የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w97 8/1 ገጽ 26-29
  • ደስታ የሚያስገኝ የቤተሰብ ጥናት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ደስታ የሚያስገኝ የቤተሰብ ጥናት
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ምን ማጥናት ይኖርብናል?
  • አካባቢው ጸጥታ የሰፈነበት ይሁን
  • መጽሐፍ ቅዱስን ሕያው ማድረግ
  • ሁሉም ተሳታፊ እንዲሆኑ መርዳት
  • በነፃነት የሐሳብ ልውውጥ አድርጉ እንጂ አትቆጡ!
  • ጥረት ሊደረግለት የሚገባው ነው
  • የአምላክን ቃል በቤተሰብ መልክ አዘውትራችሁ አጥኑ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ጥናት ብዙ ጥቅም ያስገኛል
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
  • የቤተሰብ ፕሮግራም ይኑራችሁ—ለቤተሰብ ጥናት
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2005
  • ቤተሰባችሁ ጥሩ አቋሙን ጠብቆ ወደ አምላክ አዲስ ዓለም እንዲገባ ለማድረግ ጣሩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
w97 8/1 ገጽ 26-29

ደስታ የሚያስገኝ የቤተሰብ ጥናት

“በቤት ውስጥ ውበት ያላቸውና ውድ የሆኑ ዕቃዎች የሚገኙት ዕውቀት ሲኖር ነው” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ምሳሌ 24:​4 “የ1980 ትርጉም”) እነዚህ ውድ የሆኑ ነገሮች ቁሳዊ ንብረቶች ብቻ ሳይሆኑ እውነተኛ ፍቅርን፣ አምላካዊ ፍርሃትንና ጠንካራ እምነትን የሚጨምሩ ናቸው። እንደነዚህ ያሉት ባሕርያት የቤተሰብን ሕይወት አስደሳች ያደርጉታል። (ምሳሌ 15:​16, 17፤ 1 ጴጥሮስ 1:​7) ሆኖም እነዚህን ባሕርያት ለማግኘት ቤታችን በአምላክ እውቀት እንዲሞላ ማድረግ ይኖርብናል።

የቤተሰቡ ራስ ይህን እውቀት በቤተሰቡ አባላት አእምሮ ውስጥ የመቅረጽ ኃላፊነት አለበት። (ዘዳግም 6:​6, 7፤ ኤፌሶን 5:​25, 26፤ 6:​4) ይህንን ለማድረግ ከሚያስችሉት ጥሩ መንገዶች አንዱ ዘወትር የሚደረግ የቤተሰብ ጥናት ነው። ጥናቱ እውቀት በሚሰጥና አስደሳች በሆነ መንገድ ከተመራ በጥናቱ በሚካፈሉት ሁሉ ዘንድ በጣም ሊወደድ ይችላል! ውጤታማ የሆነ የቤተሰብ ጥናት ለመምራት አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ አንዳንድ ጠቃሚ የሆኑ ነገሮችን እስቲ እንመልከት።a

የቤተሰብ ጥናት ሳይቋረጥ የሚደረግ ከሆነ ውጤታማነቱ ከፍተኛ ይሆናል። በተመቸ ጊዜ ወይም ድንገት ትዝ ሲል ብቻ የሚደረግ ከሆነ ከስንት አንዴ የሚከናወን ነገር መሆኑ የማይቀር ነው። ስለዚህ ለጥናቱ የሚሆን ‘ጊዜ መዋጀት’ አለባችሁ። (ኤፌሶን 5:​15-17) ለሁሉም አመቺ የሆነ ቋሚ ጊዜ መምረጥ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። “የቤተሰብ ጥናታችንን ቋሚ የማድረግ ችግር ነበረብን” በማለት አንድ የቤተሰብ ራስ ሳይሸሽግ ተናግሯል። “በመጨረሻ ለሁላችንም አመቺ የሆነውን አመሻሹ ላይ ያለውን ጊዜ እስክናገኝ ድረስ የተለያየ ጊዜ ሞክረናል። አሁን የቤተሰብ ጥናታችን ቋሚ ሆኗል።”

