ውጤታማ ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ ቀደም ሲል ያሳዩትን ፍላጎት ገንባ
1 በሚገባ ዝግጅት የተደረገበት ንግግር ሁሉ ፍላጐት የሚያነሳሳ መግቢያ፣ ትምህርት የሚሰጥ አካልና ለሥራ የሚገፋፋ መደምደሚያ አለው። መግቢያው የአድማጮችን ትኩረት ይስባል። ያለ አካሉና ያለ መደምደሚያው ግን ንግግሩ ያልተሟላ ይሆናል። ይኸው መሠረታዊ ሥርዓት በአገልግሎታችንም ላይ ይሠራል። በመጀመሪያ ጉብኝታችን ላይ የቤቱን ባለቤት ፍላጐት ማነሳሳት ጥሩ ነው። ይሁን እንጂ ውጤታማ ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ ያንን በመጀመሪያ ያሳዩትን ፍላጐት መገንባታችንን መቀጠል አለብን።
2 አምላክ መከራ እንዲኖር ለምን ፈቀደ? እንዴት ያለ አእምሮን የሚቀሰቅስ ጥያቄ ነው! ይህ ጉዳይ በዛሬው ጊዜ በብዙ ሰዎች አእምሮ ውስጥ አለ ቢባል በዚህ አትስማማምን? ከላይ ባለው ርዕስ ውስጥ በመጀመሪያ ጉብኝትህ መደምደሚያ ላይ በተመላልሶ መጠየቅህ ወቅት እንደምትመልሰው በመንገር ይህንን ጥያቄ እንድታነሳ ሀሳብ የቀረበው በዚህ ምክንያት ነው።
3 እንዲህ ትል ይሆናል፦
◼ “ጤና ይስጥልኝ። ባለፈው ጊዜ ስንነጋገር አምላክ ክፋትን ስለመፍቀዱ ጉዳይ አንስተን ነበር። እኔም ተመልሼ ስመጣ አንዳንድ ሀሳቦችን ይዤ እንደምመጣ ቃል ገብቼለዎት ነበር። ብዙ ሰዎች አምላክ በእውነት የሚያስብልን ከሆነ መከራ እንዲቆም ያደርግ እንደነበር ይሰማቸዋል። ምናልባት እርስዎም እንዲሁ ይሰማዎት ይሆናል። [የቤቱ ባለቤት መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] አምላክ በእርግጥ እንደሚያስብልን መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጥልናል። [1 ዮሐንስ 4:8ን አንብብ።] አምላክ እስካሁን ድረስ ክፋት እንዲቆይ የፈቀደበት ጥሩ ምክንያቶች አሉት። ከነዚህም ምክንያቶች አንዱ በ2 ጴጥሮስ 3:9 ላይ ተብራርቷል። [አንብብ።] ሌሎቹ ምክንያቶች ደግሞ በዚህ ብሮሹር ውስጥ ተዘርዝረዋል።” ከዚያም አምላክ በእርግጥ ያስብልናልን? የሚለውን ብሮሹር ገጽ 12–14ን አውጣና በሚፈልገው ነጥብ ላይ አወያየው።
4 አንዳንድ ባለቤቶች ይበልጥ ዝርዝር ማብራሪያዎችን ስለሚፈልጉ በመልሱ ሙሉ በሙሉ መርካት እንዲችሉ በርከት ላለ ጊዜ ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ ያስፈልግ ይሆናል። በጥር ወር የሚበረከቱት ባለ 192 ገጽ የሆኑ በርካታ የማኅበሩ መጻሕፍት በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ መሠረት በመሆን የሚረዳ ምዕራፍ የያዙ ናቸው።
5 ውይይቱን ወደ መደምደሙ ስትቃረብ ሌላ ጥያቄ አንሳና ተመልሰህ ስትመጣ ጠቃሚ ሀሳቦችን ብታካፍለው ደስ እንደሚልህ ለቤቱ ባለቤት ንገረው። ብዙ ሰዎች ሰው ሲሞት ምን እንደሚሆን ለማወቅ ይፈልጋሉ። ይህንን ርዕስ አመቺ በሆነ ጊዜ ለመወያየት ለምን ዝግጅት አታደርጉም?
6 ሦስት መሠረታዊ ሥርዓቶችን በአእምሮህ መያዝህ በጣም ጠቃሚ ይሆናል። አያያዝህን ወይም አቀራረብህን እንደ ሁኔታው ለመለዋወጥ ፈቃደኛ ሁን። የቤቱ ባለቤት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለመወያየት የተወሰነ ሰዓት የመመደብ ልማድ የሌለው ይሆናል። አጠር አድርገህ ተናገር። በመጀመሪያ ጉብኝትህ ላይ ረጅም ጊዜ አትቆይ ወይም በጣም ብዙ ነጥቦችን አትሸፍን። ብዙውን ጊዜ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥቂት ነጥቦችን ብትሸፍን ለጉብኝትህ ይበልጥ መልካም የሆነ ምላሽ ይኖራል። ሞቅ ያለ ስሜት ያለህና ተግባቢ ሁን። በግለሰብ ደረጃ እንደምታስብለት ለቤቱ ባለቤት አሳየው።
7 የመጀመሪያው ግባችን የቤቱ ባለቤት በቅዱስ ጽሑፋዊው ውይይት ውስጥ እንዲገባ ማድረግ ነው። ከዚያም እንደ ዘላለም መኖር ባለ ተስማሚ በሆነ ጽሑፍ ፍሬያማ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር እንፈልጋለን። ውጤታማ የሆኑ ተመላልሶ መጠየቆችን በማድረግ ሰዎቹ በመጀመሪያ ያሳዩትን ፍላጐት በትዕግሥት የምትገነባ ከሆነ ያንን ደስታ ልታገኝ ትችላለህ።