1 እውነት፣ የቤተሰብ ሕይወት ትክክለኛ ትርጉምና ዓላማ እንዲኖረው ያደርጋል። ይሁን እንጂ ይሖዋን በማገልገል ረገድ ስኬታማ መሆን በቀላሉ የሚገኝ ነገር አይደለም። በመንፈሳዊ ጠንካራ የሆነ ቤተሰብ መገንባት ጊዜና ጥረት ይጠይቃል። ይህን ግብ ላይ ለማድረስ በሚደረገው ጥረት የቤተሰብ አባላት በቅርብ ተደጋግፈው መሥራታቸው በጣም አስፈላጊ ነው። በሦስት ተከታታይ ክፍሎች ከሚቀርበው ትምህርት የመጀመሪያ የሆነው ይህ ርዕስ ጥሩ የጥናት ልማድ በማዳበር ረገድ የቤተሰብ አባላት መተባበር በሚችሉበት መንገድ ላይ ያተኩራል።
2 በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ፦ ምሳሌ 24:5 ‘አዋቂ ሰው ኃይሉን ያበዛል’ በማለት ይናገራል። ዘወትር የአምላክን ቃል ከማንበብ የሚገኘው እውቀት፣ አንድ ሰው ሰይጣን በመንፈሳዊነቱ ላይ የሚሰነዝርበትን ጥቃት እንዲቋቋም የሚያስችለውን ውስጣዊ ጥንካሬ ይሰጠዋል። (መዝ. 1:1, 2) በቤተሰብ መልክ አንድ ላይ ሆናችሁ በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ታነባላችሁ? የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ፕሮግራም በየሳምንቱ የሚነበብ የአንድ ዓመት “ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም” ይዟል። ቤተሰቡ ይህን ፕሮግራም ለመከታተል የሚያስፈልገው በየቀኑ አሥር ደቂቃ ብቻ መመደብ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብና ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ መመርመር በተባለው ቡክሌት ላይ በሚገኘው የዕለቱ ጥቅስ ላይ ለመወያየት አመቺ ጊዜ ምረጡ። ይህም በቁርስ ሰዓት፣ ከእራት በኋላ ወይም ከመተኛታችሁ በፊት ሊሆን ይችላል። ይህም የቤተሰባችሁ የዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴ ክፍል ይሁን።
3 በየሳምንቱ አንድ ላይ በማጥናት፦ የቤተሰቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጎላ ያለ የሳምንቱ ገጽታ ሊሆንላቸው ይገባል። እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል በጥናቱ ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ጥናቱን መደገፍ አለበት። የቤተሰቡ ራስ የሚጠናውን ጽሑፍ እንዲሁም ጥናቱ የሚደረግበትን ቀን፣ ሰዓትና ጥናቱ የሚቆይበትን ጊዜ ሲወስን የቤተሰቡን ፍላጎት ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል። በሳምንቱ ፕሮግራም ውስጥ ለቤተሰብ ጥናት ቅድሚያ ስጡ። እምብዛም አስፈላጊ ያልሆኑ ነገሮች ጣልቃ እንዲገቡባችሁ አትፍቀዱ።—ፊልጵ. 1:10, 11
4 ከንግድ ሥራው ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ቤቱ ስልክ የሚደወልለት አንድ አባት በቤተሰብ ጥናት ወቅት የስልክ መስመሩን ይነቅለዋል። ደንበኞቹ ቤት ድረስ ከመጡ ደግሞ በጥናቱ ላይ እንዲገኙ ይጋበዛሉ አሊያም ጥናቱ እስኪያልቅ ድረስ እንዲጠብቁ ይነገራቸዋል። አባትየው የቤተሰብ ጥናታቸውን ምንም ነገር እንዲያስተጓጉልባቸው ላለመፍቀድ ቆርጦ ነበር። እንዲህ ማድረጉ በልጆቹ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል፤ ንግዱም ቢሆን አልተዳከመም።
5 የቤተሰብ አባላት በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ሲተባበሩ ማየት እጅግ አስደሳች ነው! በቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወቅት የተሟላ ተሳትፎ ለማድረግ በታማኝነት መጣራችን የይሖዋን በረከት ያስገኛል።—መዝ. 1:3