የይሖዋን ግርማ በሰፊው አውጁ
1. የይሖዋን ግርማ እንድናውጅ የሚገፋፋን ምንድን ነው?
1 “እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ሆይ፤ በሰማይና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነውና፤ ታላቅነት፣ ኀይል፣ ክብርና ግርማ የአንተ ነው።” (1 ዜና 29:11) ለይሖዋ ያለን ፍቅርና አድናቆት ምን ዓይነት ስሜት ያሳድርብናል? ‘ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራንን የእርሱን ግርማ እንድናውጅ’ ይገፋፋናል። (1 ጴጥ. 2:9 NW) ለሌሎች ስለ ታላቁ አምላካችን መናገራችንን ማቆም አንችልም! በመጋቢት፣ በሚያዝያና በግንቦት ወራት የይሖዋን ግርማ ለማወጅ የሚያስችሉ ግሩም አጋጣሚዎች ተከፍተውልናል።
2. ሰዎችን ወደ መታሰቢያው በዓል ለመጋበዝ ምን ልዩ ዘመቻ ለማድረግ ታቅዷል? በዚህ ዘመቻ ላይ እነማን መካፈል ይችላሉ?
2 ሰዎችን ወደ መታሰቢያው በዓል ለመጋበዝ የሚደረግ ልዩ ዘመቻ:- ሰኞ ሚያዝያ 2, 2007 (መጋቢት 24, 1999) የጌታ እራትን በማክበር ለይሖዋ ታላቅ ግርማ ከፍ ያለ ቦታ እንደምንሰጥ እናሳያለን። ለዚህ ትልቅ ክንውን የተዘጋጀው ልዩ የመጋበዣ ወረቀት ከመጋቢት 17 እስከ ሚያዝያ 2 ድረስ በዓለም ዙሪያ ይሰራጫል። ሁላችሁም የተሟላ ተሳትፎ እንድታደርጉ እናበረታታችኋለን። አዲሶች ብቃቶቹን የሚያሟሉ ከሆነ የምሥራቹ አስፋፊ ለመሆን ይህ በጣም ጥሩ ጊዜ ይሆንላቸዋል። ብቃቶቹን ሊያሟሉ የሚችሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ወይም ልጆች ካሏችሁ ቅድሚያውን ወስዳችሁ ከሽማግሌዎች ጋር ተነጋገሩ።
3. ሰዎችን ወደ መታሰቢያው በዓል ለመጋበዝ ምን ማለት እንችላለን?
3 ይህ ዘመቻ “መዳናችን ቀርቧል!” ለተባለው የአውራጃ ስብሰባ ካደረግነው ዘመቻ ጋር ተመሳሳይ ነው። ለእያንዳንዱ አስፋፊ 50 እንዲሁም ለእያንዳንዱ አቅኚ 150 የመጋበዣ ወረቀት እንዲደርስ ለማድረግ ሲባል በቂ የመጋበዣ ወረቀት ለሁሉም ጉባኤዎች ይላካል። መግቢያችሁ አጭር ይሁን። ምናልባት እንዲህ ልትሉ ትችላላችሁ:- “የመጣነው ትልቅ ቦታ በሚሰጠው አንድ ዓመታዊ በዓል ላይ እንዲገኙ የመጋበዣ ወረቀት ልንሰጥዎ ነው። እርስዎም በበዓሉ ላይ ቢገኙ በጣም ደስ ይለናል። ዝርዝር ሐሳቡን እዚህ መጋበዣ ወረቀት ላይ ያገኛሉ።” እርግጥ የቤቱ ባለቤት ጥያቄዎች ካሉት ጊዜ ወስዳችሁ ልታወያዩት ትችላላችሁ። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተባለው መጽሐፍ ገጽ 206 ላይ በሚገኘው ስለ ጌታ እራት በሚናገረው ተጨማሪ ክፍል ላይ በዚህ ረገድ ሊረዳችሁ የሚችል ጠቃሚ ሐሳብ ልታገኙ ትችላላችሁ። ቅዳሜና እሁድ ከመጋበዣ ወረቀቱ ጋር ወቅታዊ መጽሔቶችን እናበረክታለን። ፍላጎት ያለው ሰው ካጋጠማችሁ በማስታወሻችሁ በመያዝ በሌላ ጊዜ ሄዳችሁ ለማነጋገር ዝግጅት ማድረግ ትችላላችሁ።
4. የመታሰቢያውን በዓል ልዩ የመጋበዣ ወረቀት ማሰራጨት የሚቻለው እንዴት ነው?
