ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እንዲኖሩን ይፈለጋል
1 ይሖዋ አምላክ ምድራዊ ድርጅቱን በማያቋርጥ እድገት እየባረከው ነው። ባለፈው የአገልግሎት ዓመት በዓለም ዙሪያ 375,923 አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ተጠምቀዋል። ይህም በአማካይ በቀን ከ1,000 የሚበልጡ ወይም በሰዓት ወደ 43 የሚሆኑ ሰዎች ተጠምቀዋል ማለት ነው! ወንድሞቻችን ለብዙ አሥርተ ዓመታት መከራ ቢደርስባቸውም በተለያዩ የምድር ክፍሎች የመንግሥቱ ሥራ እየተስፋፋና ከፍተኛ እድገትም እየተገኘ ነው። ምሥራቹን በማዳረስ ረገድ የተደረገውን እድገት ማንበብ ምንኛ የሚያስደስት ነው!
2 ባለፈው ዓመት በእኛ ቅርንጫፍም የአስፋፊዎችና የረዳት አቅኚዎች ቁጥር በአማካይ እንደጨመረ ተመልክተናል። በመታሰቢያው በዓል ላይ አዲስ ከፍተኛ የተሰብሳቢ ቁጥር ተገኝቷል። ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመምራት በኩልስ እንዴት ነበር? ጠቅላላ የተመላልሶ መጠየቅ ቁጥር ሲቀንስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ቁጥር ደግሞ 17 በመቶ ቀንሷል። ይሁን እንጂ ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ ለማከናወን እነዚህ የአገልግሎት ዘርፎች አስፈላጊ ናቸው። የተመላልሶ መጠየቅና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ቁጥር ከማሽቆልቆል ይልቅ እያሻቀበ እንዲሄድ እያንዳንዳችን ምን ማድረግ እንችላለን?
3 ጥናት ለመምራት ያለንን ፍላጎት እንጨምር፦ መንፈሳዊነታችንን ለማጠናከርና ንቁ ለመሆን ትኩረት መስጠት ያስፈልገናል። እውነተኛ የክርስቶስ ተከታዮች ‘መልካም ለማድረግ የሚቀኑ’ ናቸው። (ቲቶ 2:14) አገልግሎታችንን መለስ ብለን ብንመለከት ጽሑፍ ያበረከትንላቸውን ሰዎች ተከታትለን በመርዳት በኩል ትጉዎች ነን ለማለት እንችላለን? ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምሩ በቅንዓት ግብዣ እናቀርብላቸዋለን? (ሮሜ 12:11) ወይስ ተመላልሶ መጠየቅና የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማስጀመር ረገድ ቅንዓታችንን መኮትኮት ያስፈልገን ይሆን?
4 የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፣ አዘውትሮ መሰብሰብና ጽሑፎችን ማጥናት መንፈሳዊነታችን ሕያው ሆኖ እንዲቀጥልና በአምላክ መንፈስ እንድንሞላ ያስችለናል። (ኤፌ. 3:16-19) ይህም በይሖዋ ላይ ያለን እምነትና ትምክህት እንዲሁም ለሰዎች ያለን ፍቅር እንዲጨምር ያደርጋል። አገልግሎታችንን የሚስብ፣ የተሳካና የሚያነቃቃ በማድረግ እውነትን ለሌሎች ሰዎች ለመንገር የምንነሳሳ እንሆናለን። አዎን፣ ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መፈለግ ይኖርብናል!
5 በመጀመሪያ ከቤተሰባችሁ ጋር አጥኑ፦ አብረዋቸው የሚኖሩ ልጆች ያላቸው ክርስቲያን ወላጆች ቋሚ ስለሆነ የቤተሰብ ጥናት ፕሮግራም ሊያስቡበት ይገባል። (ዘዳ. 31:12፤ መዝ. 148:12, 13፤ ምሳሌ 22:6) አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለውን ብሮሹርና ከዚያም እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ቢያጠኑ ያልተጠመቁ አስፋፊዎች እንዲሆኑ፣ ራሳቸውን እንዲወስኑና ለጥምቀት እንዲበቁ ለማዘጋጀት በጣም ሊጠቅማቸው ይችላል። እርግጥ የልጁን ፍላጎትና እድሜ ግምት ውስጥ በማስገባት ተጨማሪ ጽሑፎች ማጥናት ያስፈልግ ይሆናል። አንድ ወላጅ ያልተጠመቀ ልጁን ሲያስጠና በሚያዝያ 1987 የመንግሥት አገልግሎታችን የጥያቄ ሣጥን ላይ በወጣው መሠረት ጥናት፣ ሰዓትና ተመላልሶ መጠየቅ መመዝገብ ይችላል።
