‘ምሥራቹን በሚገባ መሥክሩ’
1. ለሰዎች ልንነግራቸው የሚገባን ምሥራች ምንድን ነው?
1 አስደሳች ወሬ መስማት ብርቅ በሆነበት በዚህ ዓለም ውስጥ ‘የአምላክን ጸጋ ምሥራች በሚገባ የመመሥከር’ ልዩ መብት አለን። (ሥራ 20:24 NW) ይህም፣ ‘የመጨረሻው ዘመን’ ይሖዋ በሚያመጣው ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም በቅርቡ እንደሚተካ ለሰዎች ማሳወቅን ይጨምራል። በዚያ ጊዜ “የቀድሞ” የተባለው ይህ ‘ሥርዓት ያልፋል።’ (2 ጢሞ. 3:1-5፤ ራእይ 21:4) ከዚያ በኋላ በሽታ ጨርሶ አይኖርም። (ኢሳ. 33:24) እናፈቅራቸው የነበሩ ሙታን ከመታሰቢያው መቃብር በመውጣት ከቤተሰቦቻቸውና ከወዳጆቻቸው ጋር እንደገና ይገናኛሉ። (ዮሐ. 5:28, 29) መላዋ ምድር ውብ ወደሆነች ገነትነት ትለወጣለች። (ኢሳ. 65:21-23) እነዚህ ለሰዎች ልንነግራቸው ከሚገባን ምሥራች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው!
2. የመታሰቢያው በዓል የሚከበርበት ሰሞን ምሥራቹን ለማወጅ የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ ይከፍትልናል የምንለው ለምንድን ነው?
2 የመጋቢት፣ የሚያዝያና የግንቦት ወራት እንዲህ የመሰለውን ምሥራች ለማወጅ የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ ይከፍቱልናል። ከዚህም በተጨማሪ በዓመቱ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የሚይዘው የመታሰቢያው በዓል ቅዳሜ መጋቢት 22 ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ በመላው ዓለም ይከበራል። ስለዚህ የአገልግሎት እንቅስቃሴያችንን ከፍ ለማድረግ ዝግጅት ማድረግ ያለብን አሁን ነው።
3. በቤተሰብ ደረጃ በአገልግሎት የምናደርገውን እንቅስቃሴ ከፍ ለማድረግ ምን ሊረዳን ይችላል?
3 ረዳት አቅኚ:- በአንዱ ወይም በሁለቱ አሊያም ደግሞ በሦስቱም ወራት ረዳት አቅኚ ለመሆን ፕሮግራምህን ማስተካከል ትችላለህ? በቀጣዩ የቤተሰብ ጥናታችሁ ላይ ስለዚህ ጉዳይ ለመወያየት የተወሰነ ጊዜ ለምን አትመድቡም? ጥሩ የትብብር መንፈስ ካለ አንዱ ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ የቤተሰባችሁ አባላት ረዳት አቅኚ ሆነው ማገልገል ይችላሉ። (ምሳሌ 15:22) ጉዳዩን በጸሎት አስቡበት፤ ይሖዋም ጥረታችሁን እንደሚባርክላችሁ እርግጠኛ መሆን ትችላላችሁ። (ምሳሌ 16:3) ከቤተሰባችሁ መካከል ረዳት አቅኚ መሆን የሚችል ባይኖር እንኳ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት፣ አቅኚ ሆነው ማገልገል ከቻሉ የጉባኤው አባላት ጋር አብረው በመሥራት በአገልግሎቱ ያላቸውን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ ግብ ማውጣት ይችላሉ።
4. የሙሉ ቀን ሠራተኛ ከሆንን ረዳት አቅኚ ለመሆን በፕሮግራማችን ላይ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
4 የሙሉ ቀን ሠራተኛ ከሆንክ ጥሩ ፕሮግራም ማውጣትህ ረዳት አቅኚ ለመሆን ያስችልሃል። የተወሰነውን የምሳ እረፍትህን ለአገልግሎት ልትጠቀምበት ትችል ይሆናል። አሊያም በቤትህ ወይም በሥራ ቦታህ አቅራቢያ የግል የአገልግሎት ክልል በመውሰድ ከሥራ በፊት ወይም በኋላ ለአንድ ሰዓት ያህል ማገልገል ትችላለህ። እምብዛም አንገብጋቢ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎችን ለሌላ ጊዜ በማስተላለፍ እንዲሁም ቅዳሜና እሁድ ሙሉውን ቀን ለአገልግሎት በማዋል ተጨማሪ ጊዜ ማግኘት ትችላለህ። አንዳንዶች በመስክ አገልግሎት የሚያሳልፉት ተጨማሪ ጊዜ ለማግኘት ሲሉ አንድ ወይም ሁለት ቀን የዓመት ፈቃድ ወስደዋል።
5. አረጋዊ የሆኑ ወይም የአቅም ገደብ ያለባቸው አስፋፊዎች ረዳት አቅኚ እንዲሆኑ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?
