ጊዜው አሁን ነው
1 ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለነበሩ ክርስቲያኖች ሁለተኛ መልእክቱን ሲጽፍላቸው ቀደም ሲል በኢየሩሳሌም ላሉት መሰል የእምነት ወዳጆቻቸው ሊሰጡ አስበው የነበሩትን እርዳታ አስታወሳቸው። አንድ ዓመት ያህል ቢያልፍም የጀመሩትን ሥራ አልፈጸሙም ነበር። ስለዚህ “ቀጥሉና ፈጽሙት:- ለመሥራት ስታስቡ እንደጓጓችሁ ሁሉ ያሰባችሁትን ለመፈጸምም ተመሳሳይ ጉጉት አሳዩ” ሲል አሳሰባቸው። — 2 ቆሮ. 8:11 ዘ ኒው እንግሊሽ ባይብል
2 ሁላችንም በአንድ ወቅት በግላችን ግብ አውጥተን ነበር። በመስክ አገልግሎት ያለንን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ፣ ወንድሞቻችንን በደንብ ለማወቅ፣ ወደ ተሻለ የአገልግሎት መብት ለመድረስ ወይም ድካማችንን ለማሸነፍ ወስነን ሊሆን ይችላል። በጥሩ መንፈስ ብንጀምረውም ግባችንን ዳር እስኪደርስ አልገፋንበት ይሆናል። ምንም ሳናደርግ ሳናስበው ሳምንታት፣ ወራት ወይም እንዲያውም ዓመታት አልፈው ሊሆን ይችላል። የጀመርነውን ‘ቀጥለን እንድንፈጽመው’ የተሰጠንን ምክር እንድንሠራበት ያስፈልገን ይሆን?
3 ግቦቻችን ላይ መድረስ፦ አንድን ግብ ዳር ማድረስ ግቡን ከማውጣት የበለጠ ይከብዳል። ዛሬ ነገ ማለት ለመሻሻል የምናደርገውን ጥረት ሊያከሽፍብን ይችላል። ቁርጥ ያለ ውሳኔ ማድረግና ሳንዘገይ ግባችንን ወደ ፍጻሜ ለማድረስ መቁረጥ አለብን። የተደራጁ መሆን አስፈላጊ ነው። ሥራውን ለመሥራት የሚያስፈልገውን ጊዜ መመደብና ጊዜውን ለዚያ ዓላማ መጠቀማችንን ማረጋገጥ ጠቃሚ ነው። ሥራችንን የምናጠናቅቅበትን ጊዜ መወሰንና በዚሁ ጊዜ ውስጥ ለመፈጸም ራስን መገሠጽ ጥሩ ነው።
4 ግባችንን መፈጸም ሲከብደን ‘ሌላ ጊዜ እጀምረዋለሁ’ ብሎ ማሰብ ቀላል ነው። ይሁን እንጂ ወደፊት የሚሆነውን አናውቅም። ምሳሌ 27:1 “ቀን የሚያመጣውን ምን እንደሆነ አታውቅምና ነገ በሚሆነው አትመካ” ሲል ይገልጻል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ነገ የሚሆነውን አታውቁምና . . . በጎ ለማድረግ አውቆ ለማይሠራው ኃጢአት ነው” በማለት ስለ ወደፊቱ ጊዜ ከሚገባው በላይ እንዳንመካ አስጠንቅቆናል።— ያዕ. 4:13–17
5 ሐሳብን የሚከፋፍሉ ብዙ ነገሮች ከመኖራቸውም በተጨማሪ ሌሎች ሰዎች እንድናደርግላቸው የሚፈልጓቸው ነገሮች ግባችንን በቀላሉ ሊያስረሱን ይችላሉ። በአእምሮአችን ትኩስ ሆነው እንዲቆዩ ከተፈለገ የታሰበበት ጥረት ልናደርግ ይገባል። ጉዳዩን በጸሎታችን ውስጥ ዘወትር መጥቀስ ይረዳል። በቅርብ የምናውቃቸው ሰዎች እንዲያስታውሱንና እንዲያበረታቱን መጠየቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። በቀን መቁጠሪያችን ላይ ማስታወሻ ማስፈር እድገታችንን ለመገምገም እንደ ማሳሰቢያ ያገለግላል። አንድ ግለሰብ “በልቡ እንዳሰበ” ለማድረግ መቁረጥ አለበት።— 2 ቆሮ. 9:7
6 የጥቅምት ወር በግቦቻችን ላይ ለማተኮር ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥርልናል። በዚህ ወር የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት ቅጂዎችን እናበረክታለን። አብዛኛውን ጊዜ በተመላልሶ መጠየቅ ወቅት እነዚህን መጽሔቶች ኮንትራት ማስገባት ይቻላል። አንዳንድ ልንደርስባቸው የምንችላቸውን ምክንያታዊ ግቦች ልናወጣ እንችላለን? የምናበረክታቸውን መጽሔቶች ቁጥርስ ከፍ ልናደርግ እንችላለንን? ተጨማሪ ተመላልሶ መጠየቆችን ማድረግና አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ማስጀመር ለብዙዎች ምክንያታዊ ግቦች ሊሆኑ ይችላሉ።
7 ይህ ‘ዓለም ስለሚያልፍ ’ አስፈላጊ የሆነውን ነገር ለሌላ ጊዜ ማስተላለፍ ጥበብ አይደለም። (1 ዮሐ. 2:17) በአሁኑ ወቅት በይሖዋ አገልግሎት ረገድ ልናገኛቸው የምንችላቸው ልዩ መብቶችና ብዙ በረከቶች አሉ። በእነዚህ መብቶች መጠቀም የእኛ ፈንታ ነው።