ሰዎች ያሳዩትን አድናቆት ለመገንባት ተመልሶ መጠየቅ
1 ትርጉም ያለው ተመላልሶ መጠየቅ የቤቱ ባለቤት አማኝ ወደ መሆን የሚያደርገውን እድገት ደረጃ በደረጃ ሊያፋጥንለት ይችላል። ፍላጎት ያሳዩትን ተመልሰን ስንጠይቅ በአእምሯችን ልንይዛቸው የሚገቡን አንዳንድ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ሐሳቦች ምንድን ናቸው?
2 ከሁሉም በፊት በደንብ ተዘጋጅ። ይህ ገና ከመጀመሪያው ዕለት ውይይት ጀምሮ መደረግ ያለበት ነገር ነው። እንዲህ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? ፍላጎት ያሳዩትን ሰዎች በትክክል መዝግቦ በመያዝ ነው። የቤቱን ባለቤት ስም፣ የተወያያችሁበትን ርዕስ፣ የሰጠውን ምላሽ፣ የተበረከተ ጽሑፍም ካለ መዝግበህ ያዝ። ከዚያ ተመልሰህ ከመሄድህ በፊት ከቤት ወደ ቤት ስትሄድ የምትመዘግብበትን ማስታወሻ መለስ ብለህ ተመልከት፤ እንዲሁም ስለምትናገረው ነገር በጸሎት አስብበት።
3 አሁን ዝግጁ ነህ። ምን ለማለት ትችላለህ? በመጀመሪያው ዕለት ውይይታችሁ አንድ ጥያቄ ጠይቀኸው ሄደህ ከነበረ ተመልሰህ ስትሄድ በዚያው ርዕስ ላይ ልትቀጥል ትችላለህ። ለምሳሌ ያህል የመጀመሪያው ዕለት ውይይታቸሁ የአምላክ መንግሥት በምታመጣቸው በረከቶች ላይ ያተኮረ ከነበረ “አምላክ መከራ እንዲኖር ለምን ፈቀደ?” የሚለውን ጥያቄ ልታነሳ ትችላለህ።
ተመልሰህ ስትሄድ ራስህን ካስተዋወቅህ በኋላ እንዲህ ልትል ትችል ይሆናል፦
◼ “ባለፈው ጊዜ አፍቃሪው አምላክ ዛሬ የሚታየውን ይህንን ሁሉ ዓመፅ ለምን እንደፈቀደ ተወያይተን ነበር። ይህን ጉዳይ ይበልጥ አስበውበታል?” [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] አምላክ በእርግጥ ስለ ሰው ልጆች ይጨነቃል ብለው ያስባሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] እስቲ መጽሐፍ ቅዱስ በዮሐንስ 3:16 ላይ ምን እንደሚል ልብ ይበሉ።” ጥቅሱን ካነበብክ በኋላ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት በተባለው መጽሐፍ ውስጥ በምዕራፍ 8 ላይ አምላክ በዛሬው ጊዜ ያለውን ክፋት የታገሰበትን ምክንያት የሚጠቁሙትን የተወሰኑ ክፍሎች ልታሳየው ትችላለህ።
4 ሌላው በመጀመሪያው ዕለት ውይይታችሁ መደምደሚያ ላይ ልታነሳው የምትችለው ስሜት አመራማሪ ጥያቄ ደግሞ:– “አምላክ ሰዎች ለዘላለም እንዲኖሩ አስቦ ከነበረ ታዲያ ለምን ያረጃሉ ለምንስ ይሞታሉ?” የሚለው ነው። ተመልሰህ ስትሄድ መጽሐፍ ቅዱስ ለጥያቄው በሮሜ 5:12 ላይ የሚሰጠውን መልስ ልታሳያቸው ትችላለህ። ጥቅሱን ካነበብክ በኋላ ሕይወት ይህ ብቻ ነውን? በተባለው የእንግሊዘኛ መጽሐፍ ውስጥ ገጽ 35 ላይ ሰዎች የሚያረጁበትንና የሚሞቱበትን መሠረታዊ ምክንያት የሚያብራራውን የመጀመሪያ አንቀጽ ልታሳየው ትችላለህ።
5 በመጀመሪያው ቀን ውይይታችሁ እውነተኛው ሃይማኖት ተለይቶ ሊታወቅ የሚችልባቸውን መንገዶች ተወያይታችሁ የሰው ዘር አምላክን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ትተህለት ሄደህ ከነበረ ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርግ መነሻ የሚሆንህ ጥሩ ጥያቄ:- “እነዚህ ሁሉ ሃይማኖቶች እንዴት ሊመጡ ቻሉ?” የሚለው ሊሆን ይችላል። በተመላልሶ መጠየቁ ወቅት በዛው መጽሐፍ ምዕራፍ 2 ውስጥ ባሉት የተወሰኑ ነጥቦች ላይ ልትወያዩ ትችላላችሁ።
6 ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ነገር አለ። ተመልሰህ ስትሄድ በምታነሳቸው ጥያቄዎች ላይ ጥንቃቄ አድርግ። “የተውኩልዎትን ጽሑፍ አንብበውታል?” ወይም “እኔን ያስታውሱኛል?” ወይም ደግሞ “ባለፈው ጊዜ መጥቼ የተነጋገርንበትን ነገር ያስታውሳሉ?” እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎች የቤቱን ባለቤት ግራ የሚያጋቡ ናቸው። እንደነዚህ ዓይነት ጥያቄዎች ብዙውን ጊዜ ጥሩ ውጤት አይኖራቸውም። ከዚያ ይልቅ ተግባቢ፣ አቀራረብህን እንደሁኔታው የምትለዋውጥና ንግግርህን የማታንዛዛ ሁን። እነዚህ ባሕርያት መልእክቱን የሚስብ ያደርጉታል።
7 እነዚህና ሌሎቹም አቀራረቦች ፍላጎት ባላቸው ሰዎች ልብ ውስጥ አድናቆት ለመኮትኮት ያገለግላሉ። በየሳምንቱ ቢያንስ አንድ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ለምን በግልህ ግብ አታወጣም? ከላይ የተጠቀሱትን ሊሠሩ የሚችሉ ሐሳቦች ተጠቀምባቸው፤ እንዲሁም ተሞክሮ ያላቸውንና ሊረዱህ የሚችሉትን አስፋፊዎች ቀርበህ ጠይቅ። ውጤታማ ተመላልሶ መጠየቆችን በማድረግ ሰዎች በመጀመሪያ ላይ ያሳዩትን ፍላጎት ስትገነባ ደስታህ ይጨምራል።