5 አረጋዊ አሊያም የአቅም ገደብ ያለብህ ከሆንክ በእያንዳንዱ ቀን ጥቂት ሰዓት በማገልገል ረዳት አቅኚ መሆን ትችላለህ። ይሖዋ “እጅግ ታላቅ ኀይል” እንዲሰጥህ ጠይቀው። (2 ቆሮ. 4:7) አንዲት እህት በ106 ዓመታቸው ረዳት አቅኚ ሆነው ማገልገል ችለዋል! ክርስቲያን የሆኑ ዘመዶቻቸውና ሌሎች የጉባኤው አባላት ባደረጉላቸው እገዛ ከቤት ወደ ቤት በመሄድ አገልግለዋል፣ ተመላልሶ መጠየቅ አድርገዋል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ላይ ተገኝተዋል እንዲሁም በሌሎች የአገልግሎት እንቅስቃሴዎች ላይ ተካፍለዋል። አሥር ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምሩ ረድተዋል። እንዲህ በማለት የተሰማቸውን ተናግረዋል:- “ረዳት አቅኚ በመሆን የማገልገል አስደናቂ መብት ማግኘቴን ሳስብ ልቤ ለይሖዋ፣ ለልጁና አፍቃሪ ለሆነው ድርጅቱ ባለኝ ፍቅርና አድናቆት ይሞላል። ‘ይሖዋ፣ አመሰግንሃለሁ!’ በማለት ከልቤ ለመናገር እፈልጋለሁ።”
6. በመማር ላይ ያሉ የተጠመቁ ወጣቶች ረዳት አቅኚ መሆን የሚችሉት እንዴት ነው?
6 የተጠመቅህ ተማሪ ከሆንክ አንተም ረዳት አቅኚ መሆን ትችላለህ። እንደ ሙሉ ቀን ሠራተኞች ሁሉ አንተም ቅዳሜና እሁዶችን በዋነኝነት ለአገልግሎት ልትጠቀምባቸው ትችላለህ። በተጨማሪም ሌሎቹን ቀናት ከትምህርት ቤት መልስ ለአንድ ሰዓት ወይም ከዚያ በላይ ለሆነ ጊዜ አገልግሎት መውጣት ትችል ይሆናል። በአገልግሎት ለመካፈል የምትችልባቸው ትምህርት የሚዘጋባቸው ቀናት ይኖሩ ይሆን? ረዳት አቅኚ መሆን ከፈለግህ፣ ሐሳብህን ለወላጆችህ አካፍላቸው።
7. ሽማግሌዎች የመታሰቢያው በዓል በሚከበርበት ሰሞን የጉባኤውን የአገልግሎት መንፈስ ለማነቃቃት ምን ማድረግ ይችላሉ?
7 የጉባኤውን መንፈስ አነቃቁ:- ሽማግሌዎች ምሳሌ በመሆን የጉባኤውን የአገልግሎት መንፈስ ለማነቃቃት ብዙ ማድረግ ይችላሉ። (1 ጴጥ. 5:2, 3) ሽማግሌዎች፣ ማለዳ ላይ አሊያም ከትምህርት ቤት ወይም ከሥራ መልስ ማገልገል ለሚፈልጉ አስፋፊዎች ተጨማሪ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎችን ማዘጋጀት ይችላሉ። የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ ልዩ እንቅስቃሴ በሚደረግባቸው በእነዚህ ወራት፣ የስምሪት ስብሰባውን የሚመሩ ብቃት ያላቸው አስፋፊዎች መመደብና በቂ የሆነ የአገልግሎት ክልል እንዲሁም መጽሔቶችና ጽሑፎች እንዲኖሩ ማድረግ ይኖርበታል።
8. በአንድ ጉባኤ ያሉ ሽማግሌዎች ካደረጉት ነገር ምን እንማራለን?