ተስማሚ የሆነ ጊዜ አንዴ ከመደባችሁ በኋላ የሚያዘናጉ ነገሮች ጥናቱን እንዲያስተጓጉሉ አትፍቀዱላቸው። “በጥናት ላይ እያለን እንግዶች ቢመጡ አባቴ ጥናታችንን እስክንጨርስ ድረስ እንዲጠብቁ ይነግራቸዋል። ስልክ በሚደወልበትም ጊዜ ትንሽ ቆየት ብለው እንዲደውሉ ይነግራቸው ነበር” በማለት የ33 ዓመቷ ማሪያb ታስታውሳለች።

ይሁን እንጂ ይህ ሲባል ምንም ፍንክች ማለት የለም ማለት አይደለም። ድንገተኛ ወይም ያልተጠበቀ ነገር ሊከሰት ይችላል፤ ከዚህም የተነሳ አልፎ አልፎ ጥናቱን መሰረዝ ወይም ለሌላ ጊዜ ማስተላለፍ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። (መክብብ 9:​11) ይሁን እንጂ ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል የትኛውም ቢሆን ልማዳችሁን እንድታቋርጡ እንዲያደርጋችሁ አትፍቀዱ።​—⁠ፊልጵስዩስ 3:​16

ጥናቱ መቆየት ያለበት ለምን ያህል ጊዜ ነው? አንድ ሴት ልጅና አንድ ወንድ ልጅ ጥሩ አድርጎ ያሳደገ ሮበርት የተባለ ሰው “ጥናታችን ብዙውን ጊዜ የሚቆየው ለአንድ ሰዓት ያህል ነው። ልጆቹ ገና ትንንሽ በነበሩበት ጊዜ ከመጠበቂያ ግንብ የጥናት ርዕስ ጥቂት አንቀጾችን፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቂት ምንባቦችንና ከሌሎች ጽሑፎች ውስጥ አንድ ክፍል በማጥናት ለአንድ ሰዓት ያህል ፍላጎታቸው ሳይቀንስ እንዲቆዩ ለማድረግ እንሞክር ነበር” በማለት ይናገራል። ማሪያ “እኔና ሁለት እህቶቼ ገና ትንንሽ በነበርንበት ጊዜ ጥናታችን 20 ደቂቃ የሚቆይ ሲሆን በሳምንት ሁለት ወይም ሦስት ጊዜ ይደረግ ነበር። እያደግን ስንሄድ የቤተሰብ ጥናታችን አንድ ሰዓት ወይም ከዚያ በላይ ይቆይ ነበር” በማለት ታስታውሳለች።

ምን ማጥናት ይኖርብናል?

ሁሉም ለጥናት ከተሰበሰቡ በኋላ ምን ይጠና እያሉ ማሰብ ተስፋ ከማስቆረጡና ጠቃሚ የሆነውን የጥናት ጊዜ ከማቃጠሉ ባሻገር የሚፈይደው ምንም ነገር አይኖርም። ሁኔታው እንዲህ ከሆነ ልጆች በጉጉት የሚጠባበቁት ነገር እንዳይኖርና ፍላጎታቸው እንዲጠፋ ያደርጋል። ስለዚህ የምታጠኑትን የማኅበሩን አንድ ጽሑፍ ቀደም ብላችሁ ምረጡ።

“ታማኝና ልባም ባሪያ” በጣም ብዙ ጽሑፎችን ያዘጋጀ በመሆኑ ከእነዚህ ጽሑፎች አንዱን መርጦ ማጥናት ይቻላል። (ማቴዎስ 24:​45-47) ምናልባት ቤተሰቡ እስከ አሁን ያላጠናውን አንድ መጽሐፍ ልትጠቀሙ ትችላላችሁ። ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለው መጽሐፍ በቋንቋችሁ የሚገኝ ከሆነ የተወሰኑ ክፍሎችን መርጦ ማጥናት ምንኛ አስደሳች ይሆናል! ለምሳሌ ያህል የመታሰቢያው በዓል ከመከበሩ በፊት ባሉት ሳምንታት ስለ ጌታ ራት ምሽት የሚናገረውን ርዕስ ልትከልሱ ትችላላችሁ። ብዙ ቤተሰቦች በሳምንቱ ውስጥ የሚጠናውን የመጠበቂያ ግንብ ጥናት በመዘጋጀት ደስታ ያገኛሉ። ሆኖም በመጠበቂያ ግንብ ውስጥ ከጥናት ርዕሰ ትምህርቱ በፊትና በኋላ የሚገኙት ተጨማሪ ርዕሶች ለጥናቱ ከፍተኛ እገዛ ያበረክታሉ። የቤተሰቡን መንፈሳዊ ፍላጎቶች ጠንቅቆ የሚያውቀው የቤተሰቡ ራስ የትኛው ጽሑፍ መጠናት እንዳለበት የመወሰን ኃላፊነት አለበት።

