ትክክለኛ ዝንባሌ ያላቸውን እርዱ
1. በዚህ ዘመን ይሖዋ ወደ ቤቱ እየሰበሰበ ያለው ምን ዓይነት ሰዎችን ነው?
1 እያንዳንዱ ሰው በምሳሌያዊ ልቡ ውስጥ የተቀረጸ አንድ ዓይነት ዝንባሌ አለው። (ማቴ. 12:35) መጽሐፍ ቅዱስ “በልቡ . . . ሰልፍ” ስላለ ሰው ይናገራል። (መዝ. 55:21) አንዳንዶች ‘የቁጠኝነት’ ዝንባሌ ይታይባቸዋል። (ምሳሌ 29:22) ይሁን እንጂ ‘የዘላለም ሕይወት’ ለመውረስ የሚያስችል ትክክለኛ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎችም አሉ። (ሥራ 13:48) በዘመናችን ይሖዋ እንዲህ ዓይነት ትክክለኛ ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች ወደ ቤቱ እየሰበሰበ ነው። (ሐጌ 2:7) እነዚህ ሰዎች የይሖዋ አምላኪዎች እንዲሆኑ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?
2. ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ የተሰጠንን ተልእኮ ለመፈጸም ምን ማድረግ አለብን?
2 ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ትጉ:- ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ የተሰጠንን ተልእኮ መፈጸም እንድንችል ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግን በተመለከተ ትክክለኛ አመለካከት መያዛችን በጣም አስፈላጊ ነው። (ማቴ. 28:19, 20) ፍላጎት ያሳየ ሰው ስናገኝ ፍላጎቱን ለማሳደግ ትጋት እናሳያለን? ጽሑፍ የወሰዱ ወይም ለምስራቹ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን በሙሉ ተመልሰን እንጠይቃቸዋለን? በመንፈሳዊ እንዲያድጉ በምናደርገው ጥረት በጽናት እንቀጥላለን? ጉዳዩ የሰዎችን ሕይወት የሚመለከት በመሆኑ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን በሙሉ ተከታትለን መርዳት ይኖርብናል።
3. አገልግሎት ላይ አንድን ሰው ካነጋገርን በኋላ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
3 ፍላጎት ካሳየ ሰው ጋር ያደረግነው ውይይት ከአእምሯችን ሳይጠፋ ቆም ብለን ስሙንና አድራሻውን መጻፍ ይኖርብናል። የተወያያችሁበትን ርዕሰ ጉዳይ፣ ያነበባችሁለትን ጥቅስና ያበረከታችሁለትን ጽሑፍ ጻፉ። ከዚያም ሳትዘገዩ ተመልሳችሁ ለማነጋገር ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ።
4. ውጤታማ ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
4 ተመላልሶ መጠየቅ የምናደርግበት መንገድ:- ተመልሳችሁ በምትሄዱበት ጊዜ ሰውየውን ሞቅ ባለና ወዳጃዊ በሆነ መንፈስ ማነጋገር እንዲሁም ለሰውየው ልባዊ አሳቢነት ማሳየት አስፈላጊ ነው። ውይይቱን ለመረዳት የማያስቸግርና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያተኮረ አድርጉት። የሰውየውን ትኩረት የሚስብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አርእስት ተዘጋጅታችሁ ሂዱ፣ በውይይታችሁ ማብቂያ ላይ በሚቀጥለው ቀጠሯችሁ መልስ የምትሰጡበት አንድ ጥያቄ አንሱ። የቤቱ ባለቤት በሚናገራቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ አመለካከቶች ክርክር ውስጥ ከመግባት መራቁ የተመረጠ ነው። በምትግባቡበት አርእስት ዙሪያ ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ለማካፈል ጥረት አድርጉ።—ቆላ. 4:6
5. አንድ አቅኚ ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ ረገድ ምን ዓይነት ትጋት አሳይቷል? ምን ውጤትስ አግኝቷል?
5 ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ ጥረት የሚጠይቅ ቢሆንም የሚያስገኘው ወሮታ በጣም አስደሳች ነው። በጃፓን የሚኖር አንድ አቅኚ በየወሩ የሚያደርገውን ተመላልሶ መጠየቅ ለማሳደግ ግብ አወጣ። ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግል ያነጋገራቸውን ሰዎች ሁሉ መዝግቦ መያዝና በሰባት ቀን ውስጥ ተመልሶ ሄዶ ማነጋገር ጀመረ። ለተመላልሶ መጠየቅ ጥሩ ዝግጅት አድርጎ የሚሄድ ከመሆኑም በላይ አገልግሎቱን የሚያከናውነው በመልእክቱ ሙሉ በሙሉ በመተማመን ነበር። ተመላልሶ መጠየቅ ያደረገለት አንድ ሰው ጥናት የጀመረ ሲሆን እንዲህ ብሎ ተናግሯል:- “የእናንተ ሰዎች ከዚህ በፊት ሲያነጋግሩኝ አልፈልግም ብዬ እመልሳቸው ነበር። የምትሉትን ሳዳምጥ ይህ የመጀመሪያ ጊዜዬ ነው።” አቅኚው ሥራውን በትጋት ማከናወኑ ውጤት አስገኝቶለታል። በወሩ መጨረሻ ላይ አሥር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ሪፖርት አድርጓል።
6. ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ ረገድ ትጋት ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው?
6 ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ምንጊዜም ለውጥ ያጋጥማቸዋል። (1 ቆሮ. 7:31) ፍላጎት ያሳየን ሰው በድጋሚ ቤቱ ለማግኘት በአብዛኛው ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ትጋት በማሳየት ወደ ዘላለም ሕይወት በሚያመራው ጎዳና ላይ ለመጓዝ ትክክለኛ ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች መርዳት እንችላለን።—ማቴ. 7:13, 14