መጽሐፍ ቅዱስ ለዛሬው ዓለም ያለው ጠቀሜታ
1 በዛሬው ጊዜ ብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስ ጊዜ ያለፈበትና እውነትነት የሌለው ሆኖ ይሰማቸዋል። በታሪክ በሙሉ ከማንኛውም መጽሐፍ ይበልጥ በስፋት የተሰራጨና በብዛት የተተረጎመ መጽሐፍ ቢሆንም ያነበቡት ጥቂቶች ሲሆኑ መመሪያዎቹን የሚከተሉት ደግሞ ከዚያ ያነሱ ናቸው።
2 በተቃራኒው ግን እኛ መጽሐፍ ቅዱስን እንደ አምላክ ቃል አድርገን ከፍተኛ ዋጋ እንሰጠዋለን። እውነታዎቹ የመጽሐፉን ታሪካዊ እውነተኝነት ያሳያሉ። ከዚህም በላይ እርስ በርስ ያለው አስደናቂ ስምምነት፣ ትንቢቶቹ፣ በውስጡ ያለው ጥበብ ሰዎችን ወደ መልካም ለመገፋፋት ከፍተኛ ኃይል ያለው መሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ‘በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ’ መሆኑን ያሳያሉ። (2 ጢሞ. 3:16 አዓት) በግላችን ያገኘነው ተሞክሮና ለዚህ አስደናቂ ስጦታ ያለን አድናቆት ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነተኛ ጥቅም እንዲመረምሩ እንድናበረታታቸው ይገፋፋናል።
3 አንዱ አቀራረባችን እንዲህ ሊሆን ይችላል፦
◼ “ብዙ ሰዎች በሰው ልጆች ፊት የተጋረጡትን ከባድ ችግሮች ሲመለከቱ ወደፊት ጥሩ ነገር ይመጣል ብለው መጠበቅ አዳጋች ይሆንባቸዋል። እርስዎስ እንዴት ይሰማዎታል? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] የዚህችን ትራክት ርዕስ ይመልከቱት:- ሰላም በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ የሚገኝ ሕይወት ትላለች።” በሽፋኑ ላይ ያለውን ሥዕል እንዲመለከተው አድርግ። ከዚያም በገጽ 2 ላይ ያሉትን የመጀመሪያውንና ሁለተኛውን አንቀጾች አንብብለት። ምዕራፍና ቁጥራቸው የተጠቀሱትን ጥቅሶች እያወጣችሁ የአምላክን ተስፋዎች በማጉላት ተወያዩባቸው። ከቻልክ በመጀመሪያው ንዑስ ርዕስ ሥር ያሉትን አንቀጾች በሙሉ ለመጨረስ ሞክር። በትራክቱ ላይ ይበልጥ ለመወያየት እንድትችሉ ቀጠሮ ውሰድ። ፍላጎቱን ለመቀስቀስ ምናልባት ከንዑስ ርዕሶቹ አንዱን በጥያቄ መልክ አቅርብለት።
4 ሌላው አቀራረባችን ደግሞ ከሚከተለው ጋር ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል፦
◼ “የሰው ዘር በሕይወቱ የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለመወጣት መመሪያ ያስፈልገዋል ቢባል አይስማሙምን? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ባለፉት ዘመናት ሰዎች መመሪያ ለማግኘት ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ዞር ይሉ ነበር፤ አሁን ግን ጊዜው ተለውጧል። መጽሐፍ ቅዱስ ለዘመናችን ተግባራዊ ጥቅም ያለው ይመስልዎታል? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] በ2 ጢሞቴዎስ 3:16 ላይ ያለውን ልብ ይበሉ። [አንብብ።] በጽሑፍ የሰፈረው የአምላክ ቃል ጥበብ ያለባቸው ውሳኔዎችን ለመወሰን ይረዳናል፤ እምነት ሊጣልበት የሚችል የወደፊት ተስፋም ይሰጠናል።” ዮሐንስ 17:3ን አንብብለት። ከዚያ ቀጥለህ መጽሐፍ ቅዱስ — የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? ከተባለው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ውስጥ ቀደም ብለህ የመረጥካቸውን የመጽሐፍ ቅዱስን ተግባራዊ ጠቀሜታ የሚያሳዩ አንድ ወይም ሁለት ነጥቦችን ልታሳየው ትችል ይሆናል።
5 ምክንያቱን ማስረዳት በተባለው መጽሐፍ ውስጥ በገጽ 10 ላይ “መጽሐፍ ቅዱስ/አምላክ” በሚለው ርዕስ ሥር ከተዘረዘሩት መግቢያዎች በአንዱ መጠቀም ጥሩ ሆኖ ልታገኘው ትችላለህ። የቤቱን ባለቤት ጥያቄ ለመመለስ ወይም የተቃውሞ አስተያየቱን ለማብረድ የሚረዱ ተጨማሪ ሐሳቦች ከገጽ 58–68 ላይ ቀርበዋል።
6 አዲሲቱ ዓለም ትርጉምን ማበርከት፦ አዲሲቱ ዓለም ትርጉም ን በመጀመሪያው ጉብኝትህ ወይም በተመላልሶ መጠየቅ ላይ ልታስተዋውቀው ትችላለህ። ሰውየው መጽሐፍ ቅዱስ እንዳለውና መጽሐፍ ቅዱሱን ሲያነበው ቀላል ሆኖ አግኝቶት እንደሆነ ልትጠይቀው ትችላለህ። መልሱን መሠረት በማድረግ አዲሲቱ ዓለም ትርጉም ያሉትን ጠቃሚ ጎኖች ንገረው። ምክንያቱን ማስረዳት ከተባለው መጽሐፍ ገጽ 276–80 ላይ ካሉት ነጥቦች አንድ ሁለቱን ልታጎላለት ትችላለህ።
7 ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያነቡ ልታበረታታ የምትችልባቸውን አጋጣሚዎች በንቃት ተከታተል። ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በጽሑፍ ለሰፈረው የአምላክ ቃል በውስጣቸው አክብሮትና ፍቅር እንዲያዳብሩ እርዳቸው። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ በማድረግና እውነትን በማወቅ አሁንም ሆነ ወደፊት ብዙ ጥቅሞች ያገኛሉ። — መዝ. 119:105