8 በአንድ ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌዎች የጉባኤው አስፋፊዎች ረዳት አቅኚ በመሆን እንዲያገለግሉ የተወሰኑ ወራት አስቀድመው ማበረታቻ መስጠት ጀመሩ። ምን ያህል አስፋፊዎች ረዳት አቅኚዎች ሆነው እንዲያገለግሉ እንደተፈቀደላቸው በየሳምንቱ ለጉባኤው ማስታወቂያ ይነግሩ ነበር። እንዲህ ማድረጋቸው አገልግሎታቸውን ከፍ ማድረግ የሚፈልጉ አስፋፊዎች አብረዋቸው ሊያገለግሉ የሚችሉ በርካታ አስፋፊዎች እንዳሉ እንዲሰማቸው አድርጓቸዋል። ማለዳና አመሻሹ ላይ ማገልገል ለሚፈልጉ አስፋፊዎች ተጨማሪ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎች ተዘጋጁ። በውጤቱም ከጉባኤው አስፋፊዎች ግማሽ ያህሉ ማለትም 53 አስፋፊዎች በሚያዝያ ወር ረዳት አቅኚ በመሆን አገልግለዋል!
9. የመታሰቢያው በዓል ሰሞን፣ ብቃቱን የሚያሟሉ ሰዎች አስፋፊነት ለመጀመር አመቺ ጊዜ የሚሆንላቸው ለምንድን ነው?
9 ሌሎች በአገልግሎት እንዲካፈሉ እርዷቸው:- አዲሶችም ሆኑ ወጣቶች ያልተጠመቁ አስፋፊዎች ለመሆን ብቃቱን ሲያሟሉ ልምድ ካላቸው አስፋፊዎች ጋር በመስክ አገልግሎት አብረው ማገልገል እንዲጀምሩ ግብዣ ሊቀርብላቸው ይችላል። በጉባኤ ውስጥ ያሉ ብዙ አስፋፊዎች የአገልግሎት እንቅስቃሴያቸውን ከፍ የሚያደርጉበት የመታሰቢያው በዓል ሰሞን አዲሶችም ሆኑ ወጣቶች አገልግሎት ለመጀመር የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል። ሕይወቱን ከአምላክ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር ያስማማ እድገት እያደረገ ያለ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አለህ? ጥሩ እድገት በማድረግ ላይ ያሉና መልካም ጠባይ ያላቸው ሆኖም ገና አስፋፊ ያልሆኑ ልጆች አሉህ? እነሱም ሆኑ አዲሶች፣ ያልተጠመቁ አስፋፊዎች የመሆን ፍላጎት እንዳላቸው ከገለጹልህና አንተም ብቃቱን እንደሚያሟሉ ከተሰማህ ሁኔታውን ለአንድ የጉባኤ ሽማግሌ መንገር ትችላለህ። ሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹ ሁለት ሽማግሌዎች ልጅህን ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪህን አንተ በተገኘህበት እንዲያነጋግሩት ዝግጅት ያደርጋል።
10. ሽማግሌዎች ቀዝቅዘው የነበሩትን ለመርዳት ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?
10 በተጨማሪም መጪዎቹ ወራት ከጉባኤው ጋር ያደርጉት የነበረውን እንቅስቃሴ እንደገና መቀጠል ለሚፈልጉ የቀዘቀዙ አስፋፊዎችም በጣም ጥሩ ጊዜ ይሆንላቸዋል። የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቾችና ሌሎች ሽማግሌዎች እንደነዚህ ያሉትን ለመጠየቅና በአገልግሎት ከእነሱ ጋር አብረው መሥራት እንደሚፈልጉ ሞቅ ያለ ግብዣ ለማቅረብ ትጋት የተሞላበት ጥረት ማድረግ ይገባቸዋል። አገልግሎት ካቆሙ ረጅም ጊዜ ከሆናቸው፣ መጀመሪያ ብቁ መሆናቸውን ለመወሰን ሁለት ሽማግሌዎች ሊያነጋግሯቸው ያስፈልጋል።—የመንግሥት አገልግሎታችን 11/00 ገጽ 3
11. ከሁሉ የላቀው ‘የአምላክ የጸጋ’ ስጦታ መግለጫ ምንድን ነው?