ማሪያ “ሁልጊዜ የምናጠናው ቀደም ብሎ የተመረጠ ጽሑፍ ነው” በማለት ተናግራለች። “ሆኖም አንድ ጥያቄ ከተነሳ ወይም በትምህርት ቤት አንድ ችግር ብቅ ካለ ተግባራዊ ማብራሪያ ወደምናገኝበት ጽሑፍ ዞር እንላለን።” ወጣቶች በትምህርት ቤት ስለሚገጥሟቸው ችግሮች፣ ከተቃራኒ ፆታ ጋር ተቀጣጥሮ ስለ መጫወት፣ የትርፍ ጊዜ ሥራን የመሰሉ ሌሎች ነገሮች በሚከሰቱበት ጊዜ የተለየ ትኩረት ይሰጥባቸዋል። እነዚህ ነገሮች በሚያጋጥሙበት ጊዜ በጊዜው የተፈጠረውን ችግር የሚያብራራ ርዕሰ ትምህርት ወይም ጽሑፍ ምረጡ። ከቤተሰባችሁ ጋር ወዲያውኑ ማጥናት የምትፈልጓቸው ሐሳቦች በቅርብ ጊዜ በወጡ የመጠበቂያ ግንብ ወይም የንቁ! መጽሔት እትሞች ውስጥ ካያችሁ እነርሱን ለማጥናት ዝግጅት ከማድረግ ወደኋላ አትበሉ። እርግጥ ነው የሚደረገውን ለውጥ ቀደም ብላችሁ ለቤተሰባችሁ አባላት ማሳወቅ ትፈልጉ ይሆናል። ሆኖም አስፈላጊ የሆኑትን ነጥቦች አንድ ጊዜ ከተመለከታችሁ በኋላ ቀደም ብላችሁ ታጠኑት ወደነበረው ፕሮግራም መመለሳችሁን እርግጠኞች ሁኑ።

አካባቢው ጸጥታ የሰፈነበት ይሁን

ትምህርትን በተሻለ መንገድ ለመቅሰም ጸጥታ የሰፈነበት አካባቢ ከፍተኛ አስተዋዕኦ ያበረክታል። (ያዕቆብ 3:​18) ስለዚህ ዘና የሚያደርግ ሆኖም ጸጥታ የሰፈነበት ቦታ ምረጡ። በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖር አንድ የቤተሰብ ራስ ሲናገር “የምናጠናው ሳሎን ክፍል ተቀምጠንም ይሁን በረንዳ ላይ ሆነን ሰፋ ባለ ክፍል ውስጥ ራቅ ራቅ ብለን ከመቀመጥ ይልቅ አጠገብ ለአጠገብ ሆነን ለመቀመጥ እንጥራለን። ይህም የመቀራረብ ስሜት ይፈጥርልናል።” እንዲሁም ማሪያ “በሳምንቱ ውስጥ የሚደረገውን ጥናት በየትኛው ክፍል እንደምናደርግ እህቴና እኔ እንድንመርጥ እንጠየቅ ነበር። ይህም የደስታ ስሜት ይፈጥርልን ነበር” በማለት ትናገራለች። በቂ ብርሃን፣ አመቺ የሆነ የአቀማመጥ ሥርዓት፣ ደስ የሚልና ያልተዝረከረከ ቦታ ጸጥታ ለሰፈነበት አካባቢ አስተዋፅዖ እንደሚያደርግ አትዘንጉ። ከጥናት በኋላ ቤተሰቡ አብሮ ምግብ ቢመገብ ምሽቱ የበለጠ አስደሳች እንዲሆን ያደርገዋል።

