የመታሰቢያው በዓል የሚከበርበት ወቅት አስደሳች እንዲሆንላችሁ አድርጉ!
1. የመታሰቢያው በዓል በሚከበርበት ወቅት ደስታችን እንዲጨምር ማድረግ ከምንችልባቸው መንገዶች አንዱ ምንድን ነው?
1 በመጋቢት፣ በሚያዝያ እና በግንቦት ወራት ደስታችሁ እንዲጨምር ማድረግ ትፈልጋላችሁ? ይህን ማድረግ ከምትችሉባቸው መንገዶች አንዱ በአገልግሎት የምታደርጉትን ተሳትፎ ከፍ ማድረግ፣ ከተቻለ ደግሞ ረዳት አቅኚ መሆን ነው። እንዲህ ማድረጋችሁ ደስታችሁ እንዲጨምር የሚያደርገው እንዴት ነው?
2. በአገልግሎት የምናደርገውን ተሳትፎ ከፍ ማድረጋችን ደስታችንን የሚጨምርልን እንዴት ነው?
2 ደስታችሁ እንዲጨምር አድርጉ፦ ይሖዋ የፈጠረን እሱን በማምለክ እንዲሁም ተፈጥሯዊ የሆነውን መንፈሳዊ ፍላጎታችንን በማሟላት ደስታ እና እርካታ እንድናገኝ አድርጎ ነው። (ማቴ. 5:3) በተጨማሪም ለሌሎች በመስጠት ደስታ እንድናገኝ አድርጎ ፈጥሮናል። (ሥራ 20:35) አገልግሎታችን ደግሞ እነዚህን ሁለት ነገሮች እንድናደርግ ይኸውም ይሖዋን እንድናመልክና ሰዎችን እንድንረዳ ያስችለናል። ከዚህ አንጻር በአገልግሎት የምናሳልፈውን ጊዜ ከፍ ማድረጋችን የዚያኑ ያህል ደስታችን እንዲጨምር ያደርጋል ቢባል ምክንያታዊ ነው። በተጨማሪም በስብከቱ ሥራ ይበልጥ በተካፈልን መጠን ችሎታችንን እያሻሻልን እንሄዳለን። ችሎታችን ማደጉ ደግሞ ድፍረት የሚጨምርልን ከመሆኑም ሌላ የሚሰማንን ፍርሃት ይቀንስልናል። ለሰዎች ለመመሥከርና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር የሚያስችል ተጨማሪ አጋጣሚ እናገኛለን። እነዚህ ሁሉ ነገሮች አገልግሎታችንን የበለጠ አስደሳች ያደርጉልናል።
3. በተለይ መጋቢት እና ሚያዝያ፣ ረዳት አቅኚ ለመሆን አመቺ ወራት የሆኑት ለምንድን ነው?
3 በተለይም መጋቢትና ሚያዝያ ረዳት አቅኚ ሆኖ ለማገልገል አመቺ ወራት ናቸው፤ ምክንያቱም በእነዚህ ወራት ከ30 ወይም ከ50 ሰዓት አንዱን በመምረጥ ረዳት አቅኚ ሆነን የማገልገል አጋጣሚ አለን። በተጨማሪም ከቅዳሜ መጋቢት 22 ጀምሮ የመታሰቢያው በዓል እስከሚከበርበት እስከ ሚያዝያ 14 ድረስ በሚዘልቀው ሰዎች በበዓሉ ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ በሚደረገው አስደሳች ዘመቻ ላይ እንካፈላለን። ብዙዎች በተመደበው ጊዜ ውስጥ በተቻለ መጠን ብዙ ክልሎችን ለመሸፈን “እጅ ለእጅ ተያይዘው” ስለሚሠሩ በሁሉም ጉባኤዎች ውስጥ በጣም አስደሳች መንፈስ እንደሚኖር የታወቀ ነው።—ሶፎ. 3:9 NW
4. ረዳት አቅኚ ለመሆን ከፈለግን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
4 አሁኑኑ ዝግጅት አድርጉ፦ እስካሁን እቅድ ካላወጣህ ጊዜ ወስደህ ፕሮግራምህን ገምግም፤ ከዚያም ለአንድ ወር ወይም ከዚያ በላይ አገልግሎትህን ለማስፋት ምን ማስተካከያዎችን ልታደርግ እንደምትችል አስብ። ስለ ጉዳዩ በጸሎት አስብበት። (ያዕ. 1:5) ከቤተሰብህ አባላትና በጉባኤ ውስጥ ካሉ ሌሎች አስፋፊዎች ጋር ተነጋገር። (ምሳሌ 15:22) የጤና ችግር ቢኖርብህም ወይም ፕሮግራምህ የተጣበበ ቢሆንም እንኳ ረዳት አቅኚ መሆን የሚያስገኘውን ደስታ መቅመስ ትችል ይሆናል።
5. የመታሰቢያው በዓል በሚከበርበት ሰሞን አገልግሎታችንን ማስፋታችን ምን ውጤት ያስገኛል?
5 ይሖዋ አገልጋዮቹ ደስተኛ እንዲሆኑ ይፈልጋል። (መዝ. 32:11) የመታሰቢያው በዓል በሚከበርበት ሰሞን አገልግሎታችንን ለማስፋት ጥረት ማድረጋችን ደስታችን እንዲጨምር የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ ለሰማዩ አባታችንም ደስታ ያመጣል።—ምሳሌ 23:24፤ 27:11