ከቅዱሳን ጽሑፎች ምክንያቱን ታስረዳለህን?
1 ወደ ጦርነት የሚሄድ ልምድ ያለው ወታደር ሙሉ ትጥቁንና መከላከያውን ይይዛል። ትልቅ የግንባታ ፕሮጀክት ውስጥ ለመሥራት የሚዘጋጅ ጥሩ ችሎታ ያለው የእጅ ባለሞያ ሥራውን ለማከናወን የሚያስፈልጉትን መሣሪያዎች በሙሉ ይዞ ይሄዳል። በመስክ አገልግሎት የተሰማራ አንድ የይሖዋ አገልጋይም ‘ሰይፉን’ ይዞ በመሄድ አጋጣሚውን ሲያገኝ በጥሩ ሁኔታ ይጠቀምበታል። (ኤፌ. 6:17) አንተም እንዲህ ታደርጋለህን? በአገልግሎቱ ስትካፈል መንፈስ ቅዱስ የአድማጮችህን ልብ ለመንካት ይችል ዘንድ የአምላክ ቃል ራሱ እንዲናገር ታደርጋለህን? — ምሳሌ 8:1, 6
2 መስበክ ሁልጊዜ ቀላል የሆነ ሥራ አይደለም። በአንዳንድ የአገልግሎት ክልሎች ውስጥ ሰዎቹ ብዙውን ጊዜ እቤት አይገኙም፤ በራቸውን የሚከፍቱልን ሰዎችም ብዙውን ጊዜ ሥራ አለብን በማለት ሰፊ ለሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት በቂ ጊዜ አይሰጡንም። መጽሐፍ ቅዱስ ዋናው የማስተማሪያ መጽሐፋችን እንደመሆኑ መጠን በአገልግሎታችን ይበልጥ ልንጠቀምበት የምንችለውና በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት መልእክቶቹ ሰሚዎቻችንን ለተግባር ማነሳሳት እንዲችሉ የምናደርገው እንዴት ነው?
3 ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ፦ በምናንኳኳቸው በሮች ላይ መጽሐፍ ቅዱስ የቤቱን ባለቤት ለተግባር እንዲገፋፋው ልንጠቀምበት እንፈልጋለን። የምናበረክተው ጽሑፍ ምንም ይሁን ምን ይህንን ለማድረግ ዝግጁ መሆን አለብን። ሰውየው ሥራ ይዞ ከሆነና መጽሐፍ ቅዱስ አውጥቶ አንድ ወይም ሁለት ጥቅስ ለማንበብ በቂ ጊዜ ባይኖር ጽሑፉን እንዲወስድ ከመጠየቅህ በፊት አንድ ጥቅስ ልትጠቅስለት ወይም የጥቅሱን ሐሳብ በራስህ አባባል ልትነግረው ትችል ይሆን? እንዲህ ማድረግህ ብቻ እንኳን ሰውየው ቆም ብሎ እንዲሰማህ ሊያደርግ ይችል ይሆናል። በዚህ መንገድ የአምላክ ቃል ራሱ እንዲናገር ልታደርገው ትችላለህ። — ዕብ. 4:12
4 ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርግ፦ ተመላልሶ መጠየቅ ከማድረጋችን በፊት መዘጋጀት ይገባናል። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ ለውይይት ያልተዘጋጀንባቸው ርዕሶች ይነሳሉ። ከቅዱሳን ጽሑፎች ምክንያቱን ማስረዳት የተባለውን መጽሐፍ ጠቃሚ መሣሪያ ሆኖ የምናገኘው በዚህ ጊዜ ነው። ምክንያቱን ማስረዳት በተባለው መጽሐፍ ላይ ያሉትን ድጋፍ የሚሆኑ ጥቅሶች መጥቀሳችን ወይም ከመጽሐፉ ላይ ማንበባችን እኛ የአምላክ አገልጋዮች እንጂ በቃሉ የምንነግድ አለመሆናችንን ሰዎች እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል። — 2 ቆሮ. 2:17
5 በአንድ በተወሰነ ርዕስ ላይ ያላወያየኸውን ሰው ተመልሰህ ሄደህ በምታነጋግረው ጊዜ ምክንያቱን ማስረዳት ከተባለው መጽሐፍ “ኢየሱስ ክርስቶስ”፣ “የመጨረሻዎቹ ቀናት” ወይም “ትንሣኤ” እንደሚሉት ያሉ ተስማሚ ርዕሶች አውጥተህ ከንዑስ ርዕሶቹ በአንዱ ላይ ውይይት መጀመር ትችላለህ። አንዳንዶቹን ጥቅሶች ከራሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያነቡ ሰዎቹን መጠየቅ ይቻላል። በዚህ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ ሕያው ይሆንላቸዋል፤ ጽድቅን የተጠሙ ከሆኑም የይሖዋ መንፈስ ቅዱስ ይፈስስላቸዋል።
6 ምሥራቹን የመስበክና ክፉዎችን የማስጠንቀቅ ከባድ ኃላፊነት አለብን። መልእክቱ የይሖዋ እንጂ የኛ አይደለም። ለዚህም የመንፈስ ሰይፍ የሆነው ቃሉ ይርዳህ።