11 ለመታሰቢያው በዓል ተዘጋጁ:- ቤዛው፣ ከሁሉ የላቀው ‘የአምላክ የጸጋ’ ስጦታ መግለጫ ነው። (ሥራ 20:24) ለዚህ ዝግጅት አድናቆት ያላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ ለማክበር ቅዳሜ መጋቢት 22 ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ይሰበሰባሉ። ይሖዋ ለሰው ዘር ለሰጠው ጸጋ ምሥክርነት ለመስጠት በሚያስችለው በዚህ አስደሳች በዓል ላይ እንዲገኙ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች መጋበዝና መርዳት እንፈልጋለን።
12. በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ እነማንን መጋበዝ ይኖርብናል?
12 ለመጋበዝ ያሰብካቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር በማስታወሻህ ላይ አስፍር። የምትጽፈው ስም ዝርዝር ዘመዶችህን፣ ጎረቤቶችህን፣ በሥራና በትምህርት ቤት የምታውቃቸውን ሰዎች፣ ጥናታቸውን አቋርጠው የነበሩትንና በአሁን ጊዜ እያጠኑ ያሉትን እንዲሁም በቋሚነት ተመላልሶ መጠየቅ የምታደርግላቸውንና ሌሎችንም እንደሚጨምር ምንም ጥርጥር የለውም። ከጋበዝካቸው ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ የመታሰቢያውን በዓል አስመልክቶ ጥያቄ ካላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተባለው መጽሐፍ ገጽ 206-208 ላይ የጌታ እራትን አስመልክቶ የሚናገረው ተጨማሪ ክፍል ጠቃሚ ሆኖ ታገኘው ይሆናል። እንዲህ ያለው አጋጣሚ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት የምንጠቀምበትን ይህን ጽሑፍ ለማስተዋወቅ ስለሚረዳህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር በር ሊከፍትልህ ይችላል።
13. ሁለት አስፋፊዎች ሌሎችን ለመጋበዝ ያደረጉትን ጥረት ይሖዋ የባረከላቸው እንዴት ነው?
13 አንዲት እህት 48 ቤተሰቦችን ለመጋበዝ ስም ዝርዝራቸውን በማስታወሻዋ ላይ አሰፈረች። እህት እነዚህን ሰዎች በምትጋብዝበት ጊዜ ስማቸውን በመሰረዝ ምልክት ታደርግ የነበረ ሲሆን የጋበዘችበትንም ቀን ትጽፍ ነበር። ከጋበዘቻቸው መካከል 26ቱ በመታሰቢያው በዓል ላይ በመገኘታቸው ምንኛ ተደስታ ይሆን! ሱቅ ያለው አንድ ወንድም ደግሞ ቀድሞ ቄስ የነበረ ተቀጣሪውን ይጋብዘዋል። ሰውየው በመታሰቢያው በዓል ላይ ከተገኘ በኋላ “በካቶሊክ እምነት ውስጥ ለ30 ዓመት ስቆይ ያላገኘሁትን ትምህርት በአንድ ሰዓት ውስጥ ተማርኩ” በማለት አድናቆቱን ገልጿል። ከመታሰቢያው በዓል በኋላ ብዙም ሳይቆይ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተባለው መጽሐፍ ጥናት እንዲጀምር የቀረበለትን ግብዣ ተቀበለ።
14. መጋቢት 1 ላይ በምድር ዙሪያ ምን ዘመቻ ይጀመራል?
14 ዘመቻ:- ከቅዳሜ መጋቢት 1 ጀምሮ እስከ መጋቢት 22 ድረስ ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ የሚጋብዝ ልዩ የመጋበዣ ወረቀት ስርጭት ዘመቻ በዓለም ዙሪያ ይደረጋል። ሁሉም አስፋፊዎች በዚህ አስፈላጊ ዘመቻ ላይ የቻሉትን ያህል ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። የመጋበዣ ወረቀቱን በር ሥር ከመተው ይልቅ ለቤቱ ባለቤት በእጁ መስጠቱ የተሻለ ነው። ነገር ግን ክልላችሁ ሰፊ ከሆነ፣ ሽማግሌዎች ቤታቸው ላልተገኙ ሰዎች የመጋበዣ ወረቀቱ ጥበብ በተሞላበት ሁኔታ በራቸው ላይ እንዲተውላቸው ሊወስኑ ይችላሉ። ከዚህም በተጨማሪ ቅዳሜና እሁድ ወቅታዊ መጽሔቶችን እናበረክታለን።
15. የመጋበዣውን ወረቀት በምንሰጥበት ጊዜ ምን ማለት እንችላለን?
