ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ለመርዳት በደስታ ተመልሰህ ጠይቃቸው
1 ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው ሥራ የሚካፈል እያንዳንዱ ሰው ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች መርዳት ደስ ይለዋል። እንዲህ ዓይነቱን እርዳታ በመስጠት ጥልቅ የሆነ ደስታና እርካታ እናገኛለን። (ከመዝሙር 126:5, 6 ጋር አወዳድር።) ይህም ተዘጋጅቶ መሄድን ይጠይቃል።
2 ዝግጅቱ የሚጀምረው ከቤት ወደ ቤት መዝገባችን ላይ ዝርዝር መረጃዎችን በመጻፍ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ቤታቸው ሄደህ ባነጋገርካቸው ወቅት በምን ርዕስ ላይ እንደተወያያችሁና የቤቱ ባለቤት ያሳየውን ስሜት በማስታወሻህ ላይ መዝግበው። ተመልሰህ በምትሄድበት ጊዜ ምን ብለህ ለመጀመር እንደምትፈልግ እንኳን ሳይቀር በማስታወሻህ ላይ ለመጻፍ ትፈልግ ይሆናል።
3 ለምሳሌ በመጀመሪያው ውይይታችሁ ቀን የጌታን ጸሎት በመጥቀስ አነጋግረኸው ከነበረ ቀጥሎ ካለው ሐሳብ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ነገር አጠር አድርገህ ልትገልጽለት ትችል ይሆናል፦
◼ “በምድር ላይ የአምላክ ፈቃድ እንዴት እንደሚፈጸምና በሁሉም የኑሮ ዘርፎች ላይ ሰላም እንደሚሰፍን ባለፈው ጊዜ ተነጋግረን ነበር። ከዚህ ሐሳብ ጋር በተያያዘ ሁኔታ የአምላክ መንግሥት ገነትን ታመጣለች የሚለው ይህ ብሮሹር የአምላክ መንግሥት ለሰው ልጆች ስለምታመጣቸው ተጨማሪ በረከቶች ምን እንደሚል እስቲ ይመልከቱ።”
4 ባለፈው ጊዜ ሰውየው በአምላክ ወዳለማመን እንደሚያዘነብል አይተህ ከነበረ ቀጥሎ ያለውን የሚመስል አንድ ሐሳብ አቅርብለት፦
◼ “በቀደምለት ጳውሎስ በዕብራውያን 3:4 ላይ ያቀረበውን ሁሉንም ነገሮች የሠራ የማሰብ ችሎታ ያለው አንድ ሠሪ ሊኖር ይገባል ብለን ለመደምደም የሚያስችለንን ሊታመን የሚችል ምክንያታዊ ሐሳብ ተወያይተን ነበር።” ጥቅሱን እንደገና አንብብለትና አምላክ ስለ እኛ በእርግጥ ያስባልን? በተባለው ብሮሹር ገጽ 4 እስከ 9 ላይ ወዳለው ሐሳብ ሄደህ በመጀመሪያው ውይይትህ ላይ ካቆምክበት ጀምረህ አወያየው። ከዚያም በጽሑፉ ላይ ያለውን ጥያቄ ጠይቀውና አንቀጹን አንብበው። ከዚያም ባለቤቱ ጥያቄውን ለመመለስ እንዲሞክር አድርግ። የሚቻል ከሆነ ሰውየው የራሱን ብሮሹር አምጥቶ ጽሑፉን አንድ ላይ እንድትወያዩበት ጋብዘው።
5 ተመላልሶ መጠየቅ የምታደርግለት ሰው ወጣት ከሆነ ሰላም በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ የሚገኝ ሕይወት የተባለውን ትራክት እያሳየህ በገጽ 3 እና 4 ላይ የተገለጸውን ሐሳብ ልታወያየው ትችላለህ። ውብ በሆነች ገነት ገነት ውስጥ በምድር ላይ መኖር ደስ አይልህም? ብለህ ባለቤቱን ጠይቀው። ምን ያህል ፍላጎት እንዳለው በይበልጥ ለማወቅ እንዲረዳህ በያዝከው መጽሔት ውስጥ ባለው አበረታች በሆነ ሐሳብ ወይም ሥዕል ላይ ያለውን አስተያየት እንዲሰጥ ልትጠይቀው ትችል ይሆናል።
6 ባለፈው ጊዜ የተነጋገራችሁት በመጠበቂያ ግንብ ወይም በንቁ! መጽሔት ውስጥ ባለ አንድ ርዕሰ ትምህርት ላይ ከነበረ ይህንኑ መሠረታዊ ዘዴ በመጠቀም ልታነጋግረው ትችላለህ። ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኝታችሁ ስትነጋገሩ አጉልተኸው ከነበረው ርዕሰ ትምህርት ላይ አንዳንድ ሐሳቦችን ከጠቀስክለት በኋላ በዚያው ርዕሰ ትምህርት ላይ ወይም አሁን በያዝከው ሌላ መጽሔት ላይ የሚገኝ ሊስበው የሚችል ሌላ ነጥብ ጥቀስለት። የሚቻል ከሆነ አንድ ጥቅስ አብራችሁ አንብቡና የቤቱ ባለቤት ሐሳብ እንዲሰጥበት ጠይቀው።
7 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ያለህን ግብ በአእምሮህ ያዝ። የሰውየውን ፍላጎት አሳድጎ ወደዚህ ደረጃ ለማድረስ ሦስት አራት ጊዜ ተመላልሶ መጠየቅ ሊያስፈልግ ይችላል። በተቻለህ መጠን ቶሎ ተመልሰህ በመሄድ ለቤቱ ባለቤት ሕይወት በግል የምታስብ መሆንህን አሳይ።
8 የምናውጀው ምሥራች ታላቅ ደስታ የሚያመጣ ነው። (ሉቃስ 2:10) ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ለጥረታችን አዎንታዊ ምላሽ ሲሰጡ መመልከታችን በእርግጥም ለደስታ ምክንያት ይሆነናል። (ፊል. 4:1) በመስክ ላይ የምናገኛቸውን ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ለመርዳት ተመልሰን በመሄድ እንዲህ ዓይነቱን ደስታ እናግኝ።