6 የተደራጀህ በመሆን ረገድ አሻሽል፦ የተበረከቱትን መጽሔቶች፣ ብሮሹሮችና መጽሐፎች ስንመለከት ብዙ ዘር ተዘርቶ እንዳለ ምንም ጥርጥር የለውም። እነዚህ የተዘሩ የእውነት ዘሮች አዳዲስ ደቀ መዛሙርትን ሊያፈሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ አንድ ገበሬ ወይም አትክልተኛ በየጊዜው እየዘራ ነገር ግን ተመልሶ አዝመራውን የማይሰበስብ ከሆነ የድካሙን ውጤት ሊያገኝ ይችላልን? በፍጹም። በተመሳሳይም በአገልግሎታችን ተከታትለን መርዳታችን አስፈላጊ ነው።
7 ዘወትር ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ጊዜ ትመድባለህን? ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ስታገኝ ወዲያውኑ ተመልሰህ ሂድ። ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርግ ግብህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ይሁን። የተመላልሶ መጠየቂያ መመዝገቢያህ ንጹሕ፣ የቅርብ ጊዜና በደንብ የተደራጀ ነውን? ከሰውየው ስምና አድራሻ በተጨማሪ በመጀመሪያ ያነጋገርክበትን ቀን፣ ያበረከትከውን ጽሑፍ፣ ስለ ተወያያችሁት ነገር አጠር በማድረግ እንዲሁም ተመልሰህ በምትሄድበት ወቅት በምን ነጥብ ላይ እንደምትወያዩ መመዝገብህን እርግጠኛ ሁን። ከእያንዳንዱ ተመላልሶ መጠየቅ በኋላ ተጨማሪ ነገር ለመመዝገብ እንዲመችህ ክፍት ቦታ ተው።
8 እንዴት አድርገህ ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ እንዳለብህ አገናዝብ፦ ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርግ ልታስብባቸው የሚገቡ ነጥቦች ምንድን ናቸው? (1) ሞቅ ያለ ስሜት ያለህ፣ ወዳጃዊ፣ በቅንዓት የምትናገርና የስብከት ዓይነት አቀራረብ የሌለህ ሁን። (2) ሰውየውን በሚስበው ጥያቄ ወይም ርዕስ ላይ ተወያይ። (3) ውይይቱን ቀላልና ቅዱስ ጽሑፋዊ አድርገው። (4) በእያንዳንዱ ጉብኝትህ ላይ ሰውየው የሚወያየው ነገር ለእሱ ጥቅም እንዳለው እንዲረዳ አድርግ። (5) በሚቀጥለው ጉብኝትህ የምትወያዩበትን ርዕስ በጉጉት እንዲጠባበቅ አድርግ። (6) ረጅም ሰዓት አትቆይ። (7) የቤቱን ባለቤት ሊያሳፍረው ወይም ዝቅ ሊያደርገው የሚችል ጥያቄ አትጠይቀው። (8) መንፈሳዊ አድናቆቱ ገና ሳይጠናከር ስለተሳሳተ አመለካከቱ ወይም ስለ መጥፎ ልማዱ እንዳትነቅፈው መጠንቀቅ ይኖርብሃል። ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማስጀመር በኩል ስኬታማ መሆን ስለሚቻልበት መንገድ ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት መጋቢት 1997 የመንግሥት አገልግሎታችን ገጽ 8-10 ተመልከት።
9 አጋጣሚዎችን ሁሉ ፈልግ፦ በአንድ ጉባኤ ውስጥ ከፍተኛ የጸጥታ ጥበቃ በሚደረግባቸው ሕንጻዎች ውስጥ ተከራይተው የሚኖሩ ሰዎችን ስምና የቤት ቁጥር ማግኘት ይቻል ነበር። ለእያንዳንዱ ነዋሪ ደብዳቤና ሁለት ትራክቶች ተላከ። መልእክቱ የሚደርሰው ሰው ምላሽ እንዲሰጥ በደብዳቤው መጨረሻ ላይ ነጻ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ግብዣና በአካባቢው ነዋሪ የሆኑ ወንድሞች የስልክ ቁጥር አብሮ በመጻፍ ተላከ። ከጥቂት ቀናት በኋላ አንድ ወጣት ስልክ በመደወል ጥናት ለማጥናት ጠየቀ። በሚቀጥለው ቀን ተመላልሶ መጠየቅ ከተደረገለት በኋላ በእውቀት መጽሐፍ ጥናት ተጀመረለት። በዚያኑ ዕለት ምሽት በጉባኤ መጽሐፍ ጥናት ላይ ከተገኘ በኋላ በሁሉም ስብሰባዎች ላይ መገኘቱን ቀጠለ። ብዙም ሳይቆይ በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ጀመረና ወደ ጥምቀት የሚያደርሰውንም ቀጣይ እድገት አደረገ።