4 በተቻለን መጠን ይህን ልዩ የመጋበዣ ወረቀት ለእያንዳንዱ የቤት ባለቤት በእጁ ለመስጠት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ስለዚህ ቤታቸው ያልተገኙትን መዝግባችሁ በመያዝ ሌላ ጊዜ ተመልሳችሁ ለመሄድ ዝግጅት አድርጉ። በርከት ያለ የመጋበዣ ወረቀት የተረፋቸው ጉባኤዎች የመታሰቢያው በዓል ከመከበሩ በፊት ባለው ሳምንት ውስጥ በቤታቸው ላልተገኙ ሰዎች መጋበዣውን ትተው መሄድ ይችላሉ። ከዚያ በፊት ግን እንዲህ መደረግ የለበትም። የመጋበዣ ወረቀቱን ለተመላልሶ መጠይቆቻችሁ፣ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችሁ፣ ለዘመዶቻችሁ፣ ለሥራ ባልደረቦቻችሁ፣ ለጎረቤቶቻችሁ እንዲሁም ለምታውቋቸው ሌሎች ሰዎች መስጠት እንደሚኖርባችሁ አትርሱ።
5. ረዳት አቅኚ ለመሆን ከአሁኑ እቅድ ማውጣት መጀመር ያለብን ለምንድን ነው?
5 ረዳት አቅኚነት:- በመጋቢት፣ በሚያዝያና በግንቦት ወራት ረዳት አቅኚ በመሆን የይሖዋን ግርማ ይበልጥ ማወጅ ትችላለህ? እንዲህ ማድረጉ በፕሮግራምህ ላይ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ ይጠይቅብህ ይሆናል። (ኤፌ. 5:15-17) በይሖዋ አገልግሎት ይበልጥ ለመካፈል ጥረት ማድረግህ ደስታና የይሖዋን በረከት እንደሚያስገኝልህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። (ምሳሌ 10:22) የመታሰቢያው በዓል ስለተቃረበ ከአሁኑ እቅድ ማውጣት መጀመር አለብህ።—ምሳሌ 21:5
6. ባለፈው ዓመት ረዳት አቅኚ ሆነው ካገለገሉ አንዲት የ90 ዓመት እህት ምን እንማራለን?
6 ባለፈው ዓመት አንዲት የ90 ዓመት አረጋዊት ረዳት አቅኚ ሆነው የማገልገል መብት አግኝተው ነበር። እንዲህ በማለት ተናግረዋል:- “ጓሮዬን መንከባከብ በጣም ስለምወድ ተጨማሪ አትክልቶችን መትከል ፈልጌ የነበረ ቢሆንም ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ቅድሚያ መስጠት እንደሚያስፈልገኝ ተገነዘብኩ። መንግሥቱን ለማስቀደም ካለኝ ፍላጎት የተነሳ በመጋቢት ወር ረዳት አቅኚ ለመሆን ወሰንኩ።” እኚህ እህት ባደረጉት ጥረት ምን በረከት አግኝተው ይሆን? “ከጉባኤያችን ወንድሞችና እህቶች ጋር በጣም እንደተቀራረብኩ የተሰማኝ ሲሆን ወደ ይሖዋም ይበልጥ መቅረብ ችያለሁ” ብለዋል። እኛስ ቅድሚያ የምንሰጣቸውን ነገሮች በመመርመር አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ እንችላለን?
7. ረዳት አቅኚ ሆኖ ማገልገል አስቸጋሪ ነው?
7 ከረዳት አቅኚዎች የሚጠበቀውን 50 ሰዓት ማሟላት አንተ እንደምታስበው አስቸጋሪ ላይሆን ይችላል። ዕለታዊ እንቅስቃሴዎችህን በጸሎት መርምርና ፕሮግራም አውጣ፤ ከዚያም ይህን ፕሮግራምህን በማስታወሻ ደብተርህ ላይ አስፍረው። ያለህበትን ሁኔታ በሚገባ ታውቀዋለህ። የጤና ችግር ካለብህና አቅም የምታጣ ከሆነ በየዕለቱ ለጥቂት ሰዓታት ያህል በአገልግሎት መካፈል ትችል ይሆናል። የሙሉ ቀን ሠራተኛ ወይም ተማሪ ከሆንክ ምሽት ላይ ወይም ቅዳሜና እሁድ በአገልግሎት በመካፈል ረዳት አቅኚ መሆን ትችላለህ።
8. አንድ ባልና ሚስት ረዳት አቅኚ እንዲሆኑ ያስቻላቸው ምን ነበር?
