ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ በመጠቀም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ማስጀመር
1 ለሰዎች ያለን ፍቅር እውነትን የተራቡትንና የተጠሙትን ለመርዳት ቶሎ ተመልሰን እንድንጠይቃቸው ያንቀሳቅሰናል። (ማቴ. 5:6) ሰዎቹ ያሳዩት ማንኛውም ፍላጎት እንዳይጠፋ ከፈለግን ስሜታቸውን ልብ ልንለውና ልናሳድገው ይገባል። የተሳካ ውጤት ለማግኘት ቁልፉ ዝግጅት ነው።
2 ግባችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ለማስጀመር መሆን አለበት። (ማቴ. 28:20) ለዘላለም መኖር የተባለው መጽሐፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲታተም በመግቢያው ላይ ቀጥሎ ያለውን ሐሳብ ይዞ ነበር፦ “ይህ መጽሐፍ ከወጣቶችም ሆነ ከአዋቂዎች እንዲሁም የቱንም ዓይነት የትምህርት ደረጃ ካላቸው ከማናቸውም ሰዎች ጋር ለማጥናት የሚረዳ ግሩም መጽሐፍ ነው።” ሌላው ቀርቶ አዲስ አስፋፊዎች እንኳን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መምራት በሚችሉበት ቀላል መንገድ የተጻፈ ነው። አዲስ ጥናቶች ማግኘታችን የተመካው ውጤታማ ተመላልሶ መጠየቆችን በማድረጋችን ላይ ነው።
3 ጥናት ማስጀመር የምንችለው እንዴት ነው? አብዛኛውን ጊዜ ተመላልሶ መጠየቅ ስናደርግ በመጀመሪያ ጉብኝታችን የተጠቀሱትን ጥቂት ነጥቦች መከለስ ወይም የተነሣውን ጥያቄ ከውይይታችን ጋር ማዛመድ ጥሩ ነው። ምናልባት ስለ ሙታን ሁኔታ ከሰውዬው ጋር ተወያይተህ “እናፈቅራቸው የነበሩ ሙታን ምን ተስፋ አላቸው?” በሚለው ጥያቄ ሐሳቡን አንጠልጥለህ ይሆናል። ትንሣኤ መሠረት የሌለው ተስፋ እንዳልሆነ አብራራ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ የሚሆኑ ከዚህ በፊት የተፈጸሙ ብዙ ትንሣኤዎችን ዘግቧል። ከገጽ 167-9 ያሉትን ሥዕሎች ከልስ። ከዚያም ከገጽ 166 አንቀጽ 1 እና 2 ላይ የተገለጸውን ሐሳብ አብራራ። ሰውዬው ፍላጎት ካሳየ ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ ተመልሰህ መምጣት እንደምትፈልግ ግለጽለት።
4 ምናልባት ልጆችን ከማሳደግ ጋር በተያያዘ እየጨመረ የመጣው ችግር ካሳሰበው ወላጅ ጋር ተነጋግረህ ይሆናል። በራስህ አባባል ቀጥሎ ካለው ጋር ተመሳሳይ የሆነ ነገር ልትናገር ትችላለህ፦
◼ “ሁሉም ወላጆች ልጆቻቸው ጥሩ ነገር እንዲያገኙ ይፈልጋሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ወላጆች ልጆቻቸውን ትርጉምና ዓላማ ያለው የሚያረካ ሕይወት እንዲያገኙ ለማስተማር ወላጆችን የሚረዳቸው ሐሳብ ይዟል። ስለዚህ ቤተሰቦች አንድ ላይ ሆነው መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ በጣም እናበረታታቸዋለን። [ገጽ 246 አንቀጽ 23ን አውጥተህ አንብብለት።] መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት የሚገኘው እውቀት ለጠቅላላው ቤተሰብ ዘላለማዊ በረከቶችን ሊያስገኝ ይችላል። ዮሐንስ 17:3ን አንብብ። ቤተሰቡ ጥናታቸውን እንዴት መጀመር እንደሚችሉ ለማሳየት ሌላ ጊዜ ለመምጣት እንደምትፈልግ ግለጽ።
5 ወጣት ወይም አዲስ አስፋፊ ከሆንክና በመጀመሪያ ጉብኝትህ ስለ ገነት ተስፋ በአጭሩ ተወያይተህ ከነበረ ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 3 ላይ አውጥተህ እንዲህ በል፦
◼ “መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርጉ ሰዎች ሰላምና ደስታ ባለበት ዓለም ውስጥ ለመኖር ተስፋ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ያበስራል። ይህ መጽሐፍ ይህን በረከት ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለብን ያሳያል።” በአጭሩ እንዴት እንደምናስጠና ግለጽለትና አጠናኑን በተግባር ልታሳየው እንደምትፈልግ ጥቀስለት።
6 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደመሆናችን መጠን ሰዎችን የመርዳት ግዴታ አለብን። (ሮሜ 10:14) ጽሑፍ አበርክተን ወይም ጥሩ ውይይት አድርገን ከሆነ ሰዎቹ ያሳዩትን ፍላጎት የማሳደግ ኃላፊነት አለብን። (ማቴ. 9:37, 38) ይህን ሥራ በተገቢ መንገድ ካከናወንን ሁላችንም ከሚገኘው በረከት ተካፋይ መሆን እንችላለን።—1 ጢሞ. 4:16