አንዳንድ ቤተሰቦች ጥናቱ የበለጠ የሚማርክ እንዲሆንና የተለያየ ዓይነት ሐሳብ ለማግኘት ሲሉ አልፎ አልፎ ሌሎች ቤተሰቦችን በጥናት ፕሮግራማቸው ላይ እንዲገኙ ይጋብዛሉ። በቅርቡ ወደ እውነት የመጡ አዳዲስ ሰዎች በዚህ ዝግጅት እንዲገኙ በሚጋበዙበት ጊዜ ተሞክሮ ያካበተ አንድ የቤተሰብ ራስ የቤተሰብ ጥናት ሲመራ በመመልከት ሊጠቀሙ ይችላሉ።

መጽሐፍ ቅዱስን ሕያው ማድረግ

የጥናቱን ክፍለ ጊዜ ለልጆች ሕያው ካደረጋችሁት የጥናቱን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃሉ። ትንንሽ ልጆች አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪኮችንና ቦታዎች በሥዕል እንዲያስቀምጡ በማበረታታት ይህንን ልታደርጉ ትችላላችሁ። ተስማሚ በሚሆንበት ጊዜም ልጆች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ታሪኮችንና ድራማዎችን አስመስለው እንዲሠሩ አድርጉ። ትንንሽ ልጆችን በጥያቄና መልስ በሚደረግ የጥናት ዘዴ ብቻ ማስተማር አስፈላጊ አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኙት ገጸ ባሕርያት ማንበብ ወይም መተረክ አምላክ ያወጣቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች በልባቸው ውስጥ ለመቅረጽ አስደሳች የሆነ መንገድ ነው። ቀደም ብሎ የተጠቀሰው ሮበርት “አንዳንድ ጊዜ የቤት ሥራ ይሰጠንና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ባለ ታሪኮችን ተራ በተራ እየተቀባበልን እናነብ ነበር” በማለት ተናግሯል። ልጆች የሚወክሏቸውን በንባቡ ውስጥ የሚገኙትን ገጸ ባሕርያት ራሳቸው እንዲመርጡ ማድረግ ይቻላል።

በዕድሜ ከፍ ያሉ ልጆች እየተጠና ባለው ትምህርት ውስጥ ያሉትን አካባቢዎችና ቦታዎች በዓይነ ሕሊናቸው እንዲስሉ ለማድረግ ካርታዎችንና ሰንጠረዦችን መጠቀም ይረዳቸዋል። በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው በጉዳዩ ላይ ትንሽ በማሰብ የቤተሰብ ጥናትን ሕያውና ማራኪ ማድረግ ይቻላል። ልጆቹም ለአምላክ ቃል ትልቅ ጉጉት ያድርባቸዋል።​—⁠1 ጴጥሮስ 2:​2, 3

ሁሉም ተሳታፊ እንዲሆኑ መርዳት

ልጆች በጥናቱ እንዲደሰቱ ለማድረግ ተሳታፊ መሆን እንዳለባቸው ማወቅ ይኖርባቸዋል። እርግጥ ነው የተለያየ የእድሜ ደረጃ ያላቸውን ልጆች በጥናቱ እንዲሳተፉ ማድረግ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት “የሚመራም በመምራቱ ይትጋ” ይላል። (ሮሜ 12:​8 NW) ግለት የሚጋባ ነገር ስለሆነ ግለት ማሳየት ይረዳል።

ሮናልድ፣ ዲና የምትባለውን የአምስት ዓመት ሴት ልጁን እየተጠና ባለው ክፍል ውስጥ ያሉትን ንዑስ ርዕሶች እንድታነብ በማድረግና በሥዕሉ ላይ ተመሥርታ ሐሳብ እንድትሰጥ በመጠየቅ በጥናቱ ተሳታፊ እንድትሆን ያደርጋታል። ባለፈው ዓመት የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በተቃረበበት ጊዜ እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ ሰውc በተባለው መጽሐፍ ውስጥ በሚገኙት ሥዕሎች ላይ ትኩረት አድርጎ ነበር። “ይህ የበዓሉን ትርጉም እንድትረዳ ረድቷታል” በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል።

