የመታሰቢያው በዓል ሰሞን—አገልግሎታችንን ከፍ ለማድረግ የሚያስችል አጋጣሚ!
1. በመጋቢት፣ በሚያዝያና በግንቦት ወር አገልግሎታችንን ከፍ ለማድረግ የሚያነሳሱ ምን ምክንያቶች አሉን?
1 ከፊታችን ባለው የመታሰቢያ በዓል ሰሞን አገልግሎታችሁን ከፍ ማድረግ ትችላላችሁ? ይህ ወቅት በብዙ አካባቢዎች ጥሩ የአየር ሁኔታ የሚኖርበትና ቀኑ ረዘም የሚልበት ጊዜ ነው። አንዳንድ አስፋፊዎች አገልግሎታቸውን ለማስፋት የሥራ ፈቃዳቸውን ወይም የትምህርት ቤት እረፍታቸውን ይጠቀማሉ። ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ሚያዝያ 17 የሚከበረውን የመታሰቢያ በዓል ከእኛ ጋር እንዲያከብሩ ለመጋበዝ ከሚያዝያ 2 ጀምሮ ልዩ ዘመቻ እናደርጋለን። ከዚያም በስብሰባው ላይ የተገኙ ሰዎችን ፍላጎት ለማሳደግና ሚያዝያ 25 በሚጀምረው ሳምንት ውስጥ በሚቀርበው ልዩ ንግግር ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ ጥረት እናደርጋለን። በእርግጥም በመጋቢት፣ በሚያዝያና በግንቦት ወር አገልግሎታችንን ከፍ ለማድረግ የሚያነሳሱ በቂ ምክንያቶች አሉን።
2. አገልግሎታችንን ለማስፋት የምንችልበት አንደኛው ግሩም መንገድ ምንድን ነው?
2 ረዳት አቅኚነት፦ አገልግሎታችንን ከፍ ማድረግ የምንችልበት አንዱ ግሩም መንገድ ረዳት አቅኚ መሆን ነው። ሁላችንም ያለን ጊዜ የተጣበበ እንደመሆኑ መጠን ረዳት አቅኚ መሆን አስቀድሞ እቅድ ማውጣትና በፕሮግራማችን ላይ አንዳንድ ማስተካከያዎች ማድረግ ይጠይቃል። (ምሳሌ 21:5) ምናልባትም በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴህ ውስጥ የምታከናውናቸው በጣም አንገብጋቢ ያልሆኑ አንዳንድ ነገሮችን ለሌላ ጊዜ ማስተላለፍ ትችል ይሆናል። (ፊልጵ. 1:9-11) በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞች አብረውህ ረዳት አቅኚ መሆን ይችሉ እንደሆነ ለማወቅ አቅኚ ለመሆን ያለህን ፍላጎት ለምን አትነግራቸውም?
3. ቤተሰቦች የአገልግሎት እንቅስቃሴያቸውን ከፍ ለማደረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
3 በሚቀጥለው የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችሁ ላይ ምን ግብ ማውጣት እንደምትችሉ በቤተሰብ ደረጃ ብትወያዩበት ጥሩ ይሆናል። (ምሳሌ 15:22) እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ከተባበረ አንዳንድ የቤተሰቡ አባላት ለአንድ ወይም ከዚያ ለሚበልጡ ወራት ረዳት አቅኚ ሊሆኑ ይችላሉ። ቤተሰባችሁ እንዲህ ማድረግ እንደማይችል ከተሰማችሁስ? ቤተሰባችሁ ምሽት ላይ በሚደረግ አገልግሎት ለመካፈል ወይም በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ረዘም ያለ ሰዓት ለማገልገል ዝግጅት በማድረግ የአገልግሎት እንቅስቃሴያችሁን ከፍ ማድረግ ትችላላችሁ።
4. በዚህ የመታሰቢያ በዓል ሰሞን የአገልግሎት እንቅስቃሴን ከፍ በማድረጋችን ምን በረከቶችን ያስገኝልናል?
4 ይሖዋ እሱን ለማገልገል የምናደርገውን እያንዳንዱን ጥረት የሚመለከት ከመሆኑም በላይ የምንከፍላቸውን መሥዋዕቶች ያደንቃል። (ዕብ. 6:10) ደስታ የሚገኘው ለይሖዋና ለሌሎች ያለንን በመስጠት ነው። (1 ዜና 29:9፤ ሥራ 20:35) አንተስ በዚህ የመታሰቢያ በዓል ሰሞን የአገልግሎት እንቅስቃሴን ከፍ በማድረግ የሚገኘውን ደስታና በረከት ለማጨድ ተዘጋጅተሃል?