15 የመጋበዣውን ወረቀት የምናሰራጭበት ጊዜ አጭር በመሆኑ አጠር ያለ መግቢያ ብንጠቀም ይመረጣል። ወዳጃዊ መንፈስና ሞቅ ያለ ስሜት ይኑርህ። ምናልባት እንዲህ ማለት ትችል ይሆናል:- “የመጣነው እርስዎን፣ ቤተሰብዎንና ወዳጆችዎን መጋቢት 22 በሚከበር አንድ ትልቅ በዓል ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ ነው። የመጋበዣ ወረቀቱ ይሄ ነው። ዝርዝር ሐሳቡ በዚህ መጋበዣ ወረቀት ላይ ሰፍሯል።” የቤቱ ባለቤት ጥያቄ ሊኖረው ይችላል፤ አሊያም የመጋበዣ ወረቀቱን ይቀበል እንዲያውም በበዓሉ ላይ እንደሚገኝ ይገልጽ ይሆናል። በመሆኑም ፍላጎት ያሳዩትን መዝግበህ ያዝ እንዲሁም በሌላ ጊዜ ለማነጋገር ዝግጅት አድርግ።
16. በክልላችን ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ የመጋበዙ ዘመቻ አስፈላጊ መሆኑን የትኛው ተሞክሮ ያሳያል?
16 ባለፈው ዓመት አንድ ወታደር የመጋበዣውን ወረቀት በሩ ሥር አገኘ። በበዓሉ ላይ ለመገኘት ቢፈልግም ከአለቃው ፈቃድ ማግኘት ነበረበት። ወታደሩ የመጋበዣውን ወረቀት ለአለቃው ሲያሳየው አለቃው መጀመሪያ ላይ ዝም ካለ በኋላ ወላጆቹ የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑና አብሯቸው ስብሰባ ይሄድ እንደነበር ነገረው። አለቃው ፈቃድ መስጠት ብቻ ሳይሆን፣ ከወታደሩ ጋር አብሮ ወደ መታሰቢያው በዓል ሄደ!
17. የአምላክን ጸጋ ከንቱ እንዳላደረግን እንዴት ማሳየት እንችላለን?
17 አድናቆታችሁን ግለጹ:- በ2008 የሚደረገው የመታሰቢያው በዓል ሲቃረብ እያንዳንዳችን ከይሖዋ ስላገኘነው ጸጋ በጥልቅ ለማሰብ የበኩላችንን እናድርግ። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘የተቀበላችሁትን የአምላክን ጸጋ ከንቱ እንዳታደርጉት ዐደራ እንላችኋለን’ በማለት ጽፏል። (2 ቆሮ. 6:1) የአምላክን ጸጋ ከንቱ እንዳላደረግን እንዴት በተግባር ማሳየት እንችላለን? ጳውሎስ “ይሁን እንጂ በምናደርገው ነገር ሁሉ ራሳችንን እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች እናቀርባለን” በማለት ጽፏል። (2 ቆሮ. 6:4) እንግዲያው መልካም ምግባር በማሳየትና ምሥራቹን በቅንዓት በመስበክ ይሖዋ ለሰጠን ስጦታ ያለንን አድናቆት እናሳይ። የመታሰቢያው በዓል የሚከበርበት ሰሞን ምሥራቹን በሚገባ በመስበክ የአገልግሎት እንቅስቃሴያችንን ከፍ ለማድረግ የሚያስችለን ግሩም አጋጣሚ ይሰጠናል።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እነማን ረዳት አቅኚ ሊሆኑ ይችላሉ?
◼ ቤተሰቦች
◼ የሙሉ ቀን ሠራተኞች
◼ አረጋውያንና አቅመ ደካሞች
◼ ተማሪዎች
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመታሰቢያውን በዓል የመጋበዣ ወረቀት በምታሰራጭበት ጊዜ፦
◼ አጠር ያለ መግቢያ ይኑርህ፤ ሞቅ ባለ መንፈስ ተናገር
◼ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች መዝግበህ ያዝ፤ እንዲሁም ተመላልሶ መጠየቅ አድርግላቸው
◼ ቅዳሜና እሁድ መጽሔቶችን አበርክት