ሮናልድ፣ ሚሻ ለተባለችው አሥር ዓመት ሴት ልጁ አንድ ተጨማሪ እርምጃ ወስዷል። “ሚሻ ሥዕሎቹ ምን እንደሚያመለክቱ ብቻ ሳይሆን ምን ትርጉም እንደሚያስተላልፉ የመረዳት ችሎታ ላይ ደርሳለች” በማለት ሮናልድ ይናገራል። “በዚህም የተነሳ ራእይ​—⁠ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል!d የተባለውን መጽሐፍ በምናጠናበት ጊዜ ሥዕሎቹ በሚያስተላልፉት ትርጉም ላይ ትኩረት አድርገን ነበር። ይህም በጣም ጠቅሟታል።”

ልጆች ወደ አሥራዎቹ እድሜያቸው በሚገቡበት ጊዜ እየተጠና ያለው ጽሑፍ የሚሰጠውን ተግባራዊ ጠቀሜታ እንዲገልጹ ጋብዟቸው። ጥናቱ እየተካሄደ እያለ ጥያቄ በሚነሳበት ጊዜ ምርምር እንዲያደርጉ የቤት ሥራ ስጧቸው። ሮበርት፣ ፖል የተባለው የ12 ዓመት ልጁ ዳንጂዮስ እና ድራጎን የተባለውን ጨዋታ አካቶ ስለያዘው በትምህርት ቤታቸው ውስጥ በቅርቡ ስለተከፈተ አንድ አዲስ ክለብ አስመልክቶ ጥያቄ ባቀረበ ጊዜ እንዲህ አድርጎ ነበር። ፖል እና ሌሎች የቤተሰቡ አባላት የመጠበቂያ ግንብ ርዕስ ማውጫ ተጠቅመው መረጃዎችን አሰባሰቡና በቤተሰብ ጥናታቸው ወቅት ተወያዩበት። “በውጤቱም” ይላል ሮበርት “ጨዋታው ለክርስቲያኖች ተገቢ እንዳልሆነ ፖል ወዲያው ተገነዘበ።”

በተጨማሪም ሮበርት በሌላ ጊዜ ምርምር እንዲያደርጉ ደለደለ። ባለቤቱ ናንሲ “ስለ ኢየሱስ ሐዋርያት ምርምር በምናደርግበት ጊዜ ሁላችንም በየሳምንቱ ስለ አንድ ሐዋርያ ምርምር አድርገን እንድንመጣ እንመደብ ነበር። ልጆቹ ያገኙትን ዘገባ በቤተሰብ ጥናቱ ላይ በጋለ ስሜት ሲያቀርቡ መመልከት እንዴት የሚያስደስት ነበር!” በማለት ትናገራለች። ልጆች ራሳቸው ምርምር ሲያደርጉና ያገኙትንም መረጃ ለቤተሰቡ ሲያካፍሉ ‘በይሖዋ ፊት’ እንዲያድጉ ይረዳቸዋል።​—⁠1 ሳሙኤል 2:​20, 21

የአመለካከትም ሆነ መሪ ጥያቄዎችን መጠየቅ ልጆች በጥናቱ ወቅት ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚረዳ ጥሩ ዘዴ ነው። ታላቁ አስተማሪ ኢየሱስ “ምን ይመስልሃል?” የሚሉ የመሰሉ የአመለካከት ጥያቄዎችን ይጠይቅ ነበር። (ማቴዎስ 17:​25) ማሪያ “ከመካከላችን ማናችንም ጥያቄ በሚኖረን ጊዜ ወላጆቻችን በቀጥታ መልስ ሰጥተውን አያውቁም” በማለት ትናገራለች። “ጉዳዩን በጥሞና እንድናስብበት ለመርዳት ሁልጊዜ መሪ ጥያቄዎችን ይጠይቁናል።”

በነፃነት የሐሳብ ልውውጥ አድርጉ እንጂ አትቆጡ!

