የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ለጥናታቸው እንዲዘጋጁ እርዳቸው
1 በየሳምንቱ ለጥናታቸው የሚዘጋጁ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ለጥናታቸው እውነተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ያሳያሉ። እንዲሁም ከማይዘጋጁት ይልቅ ብዙውን ጊዜ እነዚህ ፈጣን መንፈሳዊ ዕድገት ያደርጋሉ። አንዳንድ ጊዜ አንድ ተማሪ እንዴት እንደሚዘጋጅ ባለማወቁ የተነሳ አይዘጋጅ ይሆናል። እንዴት መዘጋጀት እንዳለበት ማስተማሩ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። ይህንን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?
2 ዝግጅት ማለት በግል ማጥናት ማለት እንሆነ ተማሪው ገና ከመጀመሪያው እንዲገባው አድርግ። ብዙ ሰዎች ማንበብ የሚችሉ ቢሆኑም እንዴት ማጥናት እንዳለባቸው አልተማሩም። ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ ጥናት ቁጥር 7 እና 8 ላይ ብዙ ጠቃሚ ሐሳቦች ተሰጥተዋል። ለተማሪው የሚያስፈልገውን እያየህ እነዚህን ሐሳቦች ልትነግረው ትችል ይሆናል።
3 የማጥናትን ጥቅም ለተማሪው ግለጽለት፦ ቁልፍ በሆኑ ቃላትና ሐረጎች ላይ ምልክት ያደረግህበትን ወይም ያሰመርክበትን የማስጠኛ መጽሐፍህን ለተማሪው ልታሳየው ትችል ይሆናል። ምልክት የተደረገባቸውን ነጥቦች አየት በማድረግ በራሱ አባባል ሊገልጸው የሚችለውን ሐሳብ እንዴት ሊያስታውሰው እንደሚችል እንዲገነዘብ አድርገው። ይህን ካደረገ ጥያቄዎችን በሚመልስበት ጊዜ ከመጽሐፉ ላይ አንድን ክፍል በሙሉ ለማንበብ አይሞክርም። በዚህ ደረጃ የሚሰጥ ጥሩ ሥልጠና የኋላ ኋላ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ትርጉም ያላቸው ሐሳቦችን እንዲሰጥ ይረዳዋል። የሚሰጣቸው ሐሳቦች እየተጠና ላለው ትምህርት ያለውን አድናቆት ያንጸባርቃሉ፤ እንዲሁም ትምህርቱን በምን ያህል ጥልቀት እንደተረዳው ያመለክታሉ።
4 በመጽሐፍ ቅዱስ መጠቀምን አስተምረው፦ ተማሪው በሚጠናው ጽሑፍ ላይ ያሉትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥቅሶች እንዴት ማውጣት እንደሚችል መማር ያስፈልገዋል። ጥቅሶችን በቅልጥፍና ማውጣት ሲችል በእርግጥም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ መሆኑን ይበልጥ ሙሉ በሙሉ ሊገነዘበው ይችላል። ምንም እንኳን በመጀመሪያ በመጽሐፍ ቅዱሱ የመጀመሪያ ገጽ ላይ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ማውጫ መጠቀም የሚያስፈልገው ቢሆንም 66ቱን የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በቅደም ተከተል በደንብ እንዲያውቃቸው ማበረታታት ያስፈልጋል። አንድን ጥቅስ አውጥቶ ሲያነብ ከምታጠኑት ነገር ጋር በቀጥታ በማይዛመዱት የጥቅሱ ክፍሎች ሐሳቡ እንዳይወሰድ እየተጠና ያለውን አንቀጽ የሚደግፈውን ክፍል ለመለየት እንዲችል እርዳው።
5 ተማሪው በጥናቱ እየገፋ ሲሄድ መጽሐፍ ቅዱስን ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው እንዲያነበው አበረታታው። ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ የአምላክ ቃል መሆኑንና እውነተኛ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ በመንፈሳዊ መመገብ እንዳለበት ጠበቅ አድርገህ ግለጽለት። — ማቴ. 4:4፤ 2 ጢሞ. 3:16, 17 አዓት
6 ሌሎች ቲኦክራሲያዊ ጽሑፎችን አስተዋውቀው፦ ተማሪው ጥሩ ዕድገት እያሳየ ሲሄድ ሌሎች ቲኦክራሲያዊ ጽሑፎችን መጠቀም ሊጀምር ይችላል። ሁኔታውን እያጤንክ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በሚገኝበት ጊዜ ካወቃቸው የማኅበሩ ጽሑፎች ውስጥ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት እንዲመረምር አበረታታው። አዲሲቱ ዓለም ትርጉም ላይ ባሉት እንደ “የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ማውጫ” በመሳሰሉ ልዩ ልዩ ክፍሎች እንዴት መጠቀም እንደሚችል አስተምረው። የራሱን ቲኦክራሲያዊ ጽሑፎች ማከማቸት ሲጀምር ደግሞ በኮምፕርኼንሲቭ ኮንኮርዳንስ፣ ከቅዱሳን ጽሑፎች ምክንያቱን ማስረዳት በተባለው መጽሐፍ፣ በኢንዴክስ እና ማስተዋል በተባለው መጽሐፍ ጥራዞች እንዴት መጠቀም እንደሚችል አሳየው።
7 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸው እንዴት እንደሚዘጋጁ ብናስተምራቸው በግል የሚደረግላቸውን የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸውን ከጨረሱ በኋላም ቢሆን ጥሩ ችሎታ ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በመሆን በእውነት ውስጥ ዕድገት ማሳየታቸውን እንዲቀጥሉ እናስታጥቃቸዋለን።