8 ብዙዎች በቤተሰብ ደረጃ ረዳት አቅኚ ሆነው ማገልገል ችለዋል። ቀደም ባሉት ዓመታት አንድ ባልና ሚስት ሁኔታቸው ረዳት አቅኚ ሆነው ለማገልገል እንደማያስችላቸው ስለተሰማቸው በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ ለመካፈል አመንትተው ነበር። ታዲያ ምን አደረጉ? “ለረጅም ጊዜ ስንመኘው በነበረው በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ አብረን መካፈል እንድንችል እንዲረዳን ወደ ይሖዋ ጸለይን” ብለዋል። እነዚህ ባልና ሚስት የታሰበበት እቅድ አውጥተው ግባቸው ላይ መድረስ ችለዋል። አክለውም ሲናገሩ:- “በጣም አስደሳች ነበር። ብዙ በረከቶችን አግኝተናል። የምንመክራችሁ እንድትሞክሩት ነው። እኛ መሆን ከቻልን እናንተም መሆን ትችላላችሁ” ብለዋል።
9. ልዩ እንቅስቃሴ ለሚደረግባቸው ለቀጣዮቹ ወራት ለመዘጋጀት በሚቀጥለው የቤተሰብ ጥናታችሁ ላይ ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ?
9 በሚቀጥለው የቤተሰብ ጥናታችሁ ላይ ሁላችሁም በቀጣዮቹ ወራት በአገልግሎት የምታደርጉትን እንቅስቃሴ እንዴት ከፍ ማድረግ እንደምትችሉ ለምን አትወያዩም? መላው ቤተሰብ ረዳት አቅኚ መሆን ባይችል እንኳ ምናልባት አንዳችሁ ሌሎቹ የቤተሰብ አባላት በሚያደርጉላችሁ እርዳታና ትብብር ረዳት አቅኚ መሆን ትችሉ ይሆናል። ካልሆነም ቤተሰባችሁ ልዩ እንቅስቃሴ በሚደረግባቸው በእነዚህ ወራት በአገልግሎት ተጨማሪ ጊዜ ማሳለፍ እንዲችል ግብ ማውጣት ትችላላችሁ።
10. በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ረዳት አቅኚ ለመሆን ያለንን ፍላጎት ለሌሎች መናገር ያለብን ለምንድን ነው?
10 እርስ በርስ ተረዳዱ:- ቅንዓት ከአንዱ ወደ ሌላው የሚጋባ ነገር ነው። ረዳት አቅኚ የመሆን ግብ እንዳለህ ለሌሎች ተናገር። የአንተ ረዳት አቅኚ መሆን ሌሎችም እንዲሁ እንዲያደርጉ ሊገፋፋቸው ይችላል። በተጨማሪም ከዚህ በፊት ረዳት አቅኚ ሆነው ያገለገሉ ወንድሞችና እህቶች ግብህ ላይ መድረስ እንድትችል በአንዳንድ እንቅስቃሴዎችህና በፕሮግራምህ ላይ ምን ማስተካከያ እንደምታደርግ ምክር ሊሰጡህ ይችላሉ። (ምሳሌ 15:22) ረዳት አቅኚ መሆን ከቻልክ፣ ምናልባትም ከአንተ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ ሌላ አስፋፊ በዚህ አስደሳች እንቅስቃሴ አብሮህ እንዲካፈል ለምን ሐሳብ አታቀርብለትም?
11. ሽማግሌዎች በቀጣዮቹ ወራት ሌሎች ረዳት አቅኚ የመሆን ጉጉት እንዲያድርባቸው ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
11 በርካታ ሽማግሌዎች በዚህ ልዩ የአገልግሎት ዘርፍ ለመካፈል አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገዋል። (ዕብ. 13:7) ይህ በእርግጥም ጉባኤውን የሚያበረታታ ነው! ሽማግሌዎችም ስለ ረዳት አቅኚነት ከሌሎች ጋር በመጨዋወት ጉጉት እንዲያድርባቸው ማድረግ ይችላሉ። አንዳንዶች ረዳት አቅኚ ለመሆን የሚያስፈልጋቸው ጥቂት የማበረታቻ ቃላት ወይም ተግባራዊ ምክሮች ማግኘት ብቻ ሊሆን ይችላል። የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ ሁሉም በቡድን ሆኖ ምሥክርነት በመስጠቱ ሥራ ላይ እንዲካፈል ለማድረግ ከሥራ ወይም ከትምህርት በኋላ ተጨማሪ የመስክ ስምሪት ስብሰባዎች እንዲኖሩ ዝግጅት እንደሚያደርግ እሙን ነው። ይህ ከሆነ በየጊዜው ማስታወቂያ መነገር አለበት፤ በተጨማሪም በቂ የአገልግሎት ክልልና የሚበረከቱ ጽሑፎች መኖራቸውን ማረጋገጥ አለበት።
12. ረዳት አቅኚ መሆን ካልቻልክ ምን ማድረግ ትችላለህ?
