የምታቀርበውን ምስጋና በሚያዝያ ወር ከፍ ልታደርገው ትችላለህን?
1 መዝሙራዊው ዳዊት ተቀባይነት ባለው መንገድ ይሖዋን ለማመስገን ልባዊ ፍላጎት ስለነበረው እንደሚከተለው ሲል ተናግሯል:- “እግዚአብሔርን በአፌ እጅግ አመሰግነዋለሁ። በብዙዎችም መካከል አከብረዋለሁ።” (መዝ. 109:30) በመስክ አገልግሎት የምናደርገውን ተሳትፎ ከፍ በማድረግ ‘ለእርሱ የምናቀርበውን ምስጋና ለመጨመር’ ሚያዝያ ጥሩ ወር ነው። (መዝ. 71:14) ረዳት አቅኚ በመሆን እንዲህ ከሚያደርጉት መካከል አንዱ ለመሆን አቅደሃልን?
2 ከአሁኑ እቅድ አውጣ፦ በምሳሌ 21:5 ላይ እንደ አዲሲቱ ዓለም ትርጉም “የትጉህ ሰው እቅድ ውጤቱ ያማረ ነው” የሚል ማሳሰቢያ እናገኛለን። ይህ ደግሞ ይሖዋን በእቅድህ ውስጥ አንደኛ ቦታ ላይ በማስቀመጥ ነገሩን በጸሎት ለእርሱ ማቅረብን ይጠይቃል። (ምሳሌ 3:5, 6) ከዚያ ቀጥሎ በቀን ውስጥ በአማካይ ሁለት ሰዓት በአገልግሎት ለማሳለፍ አሁን ባለህ ፕሮግራም ላይ ማስተካከያ ማድረግ የሚያስፈልግህ ምን ላይ እንደሆነ ለማወቅ ፕሮግራምህን በጥንቃቄ መርምር። ከሌሎች ሥራዎችህ ላይ ‘ጊዜ መዋጀትህ’ በስብከቱ ሥራ ላይ ብዙ ጊዜ እንድታጠፋ ያስችልሃል። — ኤፌሶን 5:16
3 ከሌሎች ጋር ተነጋገርበት እንዲሁም ተባበር፦ ሐዋርያው ጳውሎስ አገልግሎቱን ሲያከናውን “መጽናኛ” ሆነውለት ስለነበሩ አንዳንድ ሰዎች ተናግሯል። (ቆላ. 4:11) በሚያዝያ ወር ረዳት አቅኚ ሆነው ለመመዝገብ ከሚፈልጉ ሌሎች አስፋፊዎች ጋር ስለ እቅድህ ተወያይ። እነርሱ የሚሰጡህ ድጋፍና አብረውህ መሆናቸው የጋራ መንፈሳዊ ጥቅሞችን ሊያመጣላችሁ ይችላል። ለአገልግሎት ስለተደረገው ዝግጅት ወይም ስለምታገለግልበት ክልል ጥያቄ ካለህ የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ ሊረዳህ ይችላል።
4 በቤተሰብ ውስጥ መተባበርና ለሌላው ድጋፍ መስጠት የቤተሰቡ አባሎች ረዳት አቅኚ እንዲሆኑ ያስችላል። በቤት ውስጥ የሚሠሩ ሥራዎችን ለተወሰነ ጊዜ እንደገና መከፋፈል ይቻላል። እነዚህ ሥራዎች በሚሠሩበት ሰዓት ላይም ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልግ ይሆናል። ዓላማችሁን በማሳካት ረገድ ቤተሰቡ በአንድ ላይ በመሰብሰብ የሚያደርገው ውይይት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ስኬታማ ለመሆን ሐሳብ መለዋወጣችሁና እርስ በእርስ መተባበራችሁ ቁልፍ ነገሮች ናቸው።
5 ይሆናል የሚል አመለካከት ይኑርህ፦ ምቹ ያልሆኑ ሁኔታዎች ስላጋጠሙህ ብቻ ረዳት አቅኚ ለመሆን አልችልም በማለት ፈጥነህ አትወስን። ተማሪዎች፣ ጡረተኞች፣ ልጆች ያሏቸው የቤት እመቤቶችና ሙሉ ጊዜያቸውን ተቀጥረው የሚሠሩ የቤተሰብ ራሶችም መሥዋዕት ከፍለው በሚያዝያ ወር ረዳት አቅኚ ሆነው በደስታ ማገልገል ችለዋል። “ቅኖች ሊያመሰግኑት ይገባል” ካለው መዝሙራዊ ጋር ስለሚስማሙ በአገልግሎታቸው የሚፈለገውን 60 ሰዓት ለመምጣት የሚያደርጉትን ጥረት እንደ ጉዳት አድርገው አይመለከቱትም። (መዝ. 33:1 አዓት) ረዳት አቅኚ ሆነህ መመዝገብ ካልቻልክ እንደ አንድ የጉባኤ አስፋፊ የምታደርገውን እንቅስቃሴ ከፍ በማድረግ ለምን የደስታው ተካፋይ አትሆንም?
6 ለብዙዎቹ በሚያዝያ ረዳት አቅኚ መሆን ወደ ዘወትር አቅኚነት አገልግሎት የሚያሸጋግር ድልድይ ሆኖላቸዋል። አገልግሎታቸውን ቀደም ብለው ከፍ ስላደረጉት ወደ ዘወትር አቅኚነት ለመሸጋገር ይበልጥ ቀላል ሆኖ አግኝተውታል።
7 አዎን፣ የበልጉ ወቅት በሚያዝያ የቲኦክራሲያዊ አገልግሎታችንን ከፍ እንድናደርግ አስተዋጽኦ ያደርጋል። አምላካችንን ይሖዋን ለማመስገን የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ እንፈልጋለን። በሚያዝያ ወር ረዳት አቅኚ ሆነን ማገልገላችን ይሖዋ ይገባናል በማንለው ደግነቱ ላደረገልን ነገሮች ያለንን አድናቆት የምናሳይበት ጥሩ መንገድ ነው።