አቀላልና ውጤታማ ተመላልሶ መጠየቆችን ማድረግ
1 አዘውትራችሁ ተመላልሶ መጠየቅ ታደርጋላችሁ? ወይስ ተመልሳችሁ ስትሄዱ ስለምን ለመነጋገር እንደምትችሉ ስለማታውቁ በጠቅላላው ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ ከባድ ይሆንባችኋል? የፍርሃት ስሜት እንዲሰማችሁ አያስፈልግም። የተዋጣላችሁ ለመሆን እንድትችሉ ሦስት ነገሮች ይረዷችኋል፤ እነርሱም:- (1) በጥሩ ሁኔታ መዘጋጀት፣ (2) አንድ ወይም ሁለት ጥቅሶችን ተጠቅሞ ጥቂትና ቀላል የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሶችን ለማወያየት መቻል እንዲሁም (3) የቤቱ ባለቤት ያለውን አመለካከት ለማዳመጥ ፈቃደኛ መሆን ናቸው።
2 ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ በምትዘጋጁበት ጊዜ ከቤቱ ባለቤት ጋር በምን ነጥብ ላይ ብትወያዩ ተገቢ እንደሚሆን አስቡበት። ተማሪ ነው? ብዙ ተማሪዎች በዚህ ወር የእረፍት ጊዜ ስለሚኖራቸው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለመወያየት የሚችሉበት ትርፍ ጊዜ ያገኛሉ። አንዳንዶቹ የመንግሥቱን መልእክት የሚቀበሉ ሆነው ልታገኟቸው ትችላላችሁ። ባለፈው ጉብኝታችሁ መጨረሻ ላይ ጥያቄ አንስታችሁ ነበርን? ወይም የቤቱ ባለቤት በአንድ ነጥብ ላይ ፍላጎት አሳይቶ ነበርን? የወሰዳችኋቸውን ማስታወሻዎች እንደገና ተመልከቷቸውና ውጤታማ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ትችሉ ዘንድ የሚያስፈልጓችሁን ሐሳቦች ለማግኘት ምክንያቱን ማስረዳት በተባለው መጽሐፍ ተጠቀሙ። ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርጉ ሞቅ ባለና በወዳጅነት መንፈስ አነጋግሯቸው። የቤቱን ባለቤት ስሙን ጠርታችሁ ሰላም በሉት።
3 የቤቱ ባለቤት መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች አበርክታችሁለት ከነበረ ተመላልሶ መጠየቃችሁ ከመጽሔቱ ላይ በመረጣችኋቸው አንድ ወይም ሁለት ቀላል ነጥቦች ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ልታደርጉት ትችላላችሁ። በመጀመሪያው ጉብኝታችሁ ወቅት ትራክት አበርክታችሁለት ከነበረ በትራክቱ ላይ ወይም የትራክቱ ተከታይ በሆነው መጽሔት ወይም ብሮሹር ውስጥ ባለ ተስማሚ ነጥብ ላይ ሐሳብ ልትሰጡት ትችላላችሁ።
4 “ሰላም በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ የሚገኝ ሕይወት” የተባለውን ትራክት አበርክታችሁ ከነበረ በቀላሉ እንዲህ ልትሉ ትችላላችሁ:-
◼ “ባለፈው ጉብኝቴ ወቅት አምላክ እንደሚያመጣ ቃል ስለገባው ሰላም የሰፈነበት አዲስ ዓለም ተነጋግረን ነበር። እንደተነጋገርነው በአምላክ መንግሥት አማካኝነት የተሻሉ ሁኔታዎች ይመጡልናል። የዚያ ሰላም የሰፈነበት አዲስ ዓለም ክፍል ለመሆን እንድንችል ምን የሚፈለግብን ይመስልዎታል?” የቤቱ ባለቤት ሐሳብ እንዲሰጥበት ፍቀዱለት። ከዚያም በመዝሙር 37:9, 11, 29 ላይ ያለውን ሐሳብ አካፍሉት።
5 “ የሞቱብን ዘመዶቻችንና ወዳጆቻችን ያላቸው ተስፋ ምንድን ነው?” የምትለውን ትራክት አበርክታችሁ ከሆነ ቀጥሎ ያለው አጠር ያለ ሐሳብ ውይይት እንድትጀምሩ ሊያደርጋችሁ ይችል ይሆናል:-
◼ “ባለፈው ውይይታችን መደምደሚያ ላይ የሞቱብን ዘመዶቻችንና ወዳጆቻችን ያላቸው ተስፋ ምንድን ነው? የምትል ትራክት ትቼለዎት ነበር። በትራክቱ ላይ ያለው ሦስተኛው አንቀጽ ‘ሰዎች ለምን ይሞታሉ? ሙታን የት ናቸው? እንደገና በሕይወት ሊኖሩ እንደሚችሉ እንዴት እርግጠኛ ልንሆን እንችላለን?’ የሚሉ ስሜትን የሚቀሰቅሱ ጥያቄዎችን ያነሳል። ‘ሞት እና ስንሞት ምን እንደምንሆን’ የሚለው ንዑስ ርዕስ ለእያንዳንዱ ጥያቄ መልስ ይሰጠናል። የትራክቱን ሌላ ቅጂ ይዣለሁ። በአራተኛው አንቀጽ ላይ ምን እንደሚል ልብ ይበሉ።” ከዚያ የቤቱ ባለቤት እየተከታተላችሁ አንቀጹንና ሁለቱን ጥቅሶች አንብቧቸውና የቤቱ ባለቤት ምን አስተያየት እንዳለው ጠይቁት። የሚናገረውን በጥንቃቄ አዳምጡና ውይይታችሁን በዚያ መሠረት ቀጥሉ።
6 በውይይቱ ወቅት የቤቱ ባለቤት ትክክል ያልሆኑ በርካታ አስተያየቶችን ይሰጥ ይሆናል። ባነሳቸው ጉዳዮች ሁሉ ላይ መወያየት አስፈላጊ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የመነጋገሪያ ርዕሳችሁን በጥብቅ ተከተሉ። የቤቱ ባለቤት ያሉት ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ አመለካከቶች ወደፊት በምታደርጓቸው ተመላልሶ መጠየቆች ላይ ሊታረሙ ይችላሉ።
7 በሚያዝያ ወር ቀላልና ውጤታማ ተመላልሶ መጠየቆች በማድረግ ቀደም ሲል ያሳዩትን ማንኛውንም ፍላጎት ገንቡ።