ትምህርት ቤት ሊከፈት ነው
1 በመስከረም ወር ወጣት ልጆቻችን አዲስ የትምህርት ዘመን ይጀምራሉ። በዚህ ጊዜ በጉጉት የምንጠብቃቸው አስደሳች ነገሮች ይኖራሉ፤ ሆኖም የሚያሳስቡን ጥቂት ጉዳዮችም አሉ። ብዙ ልጆች አዲስ አስተማሪዎች ይመደቡላቸዋል፣ አዲስ ትምህርት ይሰጣቸዋል እንዲሁም ከማያውቋቸው ተማሪዎች ጋር ይገናኛሉ። ልጆቻችን ከትምህርት ቤት ባለ ሥልጣኖች ጋር መተባበርና በመሰሎቻቸው ተማሪዎች መወደድ ይፈልጋሉ። ይሁን እንጂ በመንፈሳዊ ሊጎዷቸው ከሚችሉ ነገሮች መጠንቀቅ እንደሚኖርባቸው መዘንጋት የለባቸውም።—1 ቆሮ. 15:33
2 ምሥክር ለሆኑ ልጆችና ወጣቶች አንዱ በጣም አሳሳቢ የሆነው ነገር በዛሬው ጊዜ በብዙ አገሮች ውስጥ ባሉ የትምህርት ተቋማት እየተስፋፋ ያለው በካይ የዓለም ተጽዕኖ ነው። ክርስቲያኖች ወጣቶችም ሆኑ አዋቂዎች የሥነ ምግባር አቋምን በተመለከተ በአሁኑ ወቅት የተስፋፉትን ዓለም መመዘኛዎችና አስተሳሰቦች ለመቃወም ድፍረት ያስፈልጋቸዋል። በይሖዋ ቃል ምክር በመመራት ሕይወታቸውን ‘መጠበቅ’ አለባቸው። (መዝ. 119:9 የ1980 ትርጉም) አሳቢ የሆኑ ወላጆች ለልጆቻቸው ተገቢ መመሪያ መስጠት እንዲችሉ በትምህርት ቤቱ ሥርዓተ ትምህርት ስለሚካተተው ነገር መረጃ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። በትምህርት ቤት ወይም በሌላ ቦታ የሚሰጠው ትምህርት የይሖዋ አገልጋዮች ከሚፈለግባቸው ቅድስናና ንጽሕና ጋር የሚፃረር ከሆነ በትምህርቱ መሳተፍ አይኖርብንም።—1 ጴጥ. 1:15, 16
3 ከዚህም ሌላ ሰንደቅ ዓላማ ማክበርን፣ የበዓላት አከባበርን፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ወይም ተሰባስቦ መጫወትን በተመለከተ ጥያቄ መነሳቱ የማይቀር ነው። ትምህርት ቤትና የይሖዋ ምሥክሮች የተባለው ብሮሹር በነዚህ መስኮች ወጣት ክርስቲያኖችን ይረዳል። ወላጆች በራሳቸው አነሣሽነት የዚህን ጽሑፍ አንድ ቅጂ ይዘው የልጆቻቸውን አስተማሪዎች ቢያነጋግሩ ሊከሰቱ የሚችሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ሊወጡ ወይም ሊቀንሱ ይችሉ ይሆናል። ይህ ብሮሹር የይሖዋ ምሥክሮች በአንዳንድ ጉዳዮች ለመሳተፍ የማይመርጡት ለምን እንደሆነ ሊያስገነዝበው እንደሚችል ለአስተማሪው ሊገለጹለት ይችላሉ። ይህን ማብራሪያ ለአስተማሪው መስጠቱ የትብብር መንፈስ ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሊኖረው ይችላል።
4 በተጨማሪም ክርስቲያን ወጣቶች ትምህርት ቤት የተባለውን ብሮሹር የግል ቅጂ በትምህርት ቤት ከሚጠቀሙባቸው የጥናት ጽሑፎቻቸው ጋር አብረው ቢይዙ ጥሩ ነው። በቅርቡ ይህን ብሮሹር በአማርኛ እንደምናገኝ ተስፋ እናደርጋለን። ብዙውን ጊዜ ሌሎች ተማሪዎች እምነታችን ላይ የሚያተኩሩ ጥያቄዎች ሲሰነዝሩ የመመሥከር አጋጣሚዎች ይፈጠራሉ። ከዚህም ሌላ ምክር የሆኑ ልጆች ቀኑ ያላለፈበት፣ የምሥክሮች ስም በትክክል የተሞላበትና የተፈረመበት በቅድሚያ የተሰጠ የሕክምና መመሪያ/የሕክምና ባለሙያዎችን ከኃላፊነት ነፃ የሚያደርግ ሰነድ ወይም የመታወቂያ ወረቀት በግል መያዝ አለባቸው። እነዚህን ምክሮች በሥራ ላይ የሚያውሉ በእርግጥም ‘ብልህ ክፉን አይቶ ይሸሸጋል’ እንደተባለለት ሰው ይሆናሉ።—ምሳሌ 22:3