ተመላልሶ መጠየቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ያስችላል
1. ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
1 ኢየሱስ ለተከታዮቹ ምሥራቹን የመስበክ ብቻ ሳይሆን ‘እያስተማሩ ደቀ መዛሙርት’ የማድረግም ተልዕኮ ሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 28:19, 20) አንድ ሰባኪ ምሥራቹን የሚያውጅ ሲሆን አስተማሪ ግን ከዚያም የበለጠ ነገር ያደርጋል። ያስተምራል፣ ያብራራል እንዲሁም ማስረጃ ያቀርባል። ሌሎችን የምናስተምርበት አንደኛው መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የማስጀመር ግብ ይዘን ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ ነው።
2. ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ ያለብህ ለእነማን ነው?
2 ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ ያለብህ ለእነማን ነው? ጽሑፍ ለወሰዱ ወይም ለምሥራቹ መጠነኛ ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች በሙሉ ተመላልሶ መጠየቅ ልታደርግላቸው ይገባል። ፍላጎት ያሳየ ሰው ያገኘኸው እቤቱ ካልሆነ ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ እንድትችል አድራሻውን ወይም ስልክ ቁጥሩን ጠይቀው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመርን በተመለከተ አዎንታዊ አመለካከት ይኑርህ። “ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ማወቅ ትፈልጋለህን?” በተባለው ትራክት ተጠቀም። መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ፈቃደኛ የሚሆኑ ሰዎችን ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት አታቋርጥ፤ እንዲህ ካደረግህ ሊሳካልህ ይችላል።—ማቴ. 10:11
3, 4. ውጤታማ ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ ምን ነገሮችን ያካትታል?
3 ትኩረት ስጣቸው:- ውጤታማ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ዝግጅቱ የሚጀምረው መጀመሪያ ምሥራቹን ስንነግራቸው ነው። በወንጌላዊነቱ ሥራ ስኬታማ የሆኑ አስፋፊዎች በሥርዓት የተያዘ ጥሩ ማስታወሻ አላቸው። የቤቱ ባለቤት ምን ነገር እንደሚያሳስበው ማስታወሻ የሚይዙ ሲሆን ይህን ለቀጣዮቹ ውይይቶች መንደርደሪያ አድርገው ይጠቀሙበታል። አንዳንዶች የቤቱ ባለቤት ቀጣዩን ውይይት በጉጉት እንዲጠባበቅ ለማድረግ በውይይታቸው ማብቂያ ላይ ጥያቄ ማንሳት ጠቃሚ እንደሆነ ተገንዝበዋል። ለሰዎች ያለን ልባዊ አሳቢነት ከተለየናቸውም በኋላ ስለ እነርሱ እንድናስብና ምንም ሳንዘገይ ተመልሰን እንድንጠይቃቸው ይገፋፋናል። የሚያመችህ ከሆነ ፍላጎታቸው ሳይበርድ ምናልባትም ከአንድ ወይም ከሁለት ቀን በኋላ ተመልሰህ ጠይቃቸው።
4 ተመላልሶ መጠየቅ በምታደርግበት ጊዜ በፊት በጀመራችሁት ርዕሰ ጉዳይ ለመቀጠል ጥረት አድርግ። በእያንዳንዱ ተመላልሶ መጠየቅ ቢያንስ አንድ የሚያንጽ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳብ የማካፈል ግብ ይኑርህ፤ ሰውዬው የሚናገረውንም አዳምጥ። የቤቱን ባለቤት በደንብ ለማወቅ ጥረት አድርግ። ከዚያም በቀጣዮቹ ጊዜያት እርሱን ስለሚያሳስቡት ጉዳዮች የሚናገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች አካፍለው።
5. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር የትኛውን ቀላል አቀራረብ መጠቀም ይቻላል?
5 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ንቁ ሁን:- ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርግ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የማስጀመር ግብ ይኑርህ። ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? አንድ ጥሩ ሐሳብ ልታካፍለው እንደምትፈልግ ግለጽለት። ከዚያም እውቀት መጽሐፍ ወይም አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ብሮሹር ላይ የሰውዬውን ትኩረት ሊስብ የሚችል ሐሳብ የሚገኝበት አንድ አንቀጽ አውጣ። አንቀጹን ካነበብክ በኋላ ጥያቄውን ጠይቅ፤ በአንቀጹ ላይ ከተጠቀሱት መካከል አንድ ወይም ሁለት ጥቅሶች አንብበህ አብራራ። ሁኔታው የሚፈቅድ ከሆነ እዚያው በሩ ላይ እንዳለህ ከአምስት እስከ አሥር ደቂቃ ባለው ጊዜ ውስጥ ይህን ማድረግ ትችላለህ። ከዚያ ቀጥሎ ያለውን ጥያቄ አንብብና በሌላ ጊዜ ውይይቱን የምትቀጥሉበትን ቀጠሮ ያዝ።
6. ተመላልሶ መጠየቅ የማድረግን አስፈላጊነት እንደተገነዘብን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
6 ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ተከታትሎ መርዳት የአገልግሎታችን ዐቢይ ገጽታ ነው። በመሆኑም በሳምንታዊ ፕሮግራምህ ውስጥ ተመላልሶ መጠየቅ የምታደርግበት ጊዜ መድብ። እንዲህ ማድረግህ በአገልግሎትህ ውጤታማ እንድትሆን የሚያስችልህ ከመሆኑም በላይ እውነተኛ ደስታ ያስገኝልሃል።