ጥሩ ልማዶችን በማዳበር የተትረፈረፈ በረከት እጨዱ
1. መንፈሳዊ ልማድህን መመርመርህ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
1 መጀመሪያ ክርስቲያን በሆንክበት ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትን፣ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን፣ የመስክ አገልግሎትንና ጸሎትን ጨምሮ በሌሎች መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ላይ አዘውትሮ የመካፈል ጠቃሚ ልማድ ለማዳበር ብዙ ጥረት ሳይጠይቅብህ አልቀረም። ይሖዋም ጥረትህን ስለባረከልህ መንፈሳዊ እድገት ማድረግ ችለሃል። አሁን ግን ከተጠመቅህ በርካታ ዓመታት አልፈው ሊሆን ይችላል። ታዲያ ክርስቲያን ስትሆን ያዳበርካቸውን እነዚህን ጥሩ መንፈሳዊ ልማዶች አሁንም ቀጥለህባቸዋል?
2. መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበባችን ምን ጥቅሞች ያስገኝልናል?
2 ልማዶችህን መርምር:- ከአምላክ ቃል ውስጥ የተወሰነውን ክፍል በየዕለቱ የማንበብ ልማድ አለህ? እንዲህ በማድረጋችን ምን ያህል የተትረፈረፈ በረከት እንደምናጭድ መገመት ትችላለህ! (ኢያሱ 1:8፤ መዝ. 1:2, 3) በጥንቷ እስራኤል እያንዳንዱ ንጉሥ የሕጉን ቅጂ “በሕይወቱ ዘመን ሁሉ” እንዲያነብ ይጠበቅበት ነበር። ይህስ ምን ጥቅም ያስገኝለታል? ትሑት ልብ እንዲኖረው የሚያስችለው ከመሆኑም በላይ ይሖዋን ማክበር ወይም መፍራት ይማራል፤ ይህ ደግሞ ትእዛዛቱን በጥብቅ እንዲከተል ይረዳዋል። (ዘዳ. 17:18-20) ዛሬም በተመሳሳይ መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበባችን በዚህ ክፉና የተበላሸ ዓለም ውስጥ ያለነቀፋ በየዋህነት እንድንመላለስ ይረዳናል። ከዚህም በላይ ለአገልግሎት በሚገባ የታጠቅን እንድንሆን ያደርገናል።—ፊልጵ. 2:15፤ 2 ጢሞ. 3:17
3. አዘውትረን ወደ ስብሰባዎች መሄዳችን ምን በረከቶች ያስገኝልናል?
3 ኢየሱስ ቅዱሳን መጻሕፍት ወደሚብራሩበት ወደ ምኩራብ የመሄድ ልማድ ነበረው። (ሉቃስ 4:16) እንዲህ ማድረጉ ደግሞ ከፊቱ የሚጠብቁትን ተፈታታኝ ችግሮች ለመወጣት የሚያስችለውን ብርታት እንደሰጠው ምንም ጥርጥር የለውም። እኛም እንዲሁ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በሚሰጡን ትምህርቶችና ከክርስቲያን ወንድሞች በምናገኘው ገንቢ የሆኑ ‘ማበረታቻዎች’ አማካኝነት ጥንካሬ እናገኛለን። (ሮሜ 1:12) ከወንድሞቻችን ጋር አብረን መሰብሰባችን በዚህ የመጨረሻ ዘመን ውስጥ የሚያጋጥሙንን አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንድንቋቋም ይረዳናል። (ዕብ. 10:24, 25) በአሁኑ ጊዜስ በሁሉም ስብሰባዎች ላይ የመገኘት ልማድ አለህ?
4. በየሳምንቱ በመስክ አገልግሎት መካፈላችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?
4 ሐዋርያት “በየዕለቱም፣ በቤተ መቅደስም ሆነ በየቤቱ” ምሥራቹን ያውጁ እንደነበር በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት ዘገባዎች ይናገራሉ። (ሥራ 5:42) በየዕለቱ ለመስበክ ሁኔታችን የማይፈቅድልን ከሆነ በአንድ ዓይነት የአገልግሎት ዘርፍ በየሳምንቱ የመካፈል ልማድ ማዳበር እንችል ይሆን? እንዲህ ካደረግን የአምላክን ቃል በመጠቀም ረገድ የተካንን እንደምንሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ከዚህም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች ስናካፍል አበረታች የሆኑ ተሞክሮዎችን ማግኘታችን አይቀርም።
5. አዘውትሮ ወደ ይሖዋ መጸለይ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
5 ነቢዩ ዳንኤል እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ “ሁልጊዜ” ይሖዋን እያገለገለ መኖሩ ብዙ በረከቶች አስገኝቶለታል። ዳንኤል ወደ ይሖዋ አዘውትሮ የመጸለይ ልማድ ነበረው። (ዳን. 6:10, 16, 20) በተመሳሳይ እኛም ወደ ይሖዋ አዘውትረን ከጸለይን ቅዱስ መንፈሱን በመስጠት ይባርከናል። (ሉቃስ 11:9-13) ከዚህም በላይ ይሖዋ ይበልጥ ወደ እኛ ቀርቦ የቅርብ ወዳጆቹ በማድረግ ለጸሎታችን መልስ ይሰጣል። (መዝ. 25:14፤ ያዕ. 4:8) እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! በመሆኑም ጥሩ መንፈሳዊ ልማዶችን ለማዳበር ጠንክረን እንሥራ። ከዚያም ብዙ በረከቶችን እናጭዳለን።