12 በአንዳንድ ሁኔታዎች የተነሳ ረዳት አቅኚ መሆን ባትችል እንኳ በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ የሚካፈሉትን ልታበረታታቸውና ልትጸልይላቸው ትችላለህ። (ምሳሌ 25:11፤ ቈላ. 4:12) ምናልባትም በሳምንቱ ውስጥ በአገልግሎት ከእነርሱ ጋር ተጨማሪ ቀናት ለማሳለፍ ወይም ከሌላው ጊዜ ረዘም ያለ ሰዓት ለመቆየት ማስተካከያዎችን ማድረግ ትችል ይሆናል።
13. በኢትዮጵያ ምን ግብ ላይ ለመድረስ ታስቧል? ጉባኤያችሁ እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችለው እንዴት ነው?
13 በሚያዝያ ወር 2,000 ረዳት አቅኚዎችን የማግኘት ግብ:- በኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ከፍተኛ የረዳት አቅኚዎች ቁጥር የተመዘገበው በመጋቢት 2003 ሲሆን ቁጥሩም 1,918 ነበር። ስለዚህ በሚያዝያ ወር 2,000 ረዳት አቅኚዎችን እናገኛለን የሚል ሊደረስበት የሚችል ግብ አውጥተናል። በእያንዳንዱ ጉባኤ ውስጥ ከሚገኙት አራት አስፋፊዎች መካከል በአማካይ ከአንድ በላይ የሚሆኑት አስፋፊዎች ረዳት አቅኚ ከሆኑ እዚህ ግብ ላይ መድረስ እንችላለን። እርግጥ በአንዳንድ ጉባኤዎች ውስጥ ሁኔታቸው ረዳት አቅኚ እንዲሆኑ የሚፈቅድላቸው ከዚያም በላይ አስፋፊዎች ይኖራሉ። ብዙ ጉባኤዎች እዚህ ግብ ላይ መድረስ አይቸግራቸውም። ይህ ሁኔታ በጉባኤያችሁ ውስጥ ከፍተኛ የደስታ ስሜት እንደሚፈጥርና በክልላችሁ ውስጥ በሚከናወነው የስብከት ሥራ ላይ ገንቢ ውጤት እንደሚያመጣ መገመት አያዳግትም!
14. የሚያዝያ ወር ረዳት አቅኚ ለመሆን በጣም ጥሩ ጊዜ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
14 የሚያዝያ ወር ረዳት አቅኚ ለመሆን በጣም ጥሩ ጊዜ የሆነው ለምንድን ነው? የመታሰቢያው በዓል በወሩ መጀመሪያ ላይ ስለሚከበር ከዚያ በኋላ ያለው ጊዜ በበዓሉ ላይ የተገኙትን ሰዎች ተከታትለን ለመርዳት ጥሩ አጋጣሚ ይሰጠናል። በዚያ ወር የምናበረክተው መጽሔቶችን ሲሆን ይህን የምናደርገው በተመላልሶ መጠየቅ ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ የማበርከትና ጥናት የማስጀመር ግብ ይዘን ነው። ስለዚህ በሚያዝያ ረዳት አቅኚ መሆናችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ለማስጀመር ሰፊ አጋጣሚ ይፈጥርልናል። ከዚህም በተጨማሪ የሚያዝያ ወር አምስት እሁዶችና ሌሎች ሕዝባዊ በዓላት ስላሉት መደበኛ ሥራ ላላቸውና ተማሪ ለሆኑት ረዳት አቅኚ ለመሆን ሁኔታውን ያቀልላቸዋል።
15. የመታሰቢያው በዓል ሰሞን ሲቃረብ የጥድፊያ ስሜት ሊኖረን የሚገባው ለምንድን ነው?
15 እያንዳንዱ የመታሰቢያው በዓል ባለፈ ቁጥር ወደዚህ ሥርዓት መደምደሚያ በአንድ ዓመት እንቀርባለን። ለሌሎች ስለ ታላቁ አምላካችን ለመናገር የቀረን ጊዜ በጣም አጭር ነው። (1 ቆሮ. 7:29) ይህ የመታሰቢያው በዓል ሰሞን አንዴ ካለፈ በሰማይ የሚኖረውን አባታችንን ለማወደስ ያገኘነው ውድ አጋጣሚም ዳግም ላይመለስ ያልፋል። ስለዚህ በመጋቢት፣ በሚያዝያና በግንቦት ወራት የይሖዋን ግርማ በሰፊው ለማወጅ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ ከአሁኑ ዝግጅት እናድርግ!
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በሚያዝያ ወር 2,000 ረዳት አቅኚዎች ይኖሩን ይሆን?
◼ ቅድሚያ የምትሰጧቸውን ነገሮች በጥንቃቄ መርምሩ
◼ ግባችሁን በቤተሰብ ደረጃ ተወያዩበት
◼ ረዳት አቅኚ ለመሆን ማሰባችሁን ለሌሎች ተናገሩ