በጥናቱ ላይ የተገኙት ሁሉ ይፌዝብኛል ብለው ሳይፈሩ ያላቸውን አመለካከትና የሚሰማቸውን ስሜት አውጥተው መናገር የሚችሉ ከሆነ የቤተሰብ ጥናቱ ደስታ የበለጠ ይጨምራል። ይሁን እንጂ “የቤተሰብ ጥናት በሚደረግበት ወቅት ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ሊኖር የሚችለው የንግግር መሥመሩ በሌላ ጊዜም ክፍት ከሆነ ብቻ ነው” በማለት አንድ አባት ይናገራል። “ለጥናቱ ክፍለ ጊዜ ብቻ ልትከፍቱት አትችሉም።” በተቻለ መጠን ሁሉ ‘በቃ የምትናገረው ይኸው ብቻ ነው? እኔ ደግሞ ቁም ነገር የምትናገር መስሎኝ ነበር’፤ ‘የሞኝ አነጋገር ነው’፤ ‘ድሮስ ከአንተ ምን ይጠበቃል? ልጅ አይደለህ’ እንደሚሉት ያሉ ሳይታሰብ ሊያቆስሉ የሚችሉ ሐሳቦችን ከመሰንዘር መቆጠብ አለባችሁ። (ምሳሌ 12:​18) ለልጆቻችሁ ርኅራኄንና ምሕረትን አሳዩአቸው። (መዝሙር 103:​13፤ ሚልክያስ 3:​17) በልጆቻችሁ ተደሰቱ እንዲሁም የተማሯቸውን ነገሮች በሥራ ላይ ለማዋል በሚያደርጉት ጥረት ድጋፍ ስጧቸው።​—⁠ምሳሌ 29:​17

የቤተሰብ ጥናቱ የልጁ አእምሮ ትምህርቱን መቀበል በሚችልበት ሁኔታ መካሄድ ይኖርበታል። “ልጆቻችሁን መቅጣት በምትጀምሩበት ጊዜ” ይላል አራት ልጆቹን ጥሩ አድርጎ ያሳደገ አንድ ወላጅ “በቅሬታ የተሞሉ አድማጮች ይኖሯችኋል።” ይህን የመሰለ መንፈስ ባለበት ቦታ የሚሰጠው ማብራሪያ ጠልቆ አይገባም። ስለዚህ የጥናቱን ወቅት ተግሳጽና ቅጣት የሚሰጥበት ክፍለ ጊዜ ከማድረግ መቆጠብ ይኖርባችኋል። ተግሳጽና ቅጣት መስጠት አስፈላጊ ከሆነም ከጥናት በኋላ ለብቻቸው አድርጉት።

ጥረት ሊደረግለት የሚገባው ነው

በመንፈሳዊ የበለጸገ ቤተሰብ መገንባት ጊዜና ጥረት ይጠይቃል። ሆኖም መዝሙራዊው “እነሆ፣ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው፣ የሆድም ፍሬ የእርሱ ዋጋ ነው” በማለት ገልጿል። (መዝሙር 127:​3) እንዲሁም ወላጆች ‘[ልጆቻቸውን] በጌታ ምክርና ተግሣጽ የማሳደግ’ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። (ኤፌሶን 6:​4) ስለዚህ ውጤታማና የሚያስደስት የቤተሰብ ጥናት የመምራት ችሎታ አዳብሩ። ልጆቻችሁ ‘ወደ መዳን እንዲያድጉ’ ለማድረግ “ተንኮል የሌለበትን የቃልን ወተት” ለመስጠት የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ።​—⁠1 ጴጥሮስ 2:​2፤ ዮሐንስ 17:​3

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በዚህ ርዕስ ውስጥ የቀረቡት ብዙዎቹ ሐሳቦች በቤተሰብ ጥናት ልጆችን ስለመርዳት የሚያተኩሩ ቢሆንም መሠረታዊ ሐሳቦቹ ግን ልጆች በሌሉባቸው ቤተሰቦች ውስጥ ለሚደረገው የቤተሰብ ጥናትም ሊሠሩ የሚችሉ ናቸው።

b አንዳንዶቹ ስሞች ተለውጠዋል።

c ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።

d ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