በግ መሰል የሆኑ ሰዎች በጠንካራ መሠረት ላይ እንዲታነጹ እርዳቸው
1 ቤት መሥራት በጥንቃቄ ፕላን ማውጣትንና ከፍተኛ ጥረት ማድረግን ይጠይቃል። የቤቱ ዲዛይን ከወጣ በኋላ ቤቱ የሚሠራበት ቦታ መገኘት አለበት፤ እንዲሁም ጠንካራ መሠረት መጣል ይኖርበታል። ቤቱ ደረጃ በደረጃ ቅርጽ እየያዘ ይሄድና በመጨረሻው ሥራው ይጠናቀቃል። በተመሳሳይም በግ መሰል የሆኑ ሰዎች እውነትን ደረጃ በደረጃ እንዲማሩ መርዳት አለብን። በመጀመሪያ ጉብኝታችን ላይ ፍላጎታቸውን ለመቀስቀስ ጥረት እናደርጋለን። ከዚያ በኋላ እየተመላለስን በመጠየቅ ስለ አምላክና እርሱ ለሰው ልጆች ስላለው ዓላማ መሠረታዊ የሆኑትን እውነቶች በማስተማር የእምነት መሠረት እንጥላለን። — ሉቃስ 6:48
2 መሠረቱን ከመጣላችን በፊት ግን የሰውየውን ሁኔታ በማጤን ሕንፃው የሚገነባበትን ሥፍራ ማዘጋጀት ያስፈልገናል። ከዚህ በፊት ውይይት የተደረገው በምን ርዕሰ ጉዳይ ላይ ነበር? የተነበቡትስ ጥቅሶች የትኞቹ ነበሩ? ሰውየው ምን አለ? ምን ጽሑፍ ወስዷል? ተመልሰህ በምትመጣበት ጊዜ የምትወያዩባቸውን ነጥቦች በአእምሮአህ በመያዝ መሠረቱን ደረጃ በደረጃ ገንባ። እየተመላለስን ባነጋገርነው ቁጥር የሰውየው እውቀት እያደገ፣ በአምላክ ላይ ያለው እምነትም እየጨመረ ይሄዳል።
3 “ለዘላለም መኖር” ተበርክቶለት ከነበረ እንዲህ ልንለው እንችል ይሆናል፦
◼ “በቀጠሯችን እቤት ስለተገኙ በጣም ደስ ብሎኛል። ባለፈው ጊዜ ስንወያይ በአካባቢያችን ሥነ ምግባር ምን ያህል እያዘቀጠ እንደሄደ እንደተወያየን ምናልባት ትዝ ይለዎት ይሆናል። አምላክ ለሰው ልጆች እንደሚያስብና ጻድቃንም በመንግሥቱ አማካኝነት እንደሚባረኩ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያሳያል። [ማቴዎስ 6:9, 10ን አንብብ።] በዚህ መንግሥት አማካኝነት ጽድቅና ፍትሕ ይሰፍናል።” ኢሳይያስ 11:3–5ን አንብብና ሰውየው ለዘላለም መኖር የተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ አንድ ላይ ባሉት የመጀመሪያዎቹ ሁለት አንቀጾች ላይ እንዲያተኩር አድርግ። መጽሐፉን እንዴት ማጥናት እንደሚቻል አንድ ባንድ አሳየው።
4 በመጀመሪያው ጉብኝት ወቅት ሰላም የሰፈነበት አዲስ ዓለም የተሰኘው ትራክት ተሰጥቶት ከነበረ የተሻሉ ሁኔታዎች እንደሚያስፈልጉን እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚሰጠው ተስፋ የሚናገሩት ቀደም ሲል ተብራርተውለት የነበሩት ዋና ዋና ነጥቦች ሊከለሱለት ይችላሉ። በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለመኖር ትክክለኛ እውቀት ማግኘት እንደሚያስፈልገን አጥብቀህ ግለጽለት። ዮሐንስ 17:3ን አንብብ። ይህንን እውቀት ካገኘን በኋላ የአምላክን ፈቃድ ማድረግ እንዳለብን አብራራለት። 1 ዮሐንስ 2:17ን አንብብለትና ሰውየው በትራክቱ ውስጥ በገጽ 5 ባሉት የተወሰኑ ነጥቦች ላይ እንዲያተኩር አድርግ።
5 በመጀመሪያው ጉብኝትህ ላይ “ለዘላለም መኖር” የተባለውን መጽሐፍ ስታበረክትለት የቤተሰብን ኑሮ የሚመለከተውን ሐሳብ ጎላ አድርጋችሁ ተወያይታችሁበት ከነበረ እንዲህ ለማለት ትችል ይሆናል፦
◼ “ባለፈው መጥቼ በነበረበት ጊዜ የቤተሰብን ኑሮ በሚመለከተው ጉዳይ ላይ ተወያይተን ነበር። ደስታ ያለበት የቤተሰብ ኑሮ እንዲኖረን ከተፈለገ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን መመሪያዎች መከተል ይኖርብናል በሚለው ነጥብ ላይ ተስማምተን ነበር። የተሳካ ትዳር እንዲኖረን ምን የሚያስፈልግ ይመስልዎታል? መልስ እንዲሰጥህ ፍቀድለት። ለዘላለም መኖር መጽሐፍ ውስጥ ከገጽ 243 እስከ 246 ላይ ከተዘረዘሩት ሐሳቦች ውስጥ የተወሰኑ ነጥቦችን አጉላ። ሰውየው በስዕሎቹ ላይ ምን አስተያየት እንዳለው ጠይቀው። ተገቢ በሚሆንበት ጊዜ በተመረጡ ነጥቦች ላይ ተወያዩ። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በተግባር የሚታይ ጥቅም እንዳላቸው አጥብቀህ ግለጽ።
6 በቤተሰብህ ኑሮ ተደሰት የተባለው ትራክት ተሰጥቶት ከነበረ በገጽ 4 እና 5 ላይ የተዘረዘሩትን ቁልፍ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ከልስለት። ፍላጎቱ ከተቀሰቀሰ ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ ለማበርከት ሞክር። “የቤተሰብን ኑሮ የተሳካ ማድረግ” የሚል ርዕስ ያለውን ምዕራፍ 29ን አውጣና የቤቱን ባለቤትና ቤተሰቡን እንዴት ልታስጠናቸው እንደምትችል አሳየው።
7 ሁላችንም ተመላልሶ መጠየቅ በማድረጉ ሥራ አዘውትረን ልንካፈል ይገባናል። በመስከረም ውጤታማ ተመላልሶ መጠየቆች በማድረግ ፍላጎት ያላቸውን ሁሉ ተከታትለህ ለመርዳት ጥረት አድርግ።