የቤተሰብ ፕሮግራም ይኑራችሁ—ለቤተሰብ ጥናት
1 ክርስቲያን ወላጆች ለልጆቻችሁ ልትሰጡ ከምትችሉት ስጦታ ሁሉ የላቀው እነርሱም እንደ እናንተ ለይሖዋ ፍቅር እንዲኖራቸው መርዳት ነው። ሳምንታዊ የቤተሰብ ጥናታችሁን ለማድረግ ‘በቤታችሁ ስትቀመጡ’ ይህን ለማከናወን ጥሩ አጋጣሚ ታገኛላችሁ። (ዘዳ. 6:5-7) አንዳንድ ወላጆች የትዳር ጓደኛቸው አማኝ ነው፤ ሌሎች ግን ቤተሰባቸው በሃይማኖት የተከፋፈለ ይሆናል አሊያም ልጆቻቸውን የሚያሳድጉት ብቻቸውን ነው። ያም ቢሆን ግን ቋሚ የቤተሰብ ጥናት በማድረግ ልጆቻችሁ ከእናንተና ከይሖዋ ጋር እንዲቀራረቡ መርዳት ትችላላችሁ።
2 የቤተሰብ ጥናቱን መጀመር:- በዚህ ረገድ የመጀመሪያው እርምጃ በቤተሰብ ሆኖ የማጥናት ልማድ ማዳበር ነው። የቤተሰብ ጥናታችሁን መቼ ብታደርጉት የተሻለ እንደሚሆን መወሰን ከተቸገራችሁ ጉዳዩን በቤተሰብ መልክ ልትወያዩበት ትችላላችሁ። (ምሳሌ 15:22) ትንንሽ ልጆች ካሏችሁ አጠር አጠር እያደረጋችሁ በሳምንቱ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ለማጥናት ትመርጡ ይሆናል። ለቤተሰባችሁ ተስማሚ የሚሆን ፕሮግራም አውጡ። ጥናቱን የምታደርጉበት የተወሰነ ጊዜ መድቡ፤ ይህን ፕሮግራም ለማክበርም ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ።
3 ለጥናቱ የትኞቹን ጽሑፎች መጠቀም ትችላላችሁ? አንዳንድ ቤተሰቦች በቀጣዩ የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት ወይም የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ የሚወሰደውን ትምህርት ይዘጋጃሉ። ሌሎች ደግሞ ለወጣቶች ተብለው የተዘጋጁ ጽሑፎችን ያጠናሉ። አንድ ወንድና አንዲት ሴት ልጅ ያሉት አባት እንዲህ ብሏል:- “ልጆቹ የሳምንቱን ጥናታችንን በጉጉት እንዲጠብቁ የሚያደርጋቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ በተባለው መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን ታሪኮች በድራማ መልክ የምንሠራቸው መሆኑ ነው። ትልቁ ነገር ብዙ አንቀጾች መሸፈናችን ሳይሆን ትምህርቱን በጥልቀት መረዳታቸውና ይህም የሚያሳድረው ተጽዕኖ ነው።”
4 በየሳምንቱ አጥኑ:- የቤተሰብ ጥናታችሁን በየሳምንቱ ሳታሰልሱ ልታደርጉ የሚገባ ሲሆን ጥናቱም ሁሉም የቤተሰቡ አባላት በጉጉት የሚጠብቁት መሆን ይኖርበታል። ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ቀኑንና ሰዓቱን መለወጥ ይቻላል። አንዳንድ ጊዜም የሚጠናውን ትምህርት መቀየር ያስፈልግ ይሆናል። ሆኖም ማንኛውም ዓይነት ማስተካከያ ቋሚ የሆነው የቤተሰብ ጥናት ፕሮግራም ረዘም ላለ ጊዜ እንዲቋረጥ የሚያደርግ መሆን የለበትም። አንድ አባት የቤተሰብ ጥናቱ የሚደረግበትን ፕሮግራም ሲለውጥ የተደረገውን ማስተካከያ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት ሊያዩት በሚችሉት ቦታ ላይ ጽፎ ያስቀምጠዋል። እንደዚህ ያሉት ጥረቶች ቋሚ የቤተሰብ ጥናት ለማድረግ ስለሚረዱ ሊደነቁ ይገባል! ልጆቻችሁን “በጌታ ምክርና ተግሣጽ” ለማሳደግ የምታደርጉት ጥረት እነርሱንም ሆነ ይሖዋን እንደምትወዱ ያሳያል።—ኤፌ. 6:4