ሰዎች ለዘላለም መኖር ለተባለው መጽሐፍ ፍላጎት እንዲያድርባቸው አድርግ
1 አብዛኛውን ጊዜ ሰዎችን ቤታቸው ሄደን ስናነጋግራቸው ‘በዚህ ዓለም አሳብ’ ተውጠው እናገኛቸዋለን። (ማር. 4:19) አእምሮን በሚያመራምር አቀራረብ ትኩረታቸውን የመሳብ ፈተና ያጋጥመናል። መጀመሪያ ላይ ብዙ ሰዎች ለመልእክታችን እምብዛም ፍላጎት አይኖራቸው ይሆናል። ሕይወታቸውን የሚነካ አንድ ነገር መናገር ከቻልን ግን በመጠኑም ቢሆን ለመንግሥቱ መልእክት ያላቸውን ፍላጎት መቀስቀስ እንችላለን። ውይይት ለመጀመር ከሚያስችሉት ቁልፍ ነገሮች አንዱ ለዘላለም መኖር ከተባለው መጽሐፍ ማራኪ የመነጋገሪያ ነጥቦች መምረጥ ነው። ምን ልትል ትችላለህ?
2 በዚህ አቀራረብ ትጠቀም ይሆናል፦
◼ “ኃይል ቢኖርዎት ኖሮ በዘመናችን ካሉት በሰዎች ላይ መከራ ከሚያስከትሉ ነገሮች ውስጥ የትኛውን በቅድሚያ ያጠፉ ነበር? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት፤ ትክክል ከሆነም ብዙ ሰዎች ተመሳሳይ ስሜት እንዳላቸው ግለጽ።] እስከ አሁን ድረስ ሰዎች በዘመናችን ላሉ ግራ የሚያጋቡ ችግሮች እምብዛም መፍትሔ ያገኙ አይመስልም። ሆኖም የሰው ልጆችን ያጠቁትን ችግሮች ሊያስወግድ የሚችል እንዲያውም የሚያስወግድ አለ። እስቲ በመዝሙር 145:16 ላይ የተገለጸውን ሐሳብ ልብ ይበሉ። [ጥቅሱን አንብበህ ከገጽ 11-13 ላይ ያሉትን ሥዕሎች አሳየው።] ይህ መጽሐፍ በገጽ 14 አንቀጽ 14 አሁን የተወያየንበትን ጥያቄ ያነሣና ቀጠል አድርጎ ‘ታዲያ ይህ የሚሆነው መቼ ነው?’ የሚል ጥያቄ ያቀርባል።” መጽሐፉ ለዚህ ጥያቄ መልስ እንደሚሰጥ ግለጽና ሰውዬው ፍላጎት ካሳየ መጽሐፉን አበርክትለት።
3 አለዚያም ቀጥሎ ካለው ጋር ተመሳሳይ የሆነ ነገር ልትናገር ትችላለህ፦
◼ “ምናልባት የሚያፈቅሩትን ሰው በሞት ማጣት የሚያስከትለው የከንቱነት ስሜት አጋጥሞዎት ይሆናል። አዝነውና ሁኔታውን ለመለወጥ ምንም ማድረግ እንደማይቻል ተሰምቶዎት ይሆናል። እነዚህን ጥያቄዎች አሰላስለውባቸው ሊሆን ይችላል። [በገጽ 76 አንቀጽ 1 ላይ ያሉትን ጥያቄዎች አንብብ።] ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት አያጽናናምን? መጽሐፍ ቅዱስ ለሙታን እርግጠኛ ተስፋ የያዘ መሆኑን ሲያውቁ ሊበረታቱ ይችላሉ። [ዮሐንስ 5:28, 29ን አንብብ።] ይህ መጽሐፍ ሙታን ያሉበትን ሁኔታና ወደፊት ምን ተስፋ እንዳላቸው ለማስተዋል ይረዳናል።” ምዕራፍ 8ን እና 20ን አውጣና በአጭሩ አብራራለት። ሰውዬው ፍላጎት እንዳለው ካሳየ መጽሐፉን ለመመርመር አጋጣሚ እንዲያገኝ አድርግ።
4 መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመሥከር ብዙ አጋጣሚዎች ይኖሩሃል። ባሉት ሁኔታዎች በራስህ አገላለጽ ቀጥሎ ካለው ጋር ተመሳሳይ የሆነ ነገር ልትናገር ትችላለህ፦
◼ “በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ብዙ ችግሮች አሉ። እርስዎም ከእነዚሁ ችግሮች አንዳንዶቹ እንደደረሱብዎት አያጠራጥርም። የሚያሳዝነው ግን ይበልጥ የሚጎዱት ንጹሐን የሆነ ሰዎች ይመስላል። አምላክ መከራን የሚያጠፋበት ጊዜ ይመጣል ብለው ያስባሉ?[መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] አምላክ ለሚያገለግሉት ሰዎች ምን ተስፋ እንደሰጠ ላሳይዎት። [መዝሙር 37:40ን አንብብና ከዚያ ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 99 ግለጥ።] ይህ መጽሐፍ አምላክ ክፋት እንዲኖር ለምን እንደፈቀደና እንዴት ወደ ፍጻሜው እንደሚያመጣው ያብራራል።
5 ወጣት አስፋፊ ከሆንክ ከገጽ 156-8 ላይ ባሉት ሥዕሎች ላይ የተመሠረተ አቀራረብ ልትጠቀም ትችላለህ። እንዲህ ብለህ በመጠየቅ ትጀምር ይሆናል፦
◼ “ይህን በመሰለ ዓለም ውስጥ መኖር ይፈልጋሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] እነዚህ ውብ ሥዕሎች በሙሉ የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተገለጸ ተስፋ ላይ የተመሠረቱ ናቸው። [የቀረቡትን ጥቅሶች አሳየው።] ይህ መጽሐፍ አምላክ ምድርን ገነት ለማድረግ ስለ ሰጠው ተስፋ በይበልጥ እንዲያውቁ ሊረዳዎት ይችላል። መጽሐፉ ሕይወት አድን እውቀት ያለበትና ጊዜ ወስደን ልናነበው የሚገባ መጽሐፍ ነው።”—ዮሐ. 17:3