10 በአንድ ቡድን የሚገኙ አስፋፊዎች በህብረት ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ዝግጅት አደረጉ። አንዲት እህት ከዚህ በፊት ወደ አነጋገረቻት ሴት ቤት ብትሄድም አላገኘቻትም፤ ይሁን እንጂ በሩን የከፈተችላት ወጣት ሴት “እናንተን ስጠብቅ ነበር” በማለት መልስ ሰጠቻት። ይህች ሴት ከአንድ የምታውቀው ሰው እውቀት የተባለውን መጽሐፍ አግኝታ ነበር። እህቶች ባገኟት ወቅት ይህች ሴት መጽሐፉን ሁለት ጊዜ አንብባ በውስጡ ባለው ሐሳብ በጣም ተነክታ ነበር። የዚያን ዕለት ምሥክሮቹ እቤቷ መምጣታቸው ይህችን ሴት አልገረማትም፤ ምክንያቱም እንዲመጡና ጥናት እንዲጀምሩላት ወደ አምላክ ጸልያ እንደነበር ተናግራለች። ጥናት ተጀመረ፤ በጉባኤ ስብሰባዎች መገኘት ጀመረች እንዲሁም በፍጥነት እድገት አደረገች።
11 ከተጠመቀች ወደ 25 ዓመት ገደማ የሆናት አንዲት እህት በቅርብ ጊዜ ለእናቷ እውቀት መጽሐፍ ሰጠቻት። የቤተ ክርስቲያን አባል የሆነችው እናቷ መጽሐፉን ማንበብ ትጀምራለች። ሁለት ምዕራፎች አንብባ ከጨረሰች በኋላ ልጅዋን ጠርታ “የይሖዋ ምሥክር መሆን እፈልጋለሁ!” በማለት ልጅዋ ያልጠበቀችውን መልስ ሰጠቻት። እናትየው ጥናት ጀመረች፤ አሁን ተጠምቃለች።
12 እነዚህን ሐሳቦች ሞክር፦ ጥናት ለማስጀመር ቀጥተኛ አቀራረብ ተጠቅመህ ታውቃለህን? በቀላሉ እንዲህ ማለት ትችላለህ:- “ያለ ክፍያ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲመራልዎ ከፈለጉ እንዴት እንደሚመራ በጥቂት ደቂቃ ውስጥ ላሳይዎ እችላለሁ። ከተደሰቱበት መቀጠል ይችላሉ።” ብዙ ሰዎች ይህን የመሰለውን ግብዣ ሳያቅማሙ ከመቀበላቸውም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱን ሠርቶ ማሳያ በፈቃደኝነት ሊከታተሉ ይችላሉ።
13 ጥናት ከመጀመሩ በፊት ተማሪው የተጠቀሱትን ጥቅሶች በማንበብና ቁልፍ በሆኑ ነጥቦች ላይ በማስመር በጽሑፉ ላይ ለሰፈሩት ጥያቄዎች መልስ አስቀድሞ እንዴት እንደሚዘጋጅ አሳየው። በትምህርቱ ዋና ነጥቦች ላይ ብቻ ትኩረት አድርግ። ምንም እንኳ ጥናቱ እንደተጀመረ አካባቢ የጥናት ፕሮግራሙን እንደ አስፈላጊነቱ መቀያየር ቢቻልም እየዋለ ሲያድር ግን ፕሮግራሙን ቋሚ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ጸሎት አስፈላጊ የጥናቱ ክፍል እንደሆነ እንዴት እንደምታስተዋውቀውና ለሚመጣበት ተቃውሞ እንዴት በቅዱስ ጽሑፉ እንደምታስታጥቀው አስብ። ባለህ አጋጣሚ ሁሉ በመጠቀም ጥናቱን ማራኪ አድርገው!
14 እርግጥ ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እኩል እድገት አያደርጉም። አንዳንድ ሰዎች ለመንፈሳዊ ነገር እንደሌሎች ዝንባሌ አይኖራቸው ይሆናል አለዚያም የሚማሩትን ነገር በቶሎ አይረዱ ይሆናል። ሌሎች ሰዎች ደግሞ በሥራ የተወጠረ ሕይወት ስለሚመሩ በየሳምንቱ አንድ ሙሉ ምዕራፍ ለመጨረስ ጊዜ ላያገኙ ይችላሉ። ስለዚህ ባሉት አንዳንድ ሁኔታዎች አንዱን ምዕራፍ ለመሸፈን ከአንድ በላይ የጥናት ክፍለ ጊዜ መጠቀም እንዲሁም መጽሐፉን ለመጨረስ ተጨማሪ ወራት ያስፈልገን ይሆናል። በአንዳንድ ሁኔታዎች አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለውን ብሮሹር ካስጠናን በኋላ ወደ እውቀት መጽሐፍ ልንሸጋገር እንችላለን። ከጥናቱ በተጨማሪ በጉባኤ ስብሰባዎች መገኘታቸው በእውነት ላይ በጥብቅ የተመሠረቱ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል።
15 ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ለማግኘት ጸልዩ! (1 ዮሐ. 3:22) አንድን ሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለማድረግ ይሖዋ በአንድ ክርስቲያን ሲጠቀምበት ከሁሉም በላይ ወሮታ የሚከፍል ተሞክሮ ያገኛል። (ሥራ 20:35፤ 1 ቆሮ. 3:6-9፤ 1 ተሰ. 2:8) ይሖዋ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ለማግኘት የምናደርገውን ጥረት እንደሚባርከው ሙሉ በሙሉ በመመካት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማስጠናቱ ሥራ ከፍተኛ ቅንዓት የምናሳይበት ጊዜ አሁን ነው!
[ከገጽ 3 የተቀነጨበ ሐሳብ ]
አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንድታገኝ ትጸልያለህን?