን ለመርዳት የነበረው ውስጣዊ ስሜት “እወዳለሁ” ብሎ በተናገረው ቃል ጠቅለል ተደርጎ ሊገለጽ ይችላል። (ማቴዎስ 8:​3) ኢየሱስ ለሰዎች በተለይ ደግሞ በሰይጣን ዓለም ‘ተጨንቀውና ተጥለው” ለነበሩ ሰዎች ከፍ ያለ የርኅራኄ ስሜት ነበረው። (ማቴዎስ 9:​35, 36) አንተስ በመንፈሳዊ ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች የአምላክን ቃል ብርሃን ለመፈንጠቅ “እወዳለሁ” ትላለህ? እንደዚያ ከሆነ ኢየሱስ “ሂዱና አሕዛብን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” የሚለውን የኢየሱስን ትእዛዝ ለመፈጸም ከውስጥ ትገፋፋለህ ማለት ነው። (ማቴዎስ 28:​19) አዎን፣ ጤንነትህና ሁኔታህ የሚፈቅድልህን ያክል በዚህ ሥራ ሙሉ በሙሉ ለመካፈል ከውስጥ እንደምትገፋፋ የተረጋገጠ ነው።

እድገት ለማድረግ የሚያግዘው ሌላው ቁልፍ ነገር ደግሞ ቢያንስ በየሳምንቱ አዘውትሮ በአገልግሎት መካፈል ነው። እንዲህ ማድረጉ አልፎ አልፎ ብቻ የሚሰብክ ሰው የሚያጋጥሙትን የመርበትበትና የፍርሃት ስሜት ለማጥፋት ይረዳል። አዘውትሮ በመስክ አገልግሎት መካፈል በሌሎች ተጨማሪ መንገዶችም ይጠቅምሃል። ለእውነት ያለህን አድናቆት ያሳድግልሃል፣ ለይሖዋና ለጎረቤት ያለህን ፍቅር ከፍ ያደርግልሃል እንዲሁም በመንግሥቱ ተስፋ ላይ ብቻ ትኩረት እንድታደርግ ይረዳሃል።

ይሁን እንጂ ያለህበት ሁኔታ በስብከቱ ሥራ የምታከናውነውን ተሳትፎ በእጅጉ የሚገታብህ ቢሆንስ? ያለህበት ሁኔታ ፈጽሞ ሊስተካከል የማይችል ከሆነ አገልግሎትህን በሙሉ ነፍስ በማከናወን ማድረግ በምትችለው ነገር ሁሉ አምላክ እንደሚደሰት በማወቅህ ልትጽናና ትችላለህ። (ማቴዎስ 13:​23) ምናልባትም የስብከት ችሎታን ማሻሻልን በመሰሉ በሌሎች መንገዶችም እድገት ማድረግ ትችል ይሆናል። በጉባኤ ውስጥ የሚቀርቡት ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤትና የአገልግሎት ስብሰባ በዚህ በኩል ከፍተኛ ስልጠና ይሰጣሉ። በአገልግሎቱ በጥሩ ብቃት በተካፈልን መጠን ይበልጥ ደስተኞችና ውጤታማ እንሆናለን።

ስለዚህ አንድ ሰው ልክ ሲጠመቅ መንፈሳዊ እድገት ማድረጉን ያቆማል ማለት አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ በሰማይ የማይሞት ሕይወት የማግኘት ተስፋውን አስመልክቶ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል:- “ወንድሞች ሆይ፣ እኔ ገና እንዳልያዝሁት እቈጥራለሁ፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ከፍ ከፍ ያለውን የእግዚአብሔርን መጥራት ዋጋ እንዳገኝ ምልክትን እፈጥናለሁ። እንግዲህ ፍጹማን የሆንን ሁላችን ይህን እናስብ፤ በአንዳች ነገርም ልዩ አሳብ ቢኖራችሁ፣ እግዚአብሔር ይህን ደግሞ ይገልጥላችኋል።”​—⁠ፊልጵስዩስ 3:​13-15

አዎን፣ ሁሉም ክርስቲያኖች ተስፋቸው በሰማይ የማይጠፋ ሕይወት ማግኘትም ሆነ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም መኖር የሕይወት ግባቸው ላይ ለመድረስ ‘ወደፊት መዘርጋት’ በሌላ አባባል ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለባቸው! መጠመቅህ ጥሩ ጅምር ቢሆንም ይህ የመጀመሪያ እርምጃ ብቻ ነው። መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ ጥረት ማድረግህን ቀጥል። በስብሰባዎችና በግል ጥናት አማካኝነት ‘በአእምሮ የበሰልክ ሁን።’ (1 ቆሮንቶስ 14:​20) የእውነትን ‘ስፋትና ርዝመት ከፍታውንም ጥልቅነቱንም የምታስተውል’ ሁን። (ኤፌሶን 3:​18) የምታደርገው እድገት የሚረዳህ በአሁን ጊዜ ደስታና እርካታ እንድታገኝ ብቻ ሳይሆን በአምላክ አዲስ ዓለምም የተረጋጋ ሕይወት እንድታገኝም ጭምር ነው። በአምላክ ሰማያዊ መንግሥት አገዛዝ ፍጻሜ ለሌለው ጊዜ እድገት ማድረግ ትችላለህ!

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የግል ጥናት ለማድረግ የሚያስችል ጊዜ ለመመደብ ራስን መገሰጽ ይጠይቃል

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አዎንታዊ አመለካከት መያዝ በአገልግሎት ደስታ እንድናገኝ ሊረዳን ይችላል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