ሕይወት አድን በሆነው አገልግሎታችን ስኬታማ በሆነ መንገድ መካፈል
1 ሐዋርያው ጳውሎስ ‘በሁሉ መንገድ አንዳንዶችን ያድን ዘንድ’ የምሥራች አቀራረቡን እንደ ሁኔታው ይለዋውጥ ነበር። (1 ቆሮ. 9:19–23) እኛም በተመሳሳይ የቤቱን ባለቤት ፍላጎት ከሁኔታዎቹ ለማስተዋል ንቁዎች ከሆንንና ውይይታችንን ለሰውየው ከሚያስፈልጉት ነገሮች ጋር የሚስማማ ካደረግነው በአገልግሎታችን ይበልጥ የተሳካልን እንሆናለን። መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን ወይም ከብሮሹሮቻችን አንዱን በምናበረክትበት ጊዜ እንደዚህ ማድረግ አስቸጋሪ ሊሆንብን አይገባም።
2 ክርስቲያን ነኝ የሚል ሰው ስታገኝ ራስህን ካስተዋወቅኸው በኋላ በራስህ አነጋገር ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ አንድ ነገር በማለት ትጀምር ይሆናል፦
◼ “በዚህ አካባቢ ላሉት ሰዎች አንድ ጥያቄ እያቀረብንላቸው ነው። እርስዎም ያለዎትን አስተያየት ቢሰጡን ደስ ይለናል። ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት እንድትመጣና ፈቃዱ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሆን ዘንድ እንድንጸልይ አስተምሮናል። ግን በእርግጥ የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ ይፈጸማል ብለው ያስባሉን?” የቤቱ ባለቤት መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት። ከዚያም ወደ ኢሳይያስ 55:10, 11 ሂድና የቤቱ ባለቤት የአምላክ ተስፋዎች በሙሉ እንዴት እንደሚፈጸሙ ልብ እንዲል ጋብዘው። — ምማ ገጽ 12, “መንግሥት” በሚለው ርዕስ ሥር ያለው ሁለተኛው የመግቢያ ሐሳብ።
3 የቤቱ ባለቤት ፍላጎት ካሳየ እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችል ይሆናል፦
◼ “መጠበቂያ ግንብ የተባለው መጽሔት ካሉት ዓላማዎች አንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መፈጸማቸውን ለሰዎች ማሳሰብ ነው። እስቲ ይህንን ርዕሰ ትምህርት ይመልከቱት።” ከዚያም “አምላክ የሚሰጠውን ማስጠንቀቂያ ሰምተህ እርምጃ ትወስዳለህን?” የሚለውን በመጋቢት 1 የመጠበቂያ ግንብ እትም ላይ የወጣውን ርዕሰ ትምህርት አሳየው። በገጽ 5 ላይ ባለው ሣጥን ውስጥ ካሉት ነጥቦች አንድ ሁለቱን እያሳየኽ አወያየውና “ከጥፋቱ በኋላ የሚመጣው አስደሳች ጊዜ” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር ባሉት የመጨረሻ አንቀጾች ላይ እንዲያተኩር አድርግ። ከዚያም ኮንትራት እንዲገባ ጠይቀው። ኮንትራት እንዲገባ ያቀረብክለትን ግብዣ ካልተቀበለ ሁለቱን መጽሔቶችና አንድ ብሮሹር በመደበኛው ዋጋ አበርክትለት።
4 የቤቱ ባለቤት በአምላክ ላይ ምንም እምነት እንደሌለው ካስተዋልክ ዕብራውያን 3:4ን ጠቅሰህ ልታወያየው ትችላለህ። ከዚያም አምላክ ስለ እኛ በእርግጥ ያስባልን? የተባለውን ብሮሹር ገጽ 4 ላይ አውጥተህ አንቀጽ 1 እና 2ን አንብብለትና በገጹ ግርጌ ያሉትን ጥያቄዎች ጠይቀው። ወይም በቅርቡ ከወጡት መጽሔቶች በአንዱ ላይ ካለው ተስማሚ ርዕስ ጋር አያይዘህ ሐሳብ መስጠት ትችላለህ።
5 የቤቱ ባለቤት ወጣት ከሆነ ራስህን ካስተዋወቅኸው በኋላ ቀጥሎ ያለውን ሐሳብ ልትናገር ትችላለህ፦
◼ “እንዳንተ ያሉ ወጣቶች መጽሐፍ ቅዱስ የሚያቀርብልንን ታላቅ የወደፊት ተስፋ እንዲመረምሩ እያበረታታሁ ነኝ። (እንደ ራእይ 21:3, 4 ያሉ ጥቅሶችን አንብብለት።) ጥሩ መስሎ አይታይህም?” ከዚያም በሚያዝያ 15 የመጠበቂያ ግንብ እትም ላይ የሚገኘውን ሐሳብ በመጠቀም መጽሔቶቻችን ለወጣቶች እንዴት ያሉ ትክክለኛ መመሪያዎችን እንደሚሰጡ ለማሳየት እንችላለን። ብዙ ወጣቶች የመጽሔቶቻችን ኮንትራት አላቸው።
6 የቤቱ ባለቤት ሌላ ጉብኝት እንዲደረግለት ፍላጎቱን የሚቀሰቅስ ነገር ካልተናገርክ የመጀመሪያ ጉብኝትህ ሙሉ በሙሉ የተሳካ አይሆንልህም። ስለዚህ ፍላጎት የሚቀሰቅስ ጥያቄ መጠየቅህንና ተመልሰህ ስትመጣ ጥያቄውን እንደምትመልስለት መንገርህን አትርሳ።
7 ከላይ ካሉት ሐሳቦች ውስጥ ለመናገር የሚቀልልህን ምረጥ። እነዚህን ሐሳቦች በአገልግሎት ክልልህ ውስጥ ካለው ሁኔታ ጋር እንዲስማሙ አድርግ። የቤቱ ባለቤት ምን እንደሚያስፈልገው ተገንዝበህ በየትኛው ሐሳብ ወይም ጽሑፍ ብታወያየው እንደሚሻል ወዲያው ለመወሰን እንድትችል ከያዝካቸው ብሮሹሮች፣ ትራክቶችና የመጽሔቶቹ ርዕሰ ትምህርቶች ጋር በደንብ ተዋወቅ። ሁላችንም “ስለ ምሥራቹ” ስንል አቀራረቦቻችንን በትጋት እንዘጋጅባቸው፤ ሕይወት አድን በሆነውም በዚህ አገልግሎት ስኬታማ በሆነ መንገድ እንካፈል። — 1 ቆሮ. 9:23